«በኢትዮጵያ ደህንነቶች አንተዳደርም» የሻዕቢያን አስተዳደር በመሸሽ ወደ ኢትዮጵያ የተሰደዱ የኤርትራ ተወላጆች «በኢትዮጵያ ደህንነቶች ስር አንተዳደርም» በሚል የተቃውሞ ድምጻቸውን በማሰማታቸው ግጭት መነሳቱ ተሰማ። የስደተኛ ካምፑ አስተዳደሮች « ሻዕቢያ ያሰረጋቸው ሰላዬች እንጂ እውነተኛ ስደተኞች
ይህንን ጥያቄ አያነሱም» ማለታቸውን ከስፍራው ከነበሩ ለመረዳት ተችሏል። ኦክቶበር 5 ቀን 2013 ማምሻውን በትግራይ ማይኒ ቀበሌ «ማይኒ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ውስጥ የተቀሰቀሰው ረብሻ ሲነሳ ስደተኞቹ ያሰሙት ቅሬታ» በወታደሮች አንተዳደርም፣ «የካምፑ ሰራተኞች በሙሉ ኢትዮጵያዊ ናቸው፣ የደህንነት ሰራተኞች ሊያስተዳድሩን አይገባም… »የሚሉ ሲሆኑ የጥያቄያቸው መደምደሚያ «በስደተኞች ድርጅት ዩ.ኤን.ኤስ.አር ሰራተኞች እንተዳደር» የሚል ነው። በተጠቀሰው ቀን ምሽት በጣሊያን ውሃ ላይ ሰጥመው ለሞቱ የኤርትራ ተወላጆች የሃዘን ስሜት ለማንጸባረቅ በተዘጋጀ የሻማ ማብራት ስነ ስርዓት ላይ ረብሻው እንደተነሳ የገለጹት የስፍራው የጎልጉል ምንጭ፣ ረብሻውን ተከትሎ ድንጋይና የተለያዩ ቁስቁሶች መወርወራቸውን አመልክተዋል። ረብሻውን ለማስቆም ታጣቂ የወታደሮች ተኩስ መክፈታቸውን የገለጹት ክፍሎች አራት ስደተኞች መቁሰላቸውን ተናግረዋል። ረብሻው እስኪነጋጋ ድረስ መቀጠሉንም ጠቁመዋል። ይህ ዜና እስከተጠናከረበት ጊዜ ድረስ ረብሻው ስለመቆሙ የተባለ ነገር የለም። የዜናው ምንጮች በካምፑ አስተዳደሮች በኩል ስለሚሰጠው ምላሽ ተጠይቀው «ሻዕቢያን አምልጠው ስደት ካምፕ በሰላም የደረሱ ስደተኞች በምንም መልኩ ተቃውሞ ሊያነሱ አይችሉም። ስደተኛ መስለው የተቀላቀሉ የሻዕቢያ የደህንነት ሰራቶች ናቸው ይህንን የሚያደርጉት» ሲሉ መስማታቸውን ተናግረዋል። ከተባበሩት የስደተኞች ኮሚሽን በስደተኞች ስም የሚገባው ከፍተኛ ገንዘብ ይዘረፋል በሚል ውስጥ ውስጡን ቅሬታ እንደሚደመጥ የጠቆሙት እነዚህ ክፍሎች፣ ገንዘብን አስመልክቶ ስደተኞች ከሚያሰሙት ቅሬታ በላይ ኢህአዴግና ለስደተኞች የሚላከው ገንዘብ መጠን እንዳሳሰበው ያስረዳሉ። ስደተኞቹ የባንክ አገልግሎት ተጠቃሚ በመሆናቸው ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚረዱዋቸው ወገኖቻቸው በባንክ የሚልኩላቸው ገንዘብ መብዛቱ ኢህአዴግን እንዳስጨነቀው ስለ አሰራሩ የሚያውቁ ክፍሎች አስረድተዋል። ከፍተኛ መጠን ያለው ብር ወደ ስደት ካምፖች የሚላከው «በትክክል ከዘመድ አዝማድ ወይስ ከሌላ?» የሚለውን ኢህአዴግ ማጥናት ከጀመረ መቆየቱን አመልክተዋል። በማይኒ ካምፕ ብቻ ከ4000 በላይ ስደተኞች እንደሚገኙ የሚገልጹት ምንጮች አብዛኞቹ የአስተዳደር ሰራተኞች የኤርትራ ዜግነት ያላቸው የኢህአዴግ ወዳጆች እንደሆኑ ቢገለጽም ስደተኞቹ ሊቀበሉት አልቻሉም። ተናሳ የተባለው ረብሻ በኢህአዴግና በ ሻዕቢያ መካከል ያለው ውጥረት በተካረረበት ወቅት መሆኑ ጉዳዩን እንዳያወሳስበው ስጋት አለ። አስተያየት ሰጪዎች አንደሚሉት ስደተኞቹ ኢትዮጵያ ምድር ቢገኙም የሚተዳደሩት በዓለም የስደተኞች ድርጅት ስር በመሆኑ ያለመሰለል መብታቸው የተጠበቀ ነው። እንደተባለው እየተሰለሉ ከሆነ አግባብ አይደለም ድርጊቱን ድርጅቱ ራሱ ያወግዘዋል ብለዋል። በሌላ በኩል ግን የስደት ከለላ የሰጠችውን አገር ደህንነት በሚፈታተን መልኩ መንቀሳቀስ ሌላው ትልቁ የህግ ጥሰትይሆናል ሲሉ ተናግረዋል። ዜናውን አስመልክቶ ከኢህአዴግ ወገን እስካሁን የተባለ ነገር የለም። በኢትዮጵያ በተለያዩ የስደተኞች ካምፕና በአዲስ አበባ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ የኤርትራ ተወላጆች መኖራቸው ይታወቃል። ከጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
No comments:
Post a Comment