Friday, October 18, 2013

ኢትዮጵያ፡ በፖለቲካ እስረኞች ላይ የማሰቃየት ድርጊት ይፈጸማል


በግዳጅ የእምነት ቃል እንዲሰጡ ለማድረግ ፖሊስ በጋዜጠኞች እና በተቃዋሚዎች ላይ በደሎችን ይፈጽማል።

Ethiopia
(ናይሮቢ፣ ጥቅምት 7 ቀን 2006 ዓ.ም) የኢትዮጵያ ባለስልጣናት አዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው ዋና የማሰሪያና የምርመራ ጣቢያ ውስጥ በፖለቲካ ሳቢያ የተያዙ እስረኞችን እንደሚያሰቃዩ እና ለጎጂ አያያዝ እንደሚያጋለጡ ሂዩማን ራይትስ ዎች ዛሬ ይፋ ባደረገው ሪፖርት አስታወቀ፡፡ ማዕከላዊ በመባል በሚታወቀው የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ዘርፍ የሚፈጸሙ ህገ ወጥ ተግባራትን ለማስቆም እንዲሁም የሚፈጸሙትን በደሎች በተመለከተ የሚቀርቡ ቅሬታዎች በገለልተኛ ወገን እንዲመረመሩ እና አጥፊዎቹንም ተጠያቂ ለማድረግ የኢትዮጵያ መንግስት አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ አለበት፡፡

74 ገፆች ያሉት እና “ ‘የሚፈልጉት የእምነት ቃል ነው’ ፡ ማሰቃየት እና ጎጂ አያያዝ በኢትዮጵያ ማዕከላዊ ፖሊስ ጣቢያ” በሚል ርዕስ የወጣው ይኸው ሪፖርት ከ 2002 ዓ.ም ጀምሮ በማዕከላዊ የተፈፀሙ ከባድ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች፣ በህገ ወጥ መንገድ የሚካሄድ ምርመራን እና በዚያ ያለውን አስከፊ የእስር ሁኔታ ይዘረዝራል። በማዕከላዊ ከሚታሰሩት መካከል ተቃዋሚ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች፣ የተቃውሞ ሰልፍ አስተባባሪዎች እና ጎሳን መሰረት ያደረገ ትግል የሚያካሂዱ አማፂያንን ይደግፋሉ የሚባሉ ሰዎች ይገኙበታል፡፡ ሂዩማን ራይትስ ዎች ከ35 የሚበልጡ የቀድሞ ታሳሪዎችን እና ቤተሰቦቻቸውን ያነጋገረ ሲሆን እነሱም የማዕከላዊ ሃላፊዎች መረጃ እና የእምነት ቃል ለማግኘት ሲሉ እንዴት መሰረታዊ ፍላጎቶቻቸውን እንደከለከሏቸው፣ እንዳሰቃዩአቸው፣ በተለያየ መልኩ ያልተገባ አያያዝ እንደፈጸሙባቸው እና የቤተሰብ አባላትን እና የሕግ ጠበቃ እንዳያገኙ እንደከለከሏቸው በዝርዝር ገልጸዋል፡፡
በሂዩማን ራይትስ ዎች የአፍሪካ ምክትል ዳይሬክተር ሌስሊ ሌፍኮ “መረጃ ለማግኘት ሲሉ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት በዋና ከተማዋ እምብርት በየጊዜው ጥቃት ይፈፅማሉ” ብለዋል፡፡ ሌፍኮ እንዳሉት “ድብደባ፣ ማሰቃየት እና በማስገደድ ቃል መቀበል ለጋዜጠኞች እና ተቃዋሚ ፖለቲከኞች የተገባ አይደለም።”
ሂዩማን ራይትስ ዎች እንዳለው በኢትዮጵያ ከ1997ቱ አወዛጋቢ ምርጫ በኋላ በሰላማዊ ተቃዎሞ ላይ የሚደረገው ጫና ተባብሷል። በማዕከላዊ ተይዘው ምርመራ የሚካሄድባቸው የመንግስት ተቃዋሚ ናቸው ተብለው የሚታሰቡ ሰዎች ጥብቅ በሆነው የሀገሪቱ የፀረ ሽብርተኝነት ሕግ መሠረት መከሰስን ጨምሮ የዘፈቀደ እስር እና ፖለቲካን መሠረት ያደረገ ማሳደድ ይፈጸምባቸዋል።የማዕከላዊ ሃላፊዎች በዋናነትም መርማሪ ፖሊሶች እስረኞቹን በተለያየ መንገድ ያሰቃያሉ፤ ጎጂ አያያዝም ይፈጽማሉ፡፡ በተለይ በምርመራ ጊዜ ታሳሪዎቹ በጥፊ፣ በእርግጫ እንዲሁም በብትር እና በሰደፍ በተደጋጋሚ እንደተመቱ ለሂዩማን ራይትስ ዎች ገልጸዋል፡፡ እስረኞቹ ሰውነታቸውን ለህመም በሚዳርግ ሁኔታ እንዲሆኑና በተለይም እጆቻቸውን ከግድግዳ ጋር ታስረው እንዲንጠለጠሉ ተደርጎ ለረጅም ሰዓታት ያለማቋረጥ እንደሚደበደቡ ተናግረዋል። ከኦሮሚያ ክልል የመጣ አንድ ተማሪ ብቻውን ተነጥሎና በሰንሰለት ታስሮ ለበርካታ ወራት እንዲቆይ እንደተደረገ ተናግሯል፡፡ “ለመቆም ስሞክር እቸገራለሁ፡ ለመቆም ጭንቅላቴን፣ እግሮቼን እና ግድግዳውን መጠቀም ነበረብኝ ፡፡ ምግብ ስመገብ እንኳ በሰንሰለት ታስሬ ነበር። ስመገብ እጆቼ በፊት ለፊት በኩል እንዲታሰሩ ይደረጋል ስጨርስ ደግሞ መልሰው ወደ ኋላ ያስሩኛል።”
በማዕከላዊ በሚገኙት አራቱ ዋና የማሰሪያ ብሎኮች ያለው ሁኔታ አስከፊ ነው። ሆኖም በየብሎኩ ያለው ሁኔታ በከፍተኛ ደረጃ ይለያያል፡፡ ‘ጨለማ ቤት’ በመባል በሚታወቀው በጣም የከፋ ብሎክ የቀን ብርሃን እና የመፀዳጃ አገልግሎት ማግኘት በእጅጉ የተገደበ መሆኑን የቀድሞ ታሳሪዎች የገለጹ ሲሆን ‘ጣውላ ቤት’ በሚባለው ብሎክ የታሰሩት ደግሞ ወደ ደጃፍ ለመውጣት ያለውን ገደብ እና የክፍሎቹን በተባይ መወረር ገለጸዋል። እስረኞቹ ለመርማሪዎቹ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት በሚያደርጉት ትብብር መሰረት በቅጣት ወይም በማበረታቻ መልኩ መሰረታዊ ፍላጎቶቻቸውንና ሌሎች የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ሊከለከሉ ወይም ሊፈቀዱላቸው ይችላል፡፡ ይህም ታሳሪዎቹን ከአንዱ ብሎክ ወደ ሌላ ማዘዋወርን ይጨምራል፡፡ ከዓለማቀፉ ሆቴል ስያሜውን ወዳገኘው እና ‘ሸራተን’ በመባል ወደሚታወቀው ብሎክ መዛወር የተሻለ የመንቀሳቀስ እድል ስለሚያስገኝ ከመፈታት ቀጥሎ እስረኞች እጅግ የሚናፍቁት ነገር ነው።
በጨለማ ቤት እና በጣውላ ቤት የሚታሰሩ እስረኞች በተለይ በመጀመሪያዎቹ የእስር ወቅቶች የህግ ጠበቃ እና ዘመዶቻቸውን እንዲያገኙ አይፈቀድላቸውም፡፡ የታሰሩ ዘመዶቻቸውን ለመጠየቅ በየቀኑ ወደ ማዕከላዊ ቢሄዱም ምርመራው እስኪያልቅ በሚል ለተራዘመ ጊዜ ከእስረኞቹ ጋር ለመገናኘት ሃላፊዎቹ እንደማይቅዱላቸው በርካታ የቤተሰብ አባላት ለሂዩማን ራይትስ ዎች ገልፀዋል፡፡ በምርመራ ወቅት የህግ ጠበቃ አለመኖሩ ታሳሪዎቹ ላይ የሚፈፀመውን በደል እንዲጨምር ያደርጋል፣ በመርማሪዎቹ የሚፈጸሙ ጎጂ አያያዞችና ማሰቃየትን የሚመለከቱ መረጃዎች እንዳይመዘገቡ ያደርጋል፤ እንዲሁም ፍርድ ቤት ይህ ያልተገባ አያያዝ እንዲሻሻል መፍትሔ ሊሰጥ የሚችልበትን እድል ይገድባል ሲል ሂዩማን ራይትስ ዎች ገልጿል።
“እስረኞች ከጠበቆቻቸው እና ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዳይገናኙ ማድረግ በደል ሊፈጸም የሚችልበትን ዕድል ከመጨመሩም በላይ እስረኞች የመርማሪዎቹን ፍላጎት በሚያሟላ መልኩ ብቻ እንዲሄዱ ከፍተኛ ጫና ይፈጥርባቸዋል” ያሉት ሌፍኮ “በማዕከላዊ የሚገኙ እስረኞች በምርመራ ወቅት ጠበቆቻቸው እንዲገኙላቸው፣ከዘመዶቻቸው ጋር እንዲገናኙ እንዲሁም በፍጥነት ክስ ተመስርቶ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ መደረግ ይኖርበታል” ብለዋል።
መርማሪዎች ድብደባ፣ ማስፈራራትና ሃይል በመጠቀም እስረኞች የሰጡት የእምነት ቃል ላይ እንዲፈርሙ እንደሚያደርጓቸው ሂዩማን ራይትስ ዎች መረዳት ችሏል፡፡ አንዳንድ ጊዜ የፈረሟቸውን ጽሁፎች እንደማስፈራሪያነት በመጠቀም ከተፈቱ በኋላ ከመንግስት ጋር እንዲሰሩ ጫና ለመፍጠር የሚያውሏቸው ሲሆን በፍርድ ቤት ማስረጃ ሆነውም እንዲቀርቡ ይደረጋል፡፡
በ2004ዓ.ም በማዕከላዊ ታስሮ የነበረው ስዊድናዊ ጋዜጠኛ ማርቲን ሽብዬ ታሳሪዎች የእምነት ቃል እንዲሰጡ ለማድረግ ስለሚደረገው ጫና ሲናገር “አብዛኞቹን ማዕከላዊ የሚገኙ ሰዎች ተስፋ ቆርጠው የእምነት ቃል እስኪሰጡ ድረስ ያቆዩአቸዋል። ቃለመጠይቅ ሳይደረግልህ ለሶስት ሳምንታት ልትቆይ ትችላለህ። የእምነት ቃል እስኪገኝ ድረስ ብቻ ነው የሚጠብቁት።ሁሉ ነገር የእምነት ቃል ማግኘት ላይ ብቻ የሚያጠነጥን ነው።ፖሊስ ጉዳዩ ፍርድ ቤት ሲቀርብ መላ ያገኛል ይላል ነገርግን ፍርድ ቤት ሲኬድ አንድም የሚገኝ ነገር የለም” ብሏል፡፡
ሂዩማን ራይትስ ዎች እንዳለው ታሳሪዎች ለተፈጸመባቸው ጎጂ አያያዝ መፍትሔ ሊያገኙ የሚችሉባቸው መንገዶች ውሱን ናቸው። በተለይ ፖለቲካ ነክ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች ገለልተኝነት አይንጸባረቅባቸውም፡፡ በጸረ-ሽብርተኝነት ህጉ መሰረት የተያዙ ሰዎችን ጨምሮ እስረኞች ስለሚፈጸምባቸው ጥቃት በርካታ ቅሬታ ቢያቀርቡም ቅሬታዎቹ አንዲመረመሩ ወይም ቅሬታ ያቀረቡ እስረኞች የበቀል ጥቃት እንዳይፈጸምባቸው ክትትል እንዲደረግ ፍርድ ቤቶች የወሰዱት በቂ እርምጃ የለም፡፡
ያልተገባ አያያዝን በተመለከተ ለሚቀርቡ ቅሬታዎች ፍርድ ቤቶች በንቃት ምላሽ መስጠት አለባቸው። ይህም ሊሆን የሚችለው መንግስት በነፃነት እንዲሰሩ ሲፈቅድ እና የሚሰጧቸውን ውሳኔዎች ሲያከብር ብቻ ነው። ሲል ሂዩማን ራይትስ ዎች ገልጿል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ኢትዮጵያ በነፃ አካላት የሚደረግን የሰብአዊ መብቶች ምርመራ እና ሪፖርት የማድረግ ሥራ በእጅጉ ገድባለች። ይህም በማዕከላዊ ያለው የእስር ሁኔታ ክትትል እንዳይደረግበት አድርጓል። መንግስታዊው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ ማዕከላዊን ሶስት ጊዜ የጎበኘ ሲሆን ከሰዎች ጋር ግንኙነት እንዳይኖራቸው ተነጥለው የሚታሰሩ ሰዎችን አስመልክቶ ያለውን ስጋት በይፋ አስታውቋል፡፡ ይሁንና የቀድሞ እስረኞች ለሂዩማን ራይትስ ዎች እንደገለጹት በጉብኝቱ ወቅት የማዕከላዊ ሃላፊዎች ከኮሚሽኑ ከመጡት ጎብኚዎች ጋር ስለነበሩ የኮሚሽኑን አባላት በግል ለማነጋገር ሳይችሉ ቀርተዋል። ጉብኝቱን ተከትሎ የመጣ ለውጥ ስለመኖሩም እርግጠኞች አይደሉም፡፡
ሂዩማን ራይትስ ዎች እንደሚለው በማዕከላዊ እና በሌሎች ማሰሪያ ቦታዎች የሚደረገው የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ ክትትል እንዲሻሻል የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ማህበራት አዋጅ እና የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ የተሰኙት ሁለት አፋኝ ህጎች መሻሻል አለባቸው፡፡ በሁለቱ ህጎች ምክንያት ገለልተኛ የሰብዓዊ መብቶች ክትትል ሥራ በእጅጉ ቀንሷል እንዲሁም ማሰቃየት እና ጎጂ አያያዝን ለመከላከል የሚያስችሉ መሠረታዊ የሕግ ጥበቃዎች ተሰርዘዋል።
የኢትዮጵያ ህገ መንግስት እና ሀገሪቱ የገባችባቸው ዓለማቀፍ ግዴታዎች ባለስልጣናት በእስረኞች ላይ ያልተገባ አያያዝ እንዳይፈጸም እንዲከላከሉ የሚያስገድዱ ሲሆን በሁሉም ደረጃ የሚገኙ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት በደል የመፈጸም አሰራሮችን የማስቆም እና ፈጻሚዎችም በሕግ እንዲጠየቁ የማድረግ ሃላፊነት አለባቸው ብሏል ሂዩማን ራይትስ ዎች፡፡ መንግስት የነደፈው የሦስት ዓመታት የሰብአዊ መብቶች የድርጊት መርሀ ግብር የታሳሪዎች አያያዝ መሻሻል ያለበት መሆኑን የሚገልጽ ቢሆንም መርሃ ግብሩ በአካል ላይ የሚፈጸም ጥቃትን እና ማሰቃየትን አይዳስስም። በስፋት የሚፈፀመውን በደል ለማስቆም መወሰድ ያለበትን ተጨባጭ ፖለቲካዊ እርምጃ ከመግለጽ ይልቅ የአቅም ግንባታ ጉዳዮች ላይ ያተኩራል።
“ተጨማሪ ገንዘብ እና የአቅም ግንባታ ስራ ብቻውን በማዕከላዊ እና በሌሎች የኢትዮጵያ ማሰሪያ ቦታዎች በስፋት የሚፈጸመውን ያልተገባ አያያዝ አያስቆምም” ያሉት ሌፍኮ “እውነተኛ ለውጥ የሚመጣው በደሎቹን የሚፈጽሙት ሰዎች ላይ የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት እርምጃ ሲወስዱ እና ጥፋተኞች ተጠያቂ እንዳይሆኑ የሚያደርገው የአሰራር ባሕል እንዲወገድ ሲያደርጉ ነው።” ብለዋል
ECADFOREM

No comments:

Post a Comment