Monday, October 14, 2013

ስንቱን አጣን! (ፕ/ር መስፍን ወልደ ማርያም)



እንደኢትዮጵያ ባለ ኋላቀር አገር አገር ውስጥ መሠልጠን ብዙ ችግር አለበት፤ እኔ ራሴ በኮምፒዩተር መጻፍ ከጀመርሁ ሠላሳ ዓመት ሊሆነኝ ነው፤ ታዲያ መብራት ጠፋና የምሠራው ባጣ የቆዩ ወረቀቶችን ሳገላብጥ አንድ እአአ በዲሴምበር 26 1965 ከዱሮ ተማሪዬ የተጻፈልኝን ደብዳቤ አገኘሁ፤ በዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በነበረ ከአንድ በጣም ጎበዝ ወጣት የተላከልኝ ነበረ፤ ከተመረቀ በኋላ በአንድ ኩባንያ ውስጥ ተቀጥሮ ለጥቂት ዓመታት ሠርቶ ትምህርቱን ለመቀጠል ወደአሜሪካ ሄዶ በሎዝ አንጄለስ አካባቢ ከሚገኝ ትምህርት ቤት ገብቶ ነበር፤ ደብዳቤውን የጻፈልኝ ከዚያ ነው፤ ደብዳቤው ሰባት ገጾች አሉት፤ ከሰባቱ ገጾች አምስቱ ስለኢትዮጵያ ያለውን ስጋት የሚገልጽ ነው፤ በሎዝ አንጀለስ አካባቢ ካሉ ኢትዮጵያውያን ጋር ውይይት በሚያደርግበት ጊዜ ሁሉ ብዙዎቹ የሚያሳዩት የመንደረኛነት ስሜት እያበሳጨው የተማሩት ሰዎች በእንደዚህ ያለ ማኅበረሰባዊ ኋላቀርነት ውስጥ ሆነው ኢትዮጵያ የምትባለው አገር እንዴት መራመድ ትችላለች? እያለ ይሰጋ ነበር።

Prof. Mesfin Woldemariam
Prof. Mesfin Woldemariam
ደብዳቤውን ላቋርጥና ስለሰውየው ትንሽ ልናገር፤ ተማሪ ሆኖ ክፍል ውስጥ ምንም ነገር የማያሳልፍ በጣም ተከራካሪ ተማሪ ስለነበረ አደንቀው ነበር፤ አንድ ጊዜ እንዲያውም የዘውድ መንግሥት ደጋፊ ነኝ አልሁና አንዴት በትከሻው ላይ ጭንቅላት ያለው ሰው ዓመቱን በሙሉ የዘውድ አገዛዝ የሚያደርስብንን በደልና ችግር ሲነግረን ቆይቶ አሁን ደግሞ ያንን ደጋፊ ነኝ ይላል ብሎ ወረፈኝ፤ ልጁን ስለማውቀው አነጋገሩ አሳቀኝ እንጂ አላስቆጣኝም፤ ጥያቄህ ይገባኛል፤ ግን እኔን ሳትወርፈኝ መጠየቅ ትችል ነበር በዬ ቢቀበለውም ባይቀበለውም ለጥያቄው መልሱን ሰጠሁት፤ በኋላም ጥሩ ጓደኛዬ ነበር።

ከአሜሪካ ትምህርቱን ጨርሶ እንደመጣ ተገናኘንና ወደቀድሞ ሥራው ወደወንጂ ተመልሶ እንደሆነ ስጠይቀው ‹‹እንዴት ብዬ! ዕድሜ ልኬን የፈረንጅ አሽከር ሆኜ መኖር አልፈልግም፤ አሁን ደግሞ ያስተማረኝን ሕዝብ ላገልግል እንጂ!›› ነበር ያለኝ፤ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና በወንጂ ባሉት ደመወዞች መሀከል ከፍተኛ ልዩነት ነበረ፤ ቁም-ነገረኛነቱን፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያለውን ታማኝነት፣ የግል ጥቅሙን ቀንሶ ኢትዮጵያን ለመርዳት ባሳየው ተግባራዊ አርአያነት የማደንቀው የወታደር ልጅ ነው።
ይህ ሰው በደርግ ጊዜም አልሸሸም፤ በአንድ ኢንዱስትሪ ውስጥ በሥልጣን ቦታ ላይ ነበር፤ ወያኔ/ኢሕአዴግ ወንበሩን ሲይዝ እንደዚህ ያሉ ሰዎች የማይፈለጉ መሆናቸው ሲታወቅ አገሩን ጥሎ ተሰደደ፤ በትልቅ ዓለም-አቀፍ መሥሪያ ቤት ጥሩ ሥራ አግኝቶ ዕድሜው ለጡረታ እስቲደርስ ቆየ፤ ወደሚወዳት አገሩ ለመመለስ አልቻለም፤ ከአንድ የትምህርት ቤት ጓደኛው ጋር ግንኙነት እንዳለው አውቃለሁ፤ አንድ ቀን ስለዚሁ የጋራ ጓደኛችን ስናወራ ለምን ወደኢትዮጵያ እንደማይመለስ ጠየቅሁ።
የዚህ ወጣት አጎት በወታደርነት ኢትዮጵያን ለረጅም ጊዜ በክብር ያገላገለ ነው፤ ይህ ሰው ወያኔና ሻቢያ በተጣሉ ጊዜ ዜግነታቸው በጉልበት እየተገፈፈ ከአገራቸው እንዲወጡ ከተደረጉት ሰዎች አንዱ ነው፤ በዚያን ጊዜ በሌላ የኤርትራ ተወላጅ ላይ የተፈጸመውን ግፍ ራሱ ሰውዬው በአሜሪካ ድምጽ ራድዮ ሲናገር የሰማሁት የሚከተለውን ነው፤– ‹‹ለኢትዮጵያ በአለኝ ሁሉ አገልግያለሁ፤ ኢትዮጵያን ሳገለግል አንድ እግሬን አጥቻለሁ፤ አንድ ሰው ለአገሩ ከዚህ የበለጠ ምን ያደርጋል?›› ብሎ ሲናገር አስለቅሶኛል።
የኔ የቀድሞ ተማሪና ወዳጅም ለምን ወደኢትዮጵያ እንደማይመለስ ሲጠየቅ ‹‹ለጋሼ (ማለት ለአጎቱ) ያልሆነች ኢትዮጵያ ለእኔ አንዴት ትሆነኛለች? በማለት በጥያቄ መለሰ አሉ፤ አባቱ ያገለገላትን፣ አጎቱ የለፋላትን፣ አያት ቅድመ-አያቶች የሞቱላትንና የደሙላትን አገር እንዲህ በቀላሉ ማጣት ነፍስን ያቆስላል፤ የነዚያን ሰዎች ሁሉ መስዋእት ያከሽፋል፤ ያረክሰዋል፤ ይህንን የተገነዘቡና ያዘኑ፣ ያለቀሱ ሰዎች ናቸው –
እናት ኢትዮጵያ ሞኝ ነሽ ተላላ፣
የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ!

No comments:

Post a Comment