Wednesday, October 16, 2013

አለማቀፍ ጠበቆች የኢትዮጵያን ባለስልጣናት ለፍርድ ለማቅረብ እንቅስቃሴ ጀመሩ


በወጣት አብዱላሂ ሁሴን አማካኝነት በኢትዮጵያ የኦጋዴን ክፍል የተፈጸመውን የጦር ወንጀልና የሰብአዊ መብት ጥሰት ፊልም የሚያሳይ ዘጋቢ ፊልም በስዊድን ቁጥር አንድ ቴሌቪዥን በትናንትናው እለት መቅረቡን ተከትሎ አለማቀፉ ጠበቆች ጉዳዩን ወደ አለማቀፍ ፍርድ ቤት ለመውሰድ እንቅስቃሴ ጀመረዋል።
ወጣት አብዱላሂ ለኢሳት እንደገለጸው ፊልሙ ከተላለፈ በሁዋላ ሚዲያዎች ሸፊ ሽፋን የሰጡት ሲሆን፣ ስቴላም የተባሉ የ አይ ሲ ጄ ጠበቃ ጉዳዩን ፍርድ ቤት እንደሚያቀርብ በሬዲዮ ይፋ አድርገዋል።
የስዊድን የጦር ወንጀል ኮሚሽን ፍርድ ቤትም ማስረጃዎችን በመመርመር ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ለመውሰድ ከወጣት አብዲ ጋራ ቀጠሮ ይዘዋል። ጠበቆቹ ጄኔቫ ካለው አይሲጄ ጋር እና ከሌሎችም የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ጋር በጋራ በመሆን ጉዳዩን ወደ አለማቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት ለመውሰድ እንደሚሞክሩ ተናግሯል።

ትናንት በተላለፈው ፊልም ውስጥ ከዚህ በፊት በኢሳት ያልቀረቡ መረጃዎች መቅረባቸውን ወጣት አብዲ ገልጿል።
ልዩ ፖሊስ እየተባለ በሚጠራው ሀይል የተፈጸመ የዘር ማጥፋት ወንጀልን የሚያሳይ መረጃ መካተቱትን፣ የክልሉን ፕሬዚዳንት የተቸች አንዲት ሴት በኦበነግ አባልነት ስትፈረጅ የሚያሳይ መረጃ ተካቶበታል ። የክልሉ ፖሊስ ሀላፊው በእስር ላይ የሚገኙትን ሴቶች በመድፈር ብዙ ህጻናት በእስር ቤት ውስጥ መወለዳቸውን በፖሊሶች በራሳቸው ሲነገር የሚያሳይ ፊልም መካተቱትን ወጣት አብዱላሂ ገልጿል።
ፊልሙ ” የዲክታተሮች እስረኞች” የሚል ርእስ ተሰጥቶታል።
ጉዳዩን በማስመልከት የአለማቀፍ የህግ ባለሙያዎች ኮሚሽን በእንግሊዝኛ ኢንተርናሽናል ኮሚሽን ኦፍ ጁሪስትስ ኮሚሽነር የሆኑት ስቴላ ጋርደ ለኢሳት እንደገለጹት የወንጀሉን ፈጻሚዎች ወደ ፍርድ ለማቅርብ የሚችሉትን ሁሉ እንደሚጥሩ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የአለማቀፍ ወንጀል ( ICC) ፈራሚ አገር ባለመሆኑዋ ማስረጃውን በቀጥታ ለፍርድ ቤቱ መላክ እንደማይቻል የገለጹት ኪሚሽነር ጋርደ፣ ይሁን እንጅ ሰቆቃን ለመከላከል የተቋቋመው ኮሚቴ ( Committe Against Torture) ፈራሚ አገር በመሆኑ ጉዳዩን በዚሁ በኩል ለመከታተል እና የስዊድን ፖሊስ ምርመራ ጀምሮ እርምጃ ለመውሰድ እንዲችሉ ጥረት እንደሚያደርጉ ለኢሳት ገልጸዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰብአዊ መብት ኮሚቴ እነዚህን ማስረጃዎች እንዲያገኙ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።
የኖርዌይ የቴሌቪዥን ጣቢያም ፊልሙን በቅርቡ ያሰራጫል ተብሎ ይጠበቃል። ፊልሙ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ተተርጉሞ በተለያዩ አለማቀፍ የመገናኛ ብዙሀን ይቀርባል።
በጉዳዩ ላይ የኢትዮጵያ መንግስት የሰጠው አስተያየት የለም።
ምንጭ:- ኢሳት

No comments:

Post a Comment