Wednesday, October 30, 2013

“ትግራይ ከአንድ ፋብሪካ እንደወጣ ሳሙና”


 ዛሬ አንድ ታሪክ ያስታወሰኝ አስተያየት አነበብኩ። በ97 ምርጫ ቅስቀሳ ወቅት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪ ነበርኩ። በኢህአዴጎችና ቅንጅቶች መካከል የነበረ ክርክር እከታተል ነበር። የማናቸው ደጋፊ ወይ ተቃዋሚ አልነበርኩም። አንድ ሲኔራችን ነበር። ሁሌ ወደ ዶርማችን እየመጣ ስለነዚህ የቅንጅት መሪዎች መጥፎ ታሪክ ይነግረናል፤ ለትግራይ ህዝብ መጥፎ አመለካከት እንዳላቸው (እንዲህ አደረጉ፣ እንዲህ አሉ እያለ)፣ የደርግ ከፍተኛ ባለስልጣናት የነበሩና ወንጀለኞች መሆናቸው ወዘተ።

በተደጋጋሚ ሲተርክልን የልጁ ዓላማ ግራ ገባኝና “እስቲ ይሄ ተናገሩት ወይ አደረጉት የምትለውን አምጣውና አሳየኝ” አልኩት። “እሺ አሳየሀለሁ” ብሎ በዛው ጠፋ (ቢያንስ ወደ ዶርማችን እየመጣ አይዋሽም)። ከተወሰኑ ቀናት በኋላ “ይሄ አብርሃ የሚሉት ተከታተሉት፣ ቅንጅት ይመስለኛል” ብሎ ለሌሎች ተማሪዎች (የህወሓት አባላት) እንደተናገረ ሰማሁ። ተጠራጠርኩት። ለካ ልጁ የህወሓት ሰላይ ነበር።
የህወሓት ሰላዮች (ሦስተኛ ደረጃ ሰላዮቹ) ያልሆነ ወሬ ሆን ብለው ለህዝብ ይበትናሉ። የተቃዋሚ መሪዎች ያልተናገሩት ነገር ።። “እንዲህ ተናገሩ” እያሉ አሉባልታቸው ይነዛሉ፤ የፖለቲከኞች ስም ለማጥፋትና በህዝብ እንዲጠሉ ለማድረግ። በ97ቱ ምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም “ፀረ ትግራይ ህዝብ” አስተያየት እንደሚሰጡ በካድሬዎች ይነገረን ነበር። እኔ እንኳ ልምድ ስላገኘሁ ካድሬዎቹ የሚናገሩት አላምናቸውም።
“ፕሮፌሰር መስፍን መቐለ መጥተው ‘የትግራይ ህዝብ ከአንድ ፋብሪካ እንደወጣ ሳሙና ነው’ ብለው ሰደቡን” እያሉ የተሳሳተውን መረጃ በሰፊው ለህዝብ ተበተነ። ከምርጫው በኋላ ፕሮፌሰር መስፍን በትክክል የተናገሩትን ነገር እንዲነግረኝ ለአንድ ካድሬ ጓደኛዬ ጠየኩት። መጀመርያ ህወሓቶች ተዘጋጅተው፣ ተደራጅተው ቅንጅቶች የጠሩትን ስብሰባ ለመረበሽ ገቡ (የነገረኝ ካድሬ ከረብሻው አዘጋጆች አንዱ ነበር)። ስብሰባው ተረበሸ (ልጁ “ቅንጅቶች ሰራንላቸው” አለኝ)።
በተደራጀ መልኩ ስብሰባ መረበሽ የህወሓቶች ስትራተጂ መሆኑ በደንብ አውቃለሁ። ምክንያቱም በነ ገብሩና አረጋሽም በ2002 ምርጫ ቅስቀሳ ቅንብሩ ተስርቷል። “ፕሮፌሰሩ ምን ነበር ያሉት?” ብዬ ደግሜ ጠየኩት። “ቃል በቃል አላስታውሰውም ግን ‘የትግራይ ህዝብ ከአንድ ፋብሪካ እንደወጣ ሳሙና አንድ ሊሆን አይችልም’ የሚል መልእክት ነበረው” አለኝ። “ታድያ ለምን የትግራይን ህዝብ ተሳደቡ አላቹ?” ጠየኩት። “ፖለቲካ ነዋ፣ ሽማግሌው ግን ሰራንለት! የት አባቱ!” ጨመረ።
ህወሓቶች ያልተባለውን መጠምዘዝ ይወዳሉ። ባለፈው ቅዳሜ ከዉቅሮ ህዝብ ሲንነጋገር “ወላጆቻችን የታገሉለት ዓላማ በህወሓት መሪዎች ተጠልፎ ለስልጣን ሆነዋል። ወላጆቻችን መስዋእት የከፈሉት ለስልጣን ሳይሆን ለነፃነት ነው። ህወሓቶች በሰማእታት ስም እየነገዱ ነው። (ወለድና ንነፃነት እምበር ንስልጣን አይተቃለሱን። ሕድሪ ሰማእታትና ተጨውዩ እዩ። ቃልሲ ህዝቢ ትግራይ ዒላምኡ ንክወቅዕ መንእሰይ ትግራይ ንዴሞክራሲ ክቃለስ አለዎ)።” የሚል መልእክት ያለው አስተያየት ሰጠን። ህወሓቶችም “ዓረናዎች ሰማእታትና ሲያንቋሽሹ ዋሉ፤ እንከሳቸዋለን!” እያሉ በስፒከር ለህዝብ ሲያውጁ አመሹ። ሊከሱን አይችሉም። ምክንያቱም እንደዛ አላልንም። ይህ የሚረዳው በአደራሹ የነበረ ህዝብ ብቻ ነው። የነሱን ብቻ የሚሰማ ሰው ግን በመረጃው ለግዜው ሊደናገር ይችላል።
እናም ስም ማጥፋት ስራቸው ነው። ፕሮፌሰር መስፍን “የትግራይ ህዝብ ከአንድ ፋብሪካ እንደወጣ ሳሙና አንድ ሊሆን አይችልም” ስላሉ ምንድነው ችግሩ? “ለትግራይ ህዝብ ‘ሳሙና’ ብለው ሰደቡት” ያስብላል??? እኛም (ለምሳሌ እኔ) የትግራይ ህዝብና ህወሓት አንድ አይደሉም፤ ህዝብ አንድ ዓይነት አመለካከት ወይ አስተሳሰብ ሊኖረው አይችልም … እያልን ኮ ነው። ይህ ደግሞ ትክክል ነው።
ህወሓቶች ግን የትግራይ ህዝብ በሙሉ የትግራይ አሽከር እንደሆነ ያስባሉ። ይህ ንቀት ነው። እያንዳንዱ የትግራይ ዜጋ የራሱ እምነትና አመለካከት አለው። ምናልባት ፕሮፌሰር መስፍን የተናገሩት የህወሓት ሰላዮች እንደሚነግሩን “የትግራይ ህዝብ ከአንድ ፋብሪካ የወጣ ሳሙና ነው” የሚል ከሆነ ፕሮፌሰሩ ከህወሓቶች ጋር ተመሳሳይ አረዳድ አላቸው ማለት ነው። ህወሓቶችም’ኮ “በመለስ መሬት ዃዂቶ (አቃቅማ) አይበቅልም” ሲሉን “ሁሉም የትግራይ ሰው እንደ የአንድ ፋብሪካ ሳሙና አንድ ዓይነት አመለካከት ሊኖረው ይገባል” እያሉን ነው። ስለዚህ ህወሓቶች ራሳቸው ለሚናገሩትና ለሚያደርጉት ነገር በፕሮፌሰር ስለተነገረ ብቻ እንደ ስድብ መቁጠር ያስተዛዝባል።
ህወሓት ትውልድን እየገደለ ያለ ይመስለኛል። እንዴት ነው ትውልድ የሚገደለው? ትውልድ አስተሳሰብ ነው። የአንድን ትውልድ አስተሳሰብ ከተገደለ ትውልዱ ተገደለ ማለት ነው። አስተሳሰብ እንዴት ይገደላል? ወጣቶች የራሳቸው ፖለቲካዊ (ይሁን ሌላ) አመለካከት፣ አረዳድ፣ አስተሳሰብ እንዳይኖራቸው፣ እንዳያራምዱ ከተከለከሉ አስተሳሰባቸው ተገደለ ማለት ነው። አስተሳሰናቸው ከተገደለ ትውልዱ ተገደለ ማለት ነው።
ትውልድን ላለመግደል ወጣቶች (አዲሱ ትውልድ) በራሱ መንገድ፣ የራሱን አስተሳሰብና ራእይ ሰንቆ መጓዝ አለበት። የፈለገውን አስተሳሰብ የመከተል ነፃነት ሊኖረው ይገባል። ነፃነቱ ከሌለው አስተሳሰቡ አይኖርም። አስተሳሰቡ ከሌለ ለውጡ፣ እድገቱ አይኖርም። ለውጡ ካልመጣ የተፈለገውን ልማት አይኖርም። ልማት ማምጣት ያልቻለ ትውልድ የተበደለ ነው። ስለዚህ ህወሓት ስልጣንን ላለመልቀቅ ሲል ትውልድን መግደል የለበትም።
ስለ ፕሮፌሰር መስፍንና ዶ/ር መረራ ጉዲና በትግራይ ብዙ ስም የማጥፋት ዘመቻ ተከፍቶ ነበር። አሁን እኔ ስለ ፕሮፌሰር መስፍን በመፃፌ ብቻ “አብርሃ ፀረ ትግራይ ህዝብ ስለሆነው ፕሮፌሰር መስፍን ጥሩ ነገር ይፅፋል። ከነሱ ጋር በማበር የትግራይን ህዝብ ለመጨፍጨፍ ጥረት ያደርጋል” ብለው የተለመደውን ወሬ መበተናቸው አይቀርም። ስራቸው ስለሆነ ችግር የለውም።
ስለ ዶ/ር መረራም “ደርጋውያን ጠላቶቻችን …” እየተባለ ይሰበካል። ባለፈው የዉቅሮ ስብሰባችን ሳይቀር “ዓረና ከደርግ ጠላቶቻችን እነ ዶ/ር መረራ ጋር አብሮ እየሰራ ትግራይን ለመጨቆን ተነስቷል” እያሉ ህዝብን ያደናግሩ ነበር። ግን’ኮ የአንድ ሰው ስብእናና ፖለቲካዊ አቋም መገምገም ያለብን በድሮ ህይወቱ ሳይሆን ባሁኑ አመለካከቱ ነው። ለመረጃ እንዲሆነን ግን ዶ/ር መረራ ደርግ አልነበረም። የመኢሶን አባል ነበር። በደርግ ግዜ እኛ የትግራይ ተወላጆች ከደረሰን ግፍ ባልተናነሰ ዶ/ር መረራም ብዙ ግፍና እንግልት የደረሰበት ሰው ነው።
ሁሉም የደርግ ባለስልጣናት ወንጀሎኞች ናቸው ማለት አይቻልም (ሁሉም የህወሓት ባለስልጣናት ጨቋኞች ናቸው ማለት እንደማይቻል ሁሉ)። ግን የደርግ ስርዓት ወንጀለኛ ነው፤ የህወሓት ስርዓትም ጨቋኝ ነው። እንዲህ ሁኖ የደርግ ባለስልጣናት አሁን ስልጣን መያዝ አልነበረባቸውም ብዬ ባልልም ደርግ የትግራይን ህዝብ ጠላት ነበር ካልን የደርግ ኢሠፓ አባል የነበረ ፖለቲከኛ ዶ/ር መረራ ሳይሆን በህወሓት/ኢህአዴግ ዉስጥ ያሉ እነ አቶ ገብረዋህድ (በሙስና የታሰረው)፣ አባዱላ ገመዳ፣ ኩማ ደመቅሳ … ወዘተ ናቸው።
ህወሓት የአራት ኪሎ ቤተመንግስት ሲቆጣጠር ከኦነግ ጋር ለመስራት ፈልጎ ነበር። ግን ኦነግ የህወሓት አሻንጉሊት ሁኖ የሚያገለግል መስሎ አልታየም። እንደውጤቱም ህወሓት ኦነግን አባሮ የደርግ ወታደሮች (በጦርነት የተማረኩ) አሰባስቦ ኦህዴድን መሰረተ። ስለዚህ ደርጎች የት ናቸው ያሉት? ብለን ሳናጣራ ንፁሓን ሰዎችን መንካት ተገቢ አይደለም። በደርግ ግዜ በሓላፊነት የነበረ፣ የተመዘገበና የሚያስጠይቅ ወንጀል ከሌለው፣ አቋሙ ካስተካከለ ሓላፊነት ቢሰጠው ችግር የለብኝም።
የማልደግፈው ነገር ቢኖር የደርግ ኢሠፓ አባል የነበረ፣ በሕግ የሚያስጠይቅ ወንጀል ሳይኖረው በሀገሩ በሰላም እየኖረ የነበረ ሰው ፖለቲከኛ ሲሆን (ወደ ተቃዋሚ ድርጅቶች ከገባ በኋላ) የደርግ አባል እንደነበርና የትግራይ ህዝብ ጠላት ነው ተብሎ ይነገረናል። አንድ ሰው የደርግ ይሁን የህወሓት ወንጀል ካለው በሕግ ይጠየቅ፣ አለበለዝያ ግን በፖለቲካ የመሳተፍ መብቱ ሊከበርለት ይገባል። ፖለቲከኛ ስለሆነ የባልፈው ታሪኩ እየመዘዝን የማጥላላት ዘመቻ የምንከፍትበት ከሆነ ግን ችግር ነው።
ህዝብ ትክክለኛ መረጃ የማግኘት መብት አለው። የህወሓት ሰላዮችም የተዛባ መረጃ ከመስጠት ታቀቡ። ሁሉም በግዜው ይጋለጣልና።

No comments:

Post a Comment