Monday, October 7, 2013

ታማኝ እና ቴዲ ትላንት ምሽት



ክንፉ አሰፋ
home2ትላንት ምሽት። እለተ እሁድ፤ ኦክቶበር 6፣ 2013። ታማኝ በየነ እና ቴዲ አፍሮ በስልክ ያወራሉ። ንግግራቸው
ከወትሮው የተለየ አልነበረም። እንደቀድሞው እየተቀላለዱ ይሳሳቃሉ። ታማኝ ከዴንቨር-ኮሎራዶ፣ ቴዲ ደግሞ ከሲድኒ-
አውስትራሊያ በስራ ላይ ነበሩ። በዚህ የሶስትዮሽ የስልክ ጨዋታ ላይ እኔና ጴጥሮስ አሸናፊም ገብተናል።
 ያን ሰሞን በኢትዮጵያ ድረ-ገጾች፣  በተለይ ደግሞ በፌስቡክ እና ሌሎች ማህበራዊ መድረኮች ላይ የውይይት ርእስ
ሆኖ ሰነበተ። የታማኝ እና የቴዲ ጉዳይ። በዚህ ዙርያ የነበረው ውይይት በወዳጆቻቸው ዘንድ
በጥቂቱም ቢሆን ግርታ
መፍጠሩ አልቀረም።  አንዳንዶች ለሁለቱም የጥበብ ሰዎች ካላቸው ፍቅርና አድናቆት ሲወያዩ ሰነበቱ። ሌሎች ደግሞ
ክስተቱን ወደ ሌላ አቅጣጫ ለመቀየር ሞከሩ። ጉዳዩ በእጅጉ አሳስቧቸው  ለነገሩ እልባት ለመስጠት እንቅልፍ ያጡም ነበሩ።
 የትናንት ምሽቱ ውይይት ግርታውን እንደበረዶ አጠራው። በሁለቱ የጥበብ ሰዎች ዙሪያ ለሚነሳው ጥያቄዎ ምላሽ
ሰጠ። እናም ምንም አዲስ ነገር የለም እላችኋለሁ። ሁለቱም እንደድሯቸው ያወራሉ፣ ይቀላለዳሉ፣ ይሳሳቃሉ።  
 ቴዲ በእርግጥም ቅን ነው።  ታማኝም እንዲሁ። ሳያውቅ ለሚያጠፋው ጥፋት ይቅርታ ለማለት አይከብደውም።
ወረድ ብሎ፣ ዝቅ ብሎ፤ ታናሽ ወንድሙን  ይቅርታ የሚጠይቅ ትልቅ ሰው ነው። ነገሩ እዚያም አልደረሰ። ልብ ለልብ
የሚተዋወቁ የዘመኑ ልጆች ነገሮችን አያካብዱም።
 ለምስክርነት ብጠራ እንዲህ እላለሁ። በእልህ ሳይሆን በፍቅር የሚያሸንፉ ምርጥ የኢትዮጵያ ልጆች፤ ሁለት ባለ
ራእዮች። ትውልድ አልፈው አንድን ህብረተሰብ የመለወጥ ትእንግርታዊ ስጦታ ያላቸው የዘመናችን እንቁዎች።...
 ታማኝ በየነ  ለኢሳት ድጋፍ ለማሰባሰብ እስራኤል ሃገር ሄዶ ሲናገር “አምላኬ ሰው ስጠኝ በልኬ” የሚለውን የቴዲ
አፍሮ ስራ አንስቶ አንድ-ሁለት ማለቱ ነበር ውይይቱን የጫረው።  በዚህ ጉዳይ ከታማኝ ጋር ብዙ አውርተናል። ታማኝ
ለማለት የፈለገው እና ሰዎች ለአባባሉ የሰጡት ትርጓሜ ግርግሩን እንደፈጠረው ለመረዳት ብዙ ጊዜ አልወሰደብኝም። ታማኝ
ቃል በቃል እንዲህ አለኝ። ቴዲን በቁመናው ለመተቸት ለመሆኑ እኔ ማን ነኝ?
 ለዚህ ትውልድ የተተወለት እርሾ እንዲህ አይነቱ የፍቅር እና የይቅርታ መንፈስ አልነበረም። ከዚያኛው ትውልድ
በጥበብና በፍቅር መኖርን አልወረስንም። በሃይል እና በእልህ ለማሸነፍ እንጥራለን።  እናም አሸናፊዎች ሳይሆን ተሸናፊዎች
ሆነን ቀረን።  
 መልካም ነገር ከታማኝ እና ከቴዲ ተማርኩ። ቅንነትና ራስን ዝቅ ማድረግ። በእርግጥ ሁለቱ በችግር እና በደስታ
ጊዜ ብዙ ነገሮችን ያሳለፉ የልብ ወዳጆች ናቸው። አንዱ ሌላውን ጠንቅቆ ያውቀዋል።
 "ፍቅር ያሸንፋል ከማለት በላይ የሚሆን ገላጭ ቃል የለኝም።" አለ ቴዲ በስልኩ  ውይይት። ንግግሩ ልብ
ይሰብራል። አጥንት ሰርስሮም ይገባል።
 "ስህተት እንኳን ቢሆን አዲስ ነገር አይደለም። ሁላችንም እንሳሳታለን። ነገሮችን ማየት ያለብን ከዚያ አልፈን
ነው።" ቴዲ ጨመረበት።
 ታላቁ መጽሃፍ እንዲህ ይለናል። ፈጣሪ ንጉስ ሰለሞን ጠርቶ ምን ልስጥህ ሲል ጠየቀው። ንጉስ ሰለሞንም
"አምላኬ ሆይ ጥበብ እና ማስተዋልን ስጠኝ።" አለው። ጠቢቡ ሰለሞን ሃብትና ንብረትን አልጠየቀም፣ ሃይልና ጉልበትንም
አልተመኘም። እንዲህም ሆነ። እግዚአብሄር ለሰለሞን ማስተዋልና ጥበብን ሰጠው። ንጉስ ሰለሞንንም ሃያል ሆነ። በጥበብ!
 በጥበብና በፍቅር ህብረተሰብን መቀየር እንደሚቻል አስተዋልኩ። ይህ ደግሞ የሁለቱ የጥበብ ሰዎች የጋራ መድረሻ
ነው።  እዚያ ላይ ለመድረስ የሚያስፈልገን ፍቅር ነው። ሁሉም ነገር ያልፋል። ፍቅር ያሸንፋል!
 እሁድ እንዲህ አለፈ። ከዚያ በኋላ ልክ እንደ ህጻን ልጅ ተኛሁ።  ነገ ሌላ ቀን ነው።...

No comments:

Post a Comment