Tuesday, October 29, 2013

ዋሊያዎቹ ለወሳኙ የናይጄሪያው የመልስ ጨዋታ ልምምዳቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል


- ጌታነህ ከበደ በቀጣዩ ወሳኝ ጨዋታ ሊሰለፍ ይችላል

- “በቡድኑ ውስጥ የማሸነፍ መንፈስ አለ” – ደጉ

ከቦጋለ አበበ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋልያዎቹ በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ባለፈው ጥቅምት ሦስት በሜዳቸው ሽንፈት ከደረሰባቸው በኋላ ቀጣዩን ጨዋታ በድል ለመወጣት ዝግጅታቸውን ጀምረዋል። ከሳምንት በፊት ልምምዳቸውን የጀመሩት ዋልያዎቹ በቀጣዩ ጨዋታ በሜዳቸው የገጠማቸውን ሽንፈት ለመቀልበስ ያስችላቸው ዘንድ ጠንካራ ልምምድ እየሠሩ ይገኛሉ።

ባለፈው ቅዳሜ ወደ አዲስ አበባ ስታዲየም አቅንተን ከሃያ የሚበልጡ ተጫዋቾች ጠንካራ ሊባል የሚችል ልምምድ ሲያደርጉ ተመልክተናል። አብዛኛውን የልምምድ ጊዜ የትንፋሽና ኳስን መሰረት ያደረገ ፈጣን ሊባል የሚችል እንቅስቃሴ ሲሠሩ የነበሩት ዋልያዎቹ በልምምድ ወቅት የሚታይባቸው ጥንካሬ ቀጣዩን ጨዋታ በድል ለመወጣት እንደቆረጡ የሚያመላክት ነው።
በልምምዱ ወቅት የእያንዳንዱ ተጫዋች እንቅስቃሴና የቡድን አንድነት ዋልያዎቹ ከሽንፈታቸው በኋላም ቀድሞ የነበረው የአሸናፊነት መንፈስና ጥንካሬ እንዳልተሸረሸረ ያሳያል። ከጥቅምት ሦስቱ ጨዋታ በፊት ዋልያዎቹ ልምምድ ሲሰሩ ትልቅ የራስ መተማመን ስሜት ይነበብባቸው ነበር። ከጨዋታው በኋላ እያደረጉት ባለው ልምምድም ሙሉ የዋልያዎቹ አባላት ጋር ቀድሞ የነበረው በራስ መተማመን ስሜት አልተለየም።
በቤልጂየሙ ሊርስ ክለብ እየተጫወተ የሚገኘው የዋልያዎቹ የቁርጥ ቀን ልጅ ሳላዲን ሰዒድ፣ በደቡብ አፍሪካው ቢድቪት ዊትዝ ክለብ እየተጫወተ የሚገኘው የዋልያዎቹ ፊት አውራሪ ጌታነህ ከበደ፣ በሊቢያው አልሂታድ ክለብ እየተጫወተ የሚገኘው የጨዋታ አቀጣጣይ ሽመልስ በቀለ እንዲሁም አማካዩና በሱዳኑ ክለብ አል አህሊ ሸንዴ እየተጫወተ የሚገኘው አዲስ ህንፃ ወደየ ክለባቸው በመሄዳቸው ከዋልያዎቹ ጋር በልምምድ ሜዳ ላይ አልተገኙም፡፡
እነዚህ የዋልያዎቹ ቀዳሚ ተመራጭ ተጫዋቾች ከሁለት ሳምንት በኋላ ከሜዳቸው ውጪ ናይጄሪያን ለመግጠም በሚደረገው ፍልሚያ ለመካፈል ቡድናቸውን ከሳምንት በኋላ ተቀላቅለው ልምምድ እንደሚጀምሩ ይጠበቃል።
በሌላ በኩል በአገር ውስጥ ሊጎች እየተጫወቱ የሚገኙት የዋልያዎቹ አባላት ከቡድናቸው ጋር ጠንካራውን ልምምድ አብረው እየሠሩ ይገኛሉ። ግብ ጠባቂዎቹ ጀማል ጣሰውና ሲያይ ባንጫ እንዲሁም ተጠባባቂዎቹ ሁለት ግብ ጠባቂዎች ከቡድኑ ጋር ልምምዳቸውን እየሠሩ ይገኛሉ።
ወሳኞቹ የቡድኑ አባላት አዳነ ግርማ፣ አምበሉ ደጉ ደበበ፣ አይናለም ኃይሉ፣ በኃይሉ አሰፋ፣ ብርሃኑ ቦጋለና ሌሎችም ጠንካራ ተጫዋቾች በቅዳሜው ልምምድ ላይ ነበሩ። ይሁን እንጂ ወሳኙ የአማካይ ስፍራ ተጫዋች ምንያህል ተሾመ ባጋጠመው የጡንቻ መሸማቀቅ ምክንያት በቅዳሜው ልምምድ ላይ አልተካፈለም፡፡ የዋልያዎቹ ምክትል አሠልጣኝ ታረቀኝ አሰፋን በጉዳዩ ላይ አነጋግረናቸውም ምንያህል ያጋጠመው መጠነኛ ጉዳት በመሆኑ ሰሞኑን ልምምድ እንደሚጀምር ነግረውናል።
ከቦትስዋናና ከደቡብ አፍሪካ ጋር በነበረው ጨዋታ ወሳኝ ሦስት ግቦችን ከመረብ ያሳረፈው ጌታነህ ከበደ በጉዳት ምክንያት ከናይጄሪያ ጋር በነበረው ጨዋታ አለመሰለፉ ይታወሳል።ይሁን እንጂ ጌታነህ በሚጫወትበት የደቡብ አፍሪካው ክለብ ከጉዳቱ አገግሞ በቅርቡ ልምምድ እንደሚጀምር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ምክትል አሠልጣኝ ታረቀኝ አሰፋ ነግረውናል።
ምክትል አሠልጣኙ ቡድኑ በሜዳው ከደረሰበት ሽንፈት በኋላ ወደ ቀድሞ የአሸናፊነት መንፈሱ ተመልሶ ቀጣዩን ጨዋታ ለማሸነፍ ቆርጦ መነሳቱን ይናገራሉ። ሁሉም ተጫዋቾች በሙሉ ጤንነት ላይ የሚገኙ ሲሆን፤ ቀጣዩን ጨዋታ ለማሸነፍ ያላቸው ተነሳሽነትም ከፍተኛ እንደሆነ ምክትል አሠልጣኙ ያስረዳሉ።
ምክትል አሠልጣኝ ታረቀኝ ዋልያዎቹ ቀጣዩን ጨዋታ አሸንፈው ወደ ብራዚሉ የዓለም ዋንጫ ለማለፍ ያላቸው ጉጉት አሁንም እንዳልቀነሰ ያብራራሉ። ጨዋታውን አሸንፈው ካሰቡበት ለመድረስም አስፈላጊውን ሁሉ ዝግጅት እያከናወኑ ነው።
አብዛኞቹ ተጫዋቾች ከልምምድ በኋላ ከፍተኛ የድካም ስሜት ይነበብባቸው ስለነበረ ቀርበን ለማነጋገር የቻልነው የተወሰኑትን ተጫዋቾች ብቻ ነው፡፡ አምበሉ ደጉ ደበበ አስተያየቱን የሰጠን የመጀመሪያው ተጫዋች ሲሆን፤ ቡድኑ በመልካም የአሸናፊነት ሥነ ልቦና ላይ እንዳለ ነግሮናል። ደጉ ቀጣዩን ጨዋታ ለማሸነፍ ሁሉም የዋልያዎቹ አባላት የማይከፍሉት መስዋዕትነት እንደማይኖርም ተናግሯል።
የቡድኑ የመጀመሪያ ተመራጭ ግብ ጠባቂ ጀማል ጣሰው በሰጠን አስተያየትም በሜዳቸው የገጠማቸውን ሽንፈት ለመቀልበስ ዋልያዎቹ አሁንም ተስፋ አልቆረጡም ብሏል። ጀማል አሁን እያከናወኑት ያለውን ጠንካራ ልምምድ እስከ ጨዋታው ድረስ በማጠናከርም ከሜዳቸው ውጪ አሸንፈው ለመምጣት እንደሚሠሩ ገልጿል።
zehabesha

No comments:

Post a Comment