Tuesday, October 29, 2013

የደብረማርቆስ ዩኒቨርስቲ አስተዳደር ከተማሪዎች አመጽ ጀርባ ኢሳት እና ሌሎች ሀይሎች እንዳሉበት ገለጸ


ኢሳት ዜና :- ተማሪዎች የርሃብ አድማ በማድረግ ላይ ሲሆኑ ዩኒቨርስቲው ትክክለኛነቱን አረጋግጦዋል፡፡
የተማሪዎች አመጽ የተነሳው መንግስት ለዩኒቨርስቲ ተማሪዎች አዲስ የአለባበስ ፤ የአመጋገብ እና የአምልኮ ስርዓት ህግ ማውጣቱን ተከትሎ ነው። ” ተማሪዎች እምነታችሁ ተው ፣ ማተባችሁን በጥሱ” ተብለናል ይላሉ።

በ2004 እና በ2005 ዓም ተማሪዎች ህጉን እንዲተገብሩ ሙከራ ቢደረግም ተማሪዎች ለመቀበል ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ህጉ ሳይተገበር ቀይቷል ሲሉ የደብረማርቆስ ዩኒቨርስቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ንጉሴ ምትኩ ከክልል አመራሮች ጋር ባደረጉት ውይይት ተናግረዋል።
ተማሪዎች ለዘጋቢያችን እንደነገሩት ቁርስ፣ ምሳ እና እራት ለመመገብ በሀገሪቱ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የተፈቀደው የቀን በጀት 12 ብር ብቻ ነው፡፡ በደብረ ማርቆስ ከተማ 12 ብር አንድ ሻይ እና ዳቦ የመግዛት አቅም የሚሉት ተማሪዎች፣ መንግስት እየመገበን ሳይሆን የርሃብ አድማ ውስጥ እያስገባን ነው ይላሉ።
የተማሪዎችን ጥያቄ ትክክለኛነት የደብረማርቆስ ዩኒቨርስቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ንጉሴ ምትኩ ያረጋግጣሉ፡፡ ተማሪዎች የሚቀርብላቸው የምግብ አቅርቦት የበጀት አነስተኛነት ከፍተኛ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ከመንግስት ፈቃድ ውጭ በሚልየን የሚቆጠር የበጀት ድጎማ እያደረግን ተማሪዎችን ለመመገብ ጥረት አድረገናል የሚሉት ፕሬዚዳንቱ፣ ሁኖም ግን መንግስት በገመገመውና በተቸው መሰረት የዳቦ ግራማቸው ከ80 ወደ 45 ግራም ዝቅ እንዲል መደረጉን ተናግረዋል፡፡
ተማሪዎች በ45 ግራም ዳቦ እና ከዚያ ባነሰ ሁኔታ ቁርሳቸውን እንዲመገቡ ተገደዋል፡፡ የዳቦው መጠን ግን ተማሪዎች አውጥተው ባስመዘኑት መሰረት ከ25- 30 ግራም የሚመዝን ሲሆን አንድ ጉራሻ የመሆን አቅም ብቻ ነው ያለው፡፡
በምግብ እጥረት ትምህርት በተጀመረ በወር ጊዜ ውስጥ 32 ተማሪዎች ታመው ወደ ህክምና ተቛማት መወሰዳቸውን ከጤና ጥበቃ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
የደብረማርቆስ ዩኒቨርስቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ንጉሴ ምትኩ የተማሪዎች አመጽ የአመጋገብ እና የአምልኮ ስርዓት የወጣውን ህግ ለማስተግበር በተካሄደው አሰገዳጅ ህግ እና በምግብ ማነስ ምክንያት በተነሳ ርሃብ ላይ ብቻ የተመሰረት ሳይሆን ኢሳት እና ሌሎች ሃይሎች ያደራጁት ሊሆን እንደሚችል፣ ኢሳት ዘገባውን ያቀረበበትን ሰአት አይቶ መናገር እንደሚቻል ገልጸዋል።
በአመጹ ሙሉ በሙሉ የስድስት ህንፃዎች መስታውቶች ወድመዋል፤ ሶስት የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ አምቡላንሶችን ጨምሮ ከአገልግሎት ውጭ ሁነዋል፡፡
አመጹን የፌደራል ፖሊስ ለመቆጣጠር በወሰደው እርምጃ በተማሪዎች ላይ ድብደባ ፈጽሟል፡፡
የአካባቢው ነዋሪዎች ለአመጹ ድጋፍ በመስጠታቸው ዬዩኒቨርስቲው መሪዎች ወቀሳ ሰንዝረዋል፡፡ነዋሪዎች በበኩላቸው ተማሪዎች እየራባቸው ሲወድቁ መመልከታቸውን ለደብረ ማርቆሱ ወኪላችን ነግረውታል፡፡ ተማሪዎቹ በተደጋጋሚ ጥያቄ አቅርበው መልስ በማጣታቸው በአጸፋው የወሰዱት እርምጃ አስተማሪ መሆኑንም ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡
ESAT

No comments:

Post a Comment