Sunday, October 6, 2013

SEMAYAWI PARTY ON ITS ALTERNATIVE CONSTITUTION(አማራጭ ሕገ መንግሥት?) THAT AIMS TO REPLACE THE FEDERAL SYSTEM WITH UNITARY SYSTEM

Image
በቅርቡ ሰማያዊ ፓርቲ ሕገ መንግሥት ማርቀቁን ከገለጸ በኋላ የአማራጭ ሕገ መንግሥት አንድምታና አስፈላጊነት ላይ በርካቶች እየተወያዩ ነው፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው የፖለቲካና የሕግ ኤክስፐርቶች፣ እንዲሁም የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የፓርቲው ውሳኔ እንቆቅልሽ እንደሆነባቸው የገለጹ ሲሆን፣ ጥቂቶች ግን ሕገ መንግሥት በአማራጭነት ጥቅም ላይ ሊውል ስለማይችል እንደ ‹ሕገ መንግሥታዊ ትችት› ሊወሰድ እንደሚገባ ያመለክታሉ፡፡ 
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በርካታ መቀመጫ ያለው ፓርቲ እንኳን ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ ለማድረግ የተወሳሰበ ሒደት ባለበት አገር፣ ከተቋቋመ ጥቂት ዓመታት የሆነውና በፓርላማ አንድም መቀመጫ የሌለው ፓርቲ፣ የአገሪቱ የበላይ ሕግ ለሆነው የኢፌዲሪ ሕገ መንገሥት አማራጭ ሕገ መንግሥት ማዘጋጀቱ በርካታ ጥያቄዎችን አስነስቷል፡፡ 
ሕገ መንግሥት በሚረቀቅበት ጊዜና ማሻሻያ ሲደረግ እንደ አንድ ጉዳዩ እንደሚመለከተው አካል የፖለቲካ ፓርቲዎች ንቁ ተሳትፎ ማድረጋቸው የተለመደ ቢሆንም፣ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ በሥራ ላይ ባለበትና ፓርላማውም በአንድ ፓርቲ ፍፁም የበላይነት ሥር በሆነበት ሁኔታ አማራጭ ሕገ መንግሥት ማርቀቅ የትም ተሰምቶ አያውቅም፡፡ 
ሰማያዊ ፓርቲ ረቂቅ ሕገ መንግሥት በኤክስፐርቶች መዘጋጀቱንና ፓርቲው ካፀደቀው በኋላ በሕዝቡ ውይይት ተደርጎበት እንደሚዳብር ገልጿል፡፡ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠንካራ የፖሊሲና የስትራቴጂ አማራጭ የላቸውም እየተባሉ የሚተቹ ቢሆንም፣ አማራጭ ሕገ መንግሥት እስከማቅረብ ይደርሳሉ ብሎ የጠበቀ አልነበረም፡፡ የፓርቲው ሊቀመንበር ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት ረቂቁ በፓርቲው ከፀደቀ ሕዝቡ፣ የሲቪል ማኅበራት፣ ምሁራንና የአገር ሽማግሌዎች አስተያየት፣ ትችትና ክርክር እንደሚያደርጉበት ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በ2007 ዓ.ም. ለሚካሄደው ብሔራዊ ምርጫ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ድጋፍ ለማግኘት ረቂቁ ሕገ መንግሥት ጉልህ ጠቀሜታ እንደሚኖረውም ጠቁመዋል፡፡ 
እንደ ኢንጂነር ይልቃል አተረጓጎም ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን መተቸት ሕገ መንግሥታዊ መብት ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ውስጥ በተቀመጡ አንዳንድ ድንጋጌዎች ላይ ፓርቲያቸው ከገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ የተለየ ግልጽ አቋሞች እንዳሉት ያስታወሱት ኢንጂነር ይልቃል፣ ሕገ መንግሥቱን ለመቀየር መፈለጉ ሊደንቅ እንደማይገባ አመልክተዋል፡፡ ፓርቲው ከቡድን መብት ይልቅ የግለሰብ መብቶች፣ ከብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሉዓላዊነት ይልቅ የሕዝቦች ሉዓላዊነት፣ ከመንግሥትና ሕዝብ የመሬት ባለቤትነት ይልቅ የግለሰቦች የመሬት ባለቤትነት፣ እንዲሁም ከፌዴራላዊ የመንግሥት አወቃቀር ይልቅ አሀዳዊ የመንግሥት አወቃቀር ተፈጻሚነት እንዲኖረው ይፈልጋል፡፡ ረቂቁ ሕገ መንግሥት በዋነኛነት እነዚህን አንኳር ነጥቦች የሚያንፀባርቅ እንደሆነም ኢንጂነር ይልቃል አስታውቀዋል፡፡ 
በረቂቁ ሕገ መንግሥት አማካይነት ሰማያዊ ፓርቲ ሕዝቡን በአዲስ አመለካከትና አቅጣጫ ለማንቀሳቀስ ማሰቡን ይገልጻሉ፡፡ ይሁንና ረቂቁ ሕገ መንግሥት እንደ ተራ የፓርቲ ፕሮግራም መታየት እንደሌለበት ይጠቁማሉ፡፡ ‹‹ረቂቁ ሕገ መንግሥት የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ በሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግሥት ላይ ትችት እንዲያቀርቡና መንግሥትንና አገርን እንደገና ለማዋቀር የሚያስችሉ የሕዝብን ጥቅም የሚያንፀባርቁ አዳዲስ መንገዶችን እንዲጠቁሙ ለማስቻል እንደ መሠረት ያገለግላል፡፡ ፓርቲውም ወዴት እየሄደ እንደሆነ ለሕዝቡ ለማሳወቅ ይጠቅማል፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡ 
ሰማያዊ ፓርቲ ረቂቁን ሕገ መንግሥት ለማዘጋጀት የተነሳሳው በሦስት ምክንያቶች መሆኑን በመግለጽ፣ አንደኛ ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ የሕገ መንግሥት ማርቀቅ ሒደቱን በበላይነት ስለተቆጣጠረው የአሁኑ ሕገ መንግሥት የፓርቲው ፍላጎት የሚንፀባረቅበት ስለሆነ ነው ብለዋል፡፡ መሬትን የሚመለከተውን ድንጋጌ እንደ ምሳሌ ይጠቅሳሉ፡፡ ሁለተኛ ሕገ መንግሥቱ በቂ ውይይት ሳይደረግበት በጥድፊያ የተረቀቀ መሆኑን፣ ሦስተኛ ሕገ መንግሥቱ እርስ በርስ የሚጋጩ አንቀጾች የያዘ ስለሆነ ነው ይላሉ፡፡ የመብት ገደቦችን እንደ ምሳሌም ይጠቅሳሉ፡፡ ‹‹አንዳንድ አንቀጾች መብቶች ለሕዝብ ደኅንነት ሲባል ወደፊት በሚወጣ ሕግ ሊገደቡ እንደሚችሉ ይገልጻሉ፡፡ በአንድ በኩል የሰጠውን መብት በሌላ በኩል በመገደብ ይወስደዋል፤›› በማለትም ለማብራራት ሞክረዋል፡፡ እነዚህ ምክንያቶች ከሕገ መንግሥቱ መፅደቅ ጀምሮ ሲነሱ የነበሩና አዲስ ያልሆኑ ሲሆን፣ በመብቶች ላይ ገደብ ማድረግም የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ልዩ ባሕሪ እንዳልሆኑ የሚያስረዱ ምሁራን አሉ፡፡ 
ወደ ሕገ መንግሥቱ ማርቀቅ ሒደት ስንመለስ
ኢንጂነር ይልቃል የጠቀሱት ከሕገ መንግሥት የማርቀቅ ሒደት ጋር የተያያዙ ችግሮች የበርካታ ሕገ መንግሥታዊ ምሁራንን ትኩረት ይስባሉ፡፡ ሕገ መንግሥት የማርቀቅ ሒደት በተፈጥሮው አስፈላጊ የሆኑ የፖለቲካ ኃይሎችን፣ የሚመለከታቸው የኅብረተሰብ ክፍሎችን፣ እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻዎችን ያሳትፋል፡፡ አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት የማርቀቅ፣ የማወያየትና የማፅደቅ ሒደት የተፈጸመው በበቂና በሚያመረቃ፣ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ውይይትና የሐሳብ ልውውጥና ተሳትፎ ሳያረጋግጥ እንደነበር ይጠቅሳሉ፡፡ የሽግግር ዘመኑ መንግሥት ወሳኝ ሚና ያላቸው ተሳታፊዎችን ተሳትፎ በመገደቡ ይተቻል፡፡ 
ከ1987 ዓ.ም. ጀምሮ ብሔርን መሠረት ያደረገ ውሳኔ አሰጣጥና የፖለቲካ ውድድር በአገሪቱ የተንሰራፋ ሲሆን፣ አንዳንዶች ይህ ሥርዓት ወደ ጂኦግራፊያዊ የፌዴራል መዋቅር እንዲቀየር ሲጠይቁ ሌሎች ግን ወደ አሀዳዊ የመንግሥት መዋቅር እንዲመለስ ይፈልጋሉ፡፡ እንደ ፕሮፌሰር ምናሴ ኃይሌ ያሉ ምሁራን እንዲያውም የፌዴራል ሥርዓቱን ‹‹የጎሳ ፌዴራሊዝም›› ሲሉ ነው የሚጠሩት፡፡
ፕሮፌሰር ምናሴ ኃይሌ ሕገ መንግሥቱ ለክልሎችና በውስጣቸው ለሚኖሩ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሉዓላዊነት በመስጠት ያልተመጣጠነ ሥልጣን እንደሚሰጣቸው ይገልጻሉ፡፡ የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 8 እንደ ፕሮፌሰር ምናሴ ያሉ ምሁራን ኢትዮጵያ እንድትበታተን ሊያደርግ ይችላል በማለት በሥጋት ሲያዩት፣ ሌሎች በአንፃሩ ከአንቀጽ 39 ጋር በጥምረት ሲነበብ የብሔሮች እኩልነትን ቢያንስ በሥነ ልቦና ደረጃ የሚያረጋግጥ የአዲሲቱ ኢትዮጵያ ምዕላድ እንደሆነ ያስባሉ፡፡ ውስጣዊና ውጫዊ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ነፃነትን ያቀፈው ሕገ መንግሥት የተለያዩ ቡድኖችን ልዩ ፍላጎት በማስተናገድ፣ የመሠረታዊ እኩልነትን መርህ በማክበርና የማንነት ጥያቄን በመመለስ በአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ማስፈኑን በመጥቀስ የሚከራከሩም አሉ፡፡ 
ሥርዓቱ በክልሎችና በብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች አጠቃላይ ፍላጎትና በግለሰብ ዜጎች ፍላጎት መካከል ሚዛን ለመጠበቅ የተለያዩ ተግዳሮቶች አሉበት፡፡ ብሔርተኝነት ሊያስከትል የሚችለውን አሉታዊ ተፅዕኖ የተለያዩ ብሔሮች በሚያነሷቸው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ባሕላዊ የመደራደሪያ ነጥቦችና በሚደርሱባቸው ስምምነቶች ላይ ብሔራዊ አንድነት በሒደት ወደ መፍጠር በማምራት መቀነስ እንደሚቻልም የሚጠቁሙ አሉ፡፡ 
ሕገ መንግሥቱ መንግሥት ለፈለገው ዓላማ ብቻ ሲል የሚጠቀምበት የፕሮፓጋንዳ መሣሪያ እንደሆነ የሚጠቁሙ አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች፣ ከላይ ሲታይ ዴሞክራሲያዊ ቅርፅ በመላበስ የሚያምታታ ገጽታ ያለው ቢሆንም፣ ከጀርባው ማክሲስታዊና ሌሊናዊ የፖለቲካ ጭምብሉን እንደደበቀ ይተቻሉ፡፡ 
ሕገ መንግሥት የማርቀቅ ሒደቱ ባለድርሻ አካላቱን በበቂ ሁኔታ ማሳተፍ አለማሳተፉ ላይ በርካታ ጥርጣሬዎች ያሉ ቢሆንም የግለሰቦች ነፃነቶችን፣ ሰብዓዊ መብትና ዴሞክራሲን የመሳሰሉ በየትኛውም ዘመናዊ ሕገ መንግሥት ሊታዩ የሚገባቸውን እሴቶች ሕገ መንግሥቱ ዋነኛ ማጠንጠኛ አድርጎ አቅፏቸዋል፡፡ የሕገ መንግሥቱ መፅደቅና ሥራ ላይ መዋልን ጀምሮ የተጀመረው የኢትዮጵያ አንድነት አቀንቃኞችና የብሔር ፌዴራሊዝም አቀንቃኞች ግብግብ በምርጫ 87፣ 92 እና 97 ታላቅ የምርጫ አጀንዳ የነበረ ቢሆንም፣ በምርጫ 2002 ግን አጀንዳው ከፖለቲካ ምኅዳር መጥበብ በላይ ቦታ አልነበረውም፡፡ እነ ኢንጂነር ይልቃል በምርጫ 2007 መልሰው ዋነኛ አጀንዳ ያደርጉት ይሆን?
ለሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት መታመን
አዲስ አማራጭ ሕገ መንግሥት ማርቀቅ ፓርቲው ላለው ለሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት የመታመን ግዴታ የሚኖረውን ተፅዕኖ በተመለከተ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ ኢንጂነር ይልቃል ሲያብራሩ፣ ለሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት መታመን አማራጭ ሕገ መንግሥት ከማዘጋጀት ጋር የሚያገናኘው ነገር እንደሌለ ገልጸዋል፡፡ ‹‹በሕገ መንግሥቱ ለተቀመጡት ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች ታማኝ ነን፡፡ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱን ለማጎልበት የበኩላችንን ሚና ለመጫወት ነው የተቋቋምነው፡፡ ‹‹ታማኝ›› ለመሰኘት እያንዳንዱን የኢሕአዴግ ውሳኔ መቀበል አይጠበቅብንም፡፡ በ1983 ዓ.ም. መልካም ሐሳብ ይዞ አገሪቱን መምራት የጀመረው ኢሕአዴግ አሁን የለም፡፡ አሁን ያለው ኢሕአዴግ የሚዲያ ነፃነትን የሚያፍን፣ የሲቪል ማኅበራትንና የፓርላማ ነፃነትን የማይፈቅድ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ፈላጭ ቆራጭነቱ እየጨመረ ነገር ግን በሕዝብ ያለው ተቀባይነት እየቀነሰ ነው፡፡ በአጠቃላይ ለፓርቲው ነገሮች ከቁጥጥር ውጪ እየሆኑ ነው፡፡ ለዚህ ነው የአገሪቱን ችግሮች የሚቀርፍ አዲስ የሕገ መንግሥት ረቂቅ ያዘጋጀነው፤›› በማለትም አብራርተዋል፡፡ 
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር የሆኑትና በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ሐሳባቸውን በመግለጽ የሚታወቁት ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ ሕገ መንግሥቱን በከፊልም ሆነ በሙሉ የመቀየር ሥልጣን በራሱ በኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት የተሰጠ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ከሃይማኖታዊ ሰነድ በተለየ ሕገ መንግሥት እንደ አንድ የፖለቲካና የሕግ ሰነድነት የተለያዩ ተጨባጭ ሁኔታዎችን ከግምት በማስገባት ራሱን ለለውጥና ለመሻሻል ያጋለጠ እንደሆነ ዶ/ር ዳኛቸው ጠቁመዋል፡፡ ስለ ሕገ መንግሥት ለውጥ መናገር ‹‹ነውር›› በሆነበት አገር ሰማያዊ ፓርቲ ረቂቅ ሕገ መንግሥት ማዘጋጀቱ ዜጎች ሕገ መንግሥቱን አስመልክተው በነፃነት እንዲወያዩና ሐሳብ እንዲለዋወጡ ተጨማሪ ኃይል እንደሚሰጥ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡
የሕገ መንግሥት ኤክስፐርት የሆኑት ዶ/ር ያሬድ ለገሰ ሕጋዊ ሰውነትን በሕገ መንግሥቱ ላገኘ አንድ ተቃዋሚ ፓርቲ አማራጭ ሕገ መንግሥት ማርቀቅ ውጤት አልባ ተፅዕኖ እንዳለውና ፓርቲው ለሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ታማኝ አለመሆኑን እንደሚያሳይ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ አማራጭ ሕገ መንግሥት ማርቀቅ በራሱ ሕገ ወጥ ባይሆንም፣ ፖለቲካዊ ጥንቃቄ የጎደለው ድርጊት መሆኑን ዶ/ር ያሬድ አመልክተዋል፡፡
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሕገ መንግሥት ኤክስፐርት የሆኑት አቶ እንዳልካቸው ገረመው በተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅት ሕገ መንግሥት ማርቀቅ በወንጀል ሕጉ ‹‹ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን የማፍረስ ወንጀል›› በሚል የተቀመጠውን ድንጋጌ በግልጽ የሚጥስ ወንጀል እንደሆነ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ አቶ እንደልካቸው ድርጊቱ የሕገ መንግሥታዊ መታመን ፈተናን እንደሚወድቅም አመልክተዋል፡፡ ‹‹ረቂቁ ሕገ መንግሥቱን በሙሉ የመቀየር ዕቅድ ካለው ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን እንደመፃረር ነው የሚቆጠረው፡፡ በአንድ አገር ውስጥ ሁለት የተለያዩ ሕገ መንግሥቶች ሊኖሩ አይችሉም፤›› በማለትም አክለዋል፡፡ 
ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ አይደለም
የአገር ውስጥና የውጭ የሕገ መንግሥት ኤክስፐርቶች በተለያየ ወቅቶች የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ሐሳቦችን ዝርዝር ያቀረቡ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል የመገንጠል ጥያቄ፣ የመሬት ባለቤትነት፣ ሕገ መንግሥታዊ አተረጓጎም፣ የምርጫ ሥርዓት፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አወቃቀር፣ የጎንና ቀጥተኛ የሥልጣን ክፍፍልና ሥርጭት፣ ፓርላሜንታሪያዊ የመንግሥት ቅርፅ፣ የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶች፣ የፕሬዚዳንቱ ቢሮ፣ ብሔራዊ ቋንቋ፣ ሴቶችና የፖለቲካ ተሳትፎ፣ እንዲሁም የሰብዓዊ መብት ገደብ ይገኙበታል፡፡
ሰማያዊ ፓርቲ ባዘጋጀው ረቂቅ ሕገ መንግሥት ውስጥ በዋነኛነት ትኩረት የተደረገባቸው ነጥቦች በአንድም ይሁን በሌላ ሁኔታ የእነዚህ ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ ሐሳቦች አካል ናቸው፡፡ አዲስ የሕገ መንግሥት ረቂቅ ከማዘጋጀት ፓርቲው ለምን ማሻሻያ ሐሳብ እንዳልመረጠ በሪፖርተር የተጠየቁት ኢንጂነር ይልቃል፣ የምሁራን የምክክር ኮሚቴዎች ወይም ቲንክ ታንክ ሲቪል ማኅበራትና የአደባባይ ምሁራን የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ሐሳብ ለማቅረብ ሞክረው በኢሕአዴግ ተቀባይነት እንዳጡ አስታውሰዋል፡፡ ‹‹እንደ ፓርቲ ሕገ መንግሥትን አስመልክቶ ያለንን ሐሳብ የማስፈጸም አቅም አለን፡፡ ሦስት አራተኛውን የፓርላማ መቀመጫ በማሸነፍ በሥራ ላይ ያለውን ሕገ መንግሥት ማሻሻል እንችላለን፡፡ ነገር ግን ያን የማድረግ ሥልጣን እስኪኖረን ድረስ የሕዝቡን አስተያየት ከተቻለም ስምምነት አስቀድመን ማግኘት እንፈልጋለን፤›› ሲሉም አብራርተዋል፡፡ ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ ሥነ ሥርዓቱ እጅግ የተወሳሰበና አስቸጋሪ ቢሆንም፣ አዲስ ሕገ መንግሥት ከማርቀቅ ግን እጅግ የተሻለ መንገድ መሆኑን ዶ/ር ያሬድ ለገሰ ገልጸዋል፡፡
እንደ አዲስ የሚጀምር ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት
እስከዛሬ ድረስ ሥራ ላይ የነበሩት ሕገ መንግሥቶች ከአንድ ሥርዓት በላይ ሳያገለግሉ ተቀይረዋል፡፡ የበለፀጉት አገሮች ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓታቸው ቀጣይነት ያለውና የተለያዩ መንግሥታት መጠነኛ ማሻሻያ እያደረጉባቸው ሳይለወጡ ይቀጥላሉ፡፡ አዲስ የሕገ መንግሥት ረቂቅ ማዘጋጀት ዘላቂ ሥርዓት ከመፍጠር ይልቅ በአገሪቱ አለመረጋጋትንና እንደ አዲስ የሚጀምር ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት አይፈጥርም ወይ ተብለው የተጠየቁት ኢንጂነር ይልቃል፣ በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት ከኢትዮጵያ ሕዝቦች ፍላጎት ይልቅ የሚያንፀባርቀው የኢሕአዴግን ፍላጎት ስለሆነ መቀየሩ ከሚያመጣው ችግር ጭምር የግድ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ 
የሕገ መንግሥት ኤክስፐርት የሆኑት ጌዲዮን ጢሞቲዎስ የትኛውም የዓለም ሕገ መንግሥት ፍፁም ተቀባይነት እንደሌለው ገልጸው ተቀባይነት አንፃራዊ ደረጃ እንዳለው አመልክተዋል፡፡ የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት የተቀባይነት ችግር ቢኖርበትም፣ ቀጣይነት ያለው ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ለመፍጠር ሲባል ሕገ መንግሥቱ ሥልጣን ላይ ካለው ፓርቲም ባሻገር ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባ ይገልጻሉ፡፡ ‹‹ሕገ መንግሥቱን በሦስት የተለየዩ ምክንያቶች ማቆየት ያስፈልጋል፡፡ አንደኛ ጠንካራ የብሔርተኝነት ስሜት ባላቸው ክልሎች ሕገ መንግሥቱ ተቀባይነት አለው፡፡ ሁለተኛ አዲስ መንግሥት ሥልጣን ላይ በወጣ ቁጥር አዲስ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት የመፍጠር የኢትዮጵያ አዝማሚያ መሰበር አለበት፡፡ ምክንያቱም ይህ ሕገ መንግሥቶች ሥልጣን ላይ ባለው ኃይል ልክ የተሰፉ ናቸው የሚለውን አመለካከት መቀየር ያስፈልጋል፡፡ ሦስተኛ አዲስ ሕገ መንግሥት ማርቀቅ ረዥም ጊዜ የሚወስድና ውስብስብና ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ሒደት ነው፡፡ ከወጪ በላይ ደግሞ በአገሪቱ ያሉ ልዩነቶች በተለያዩ ቡድኖች መካከል እንዲስፋፉ ዕድል ይፈጥራል፤›› በማለት አዲስ ሕገ መንግሥት የማርቀቅ ሙከራ ሊወገድ እንደሚገባ ተከራክረዋል፡፡ 
ዲዛይኑ ያልፈጠራቸው ችግሮች 
ሕገ መንግሥቱ ያስቀመጣቸው እሴቶች በኢትዮጵያ በዕለት ተዕለት የሕይወት እንቅስቃሴዎች ተፈጻሚ እንዳልሆኑ በመጥቀስ ምሁራን፣ የፖለቲካ ተንታኞችና ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች በየጊዜው ቅሬታ ማቅረባቸው የተለመደ ተግባር ነው፡፡ ተቺዎች ሕገ መንግሥቱ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ከመፍጠርም በላይ የተመቸ ቢሆንም፣ ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ ባለው ከመጠን ያለፈ የበላይነት በውሳኔ አሰጣጥ ሒደቱ ላይ የሚመለከታቸው አካላት እየተሳተፉ እንዳልሆነ ያመለክታሉ፡፡ 
እነዚህ ተቺዎች በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ ያሉት ችግሮች ከሕገ መንግሥታዊ የዲዛይን ችግር የተነሱ እንዳልሆኑም ይጠቁማሉ፡፡ ከሕገ መንግሥት ትርጉምና ዴሞክራሲንና መብቶችን ለመለየት ሰፊና አምታች ቋንቋ መጠቀሙና የመሳሰሉ የዲዛይን ችግሮች ቢኖሩትም፣ ሕገ መንግሥቱ ተቀባይነት ያለው መሆኑን ተቺዎቹ ጭምር ይመሰክሩለታል፡፡ 
የሕገ መንግሥት ኤክስፐርት የሆኑት ፀጋዬ ረጋሳ የሕገ መንግሥቱ ቀዳሚ (Original) ተቀባይነት ከኢሕአዴግ የሒደቱ የበላይነት ጋር በተያያዘ ደካማ ቢሆንም፣ የሕገ መንግሥቱን ተፈጻሚነት በመጨመርና በማብዛት ለውጥ (Derivative) ተቀባይነት ሊያገኝ እንደሚችል ያመለክታሉ፡፡ ‹‹ይህን ለማምጣት ለሕገ መንግሥቱ መታመን ያስፈልጋል፡፡ ታማኝነት ሕገ መንግሥታዊ ተቀባይነትን ያመጣል፡፡ ምሁራን ይህን አርነታዊ ሕገ መንግሥታዊ አፈጻጸም ይሉታል፡፡ በሕገ መንግሥታዊ ዲዛይንና በሕገ መንግሥታዊ አፈጻጸም መካከል ሊሞላ የሚገባው ክፍተት አለ፡፡ ክፍተቱ ሊሞላ የሚችለው በተቀባይነት፣ በሕገ መንግሥታዊነትና ምሉዕ በሆነ የሕገ መንግሥት አፈጻጸም የተነሳ ብቻ ነው፤›› ሲሉም ፀጋዬ ያጠቃልላሉ፡፡ 
ኢትዮጵያ በፌዴራልና በክልል ደረጃ ያሉ ተቋማትን አፈጻጸም በማጠናከር ጠንካራ አገር ሆኖ መቀጠል እንደምትችል ይታመናል፡፡ ዶ/ር አደም ካሴ አዲስ ሕገ መንግሥት ከማርቀቅ ይልቅ የፖለቲካ ባሕሉን ማስተካከል የተሻለ አማራጭ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ የሕገ መንግሥት ዲዛይን የራሱ አሉታዊ ተፅዕኖ ቢኖረውም ለአገሪቱ ችግር እንደ ዓቢይ ምክንያት እንደማይታይም አመልክተዋል፡፡ የአገሪቱ የፖለቲካ ባሕል ሳይቀየር የትኛውም የሕገ መንግሥት ዲዛይን ፈጠራ ሥርዓቱን ሊያሻሽል እንደማይችልም አስረድተዋል፡፡ 
የአሜሪካ ሕገ መንግሥት የሁሉንም ዜጎች እኩልነት ያረጋግጣል፡፡ ነገር ግን የሕገ መንግሥቱ ሙሉ አፈጻጸም በአዝጋሚ ሒደት የተጠናቀቀ ስኬት ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ ግማሽ ዕድሜ ውስጥ ሴቶች በአሜሪካ መምረጥ አይችሉም ነበር፡፡ በተመሳሳይ ባርነት በግልጽ የተከለከለ አልነበረም፡፡ በመንግሥት ስፖንሰር የሚደረግ የአፍሪካ አሜሪካውያን መገለል የቆመው ከጥቂት አሥርት ዓመታት በፊት ነው፡፡ እያንዳንዱ ከሕገ መንግሥት ጋር የተያያዘ ችግር ከሚፈጸምበት ባሕል ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በኢትዮጵያም ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ሙሉ በሙሉ እስኪዳብር ጊዜ መውሰዱ አይቀርም፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ ረቂቅ ሕገ መንግሥት ጊዜውን የሚያራዝም እንጂ ለዚህ ባሕል መዳበር የሚጨምረው አዎንታዊ ተፅዕኖ እንደሌለ አስተያየት ሰጪዎች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

No comments:

Post a Comment