Sunday, October 13, 2013

መሐሙድ አህመድ የቴዲ አፍሮን ኮንሰርት አቋርጦ ሄደ


የኢትዮጵያውያን በመላው አለም መበተን ለአርቲስቶቻችን በተለይም በሙዚቃው ኢንዳስትሪ ለተሰማሩ ጥሩ የገቢ ምንጭ እየሆነላቸው ይገኛል፡፡ አቀንቃኞቻችን በውጪ የሚገኙ ዳያስፖራዎቻችንን ለማዝናናት፣ የአገር ቤት ፍቅራቸውን የሚቀሰቅሱና ስሜት የሚኮረኩሩ ዘፈኖችን በሙዚቃ አልበሞቻቸው በማካተት በአውሮፓ፣ በአውስትራሊያ፣ በመካከለኛው ምስራቅና በአሜሪካ በወኪሎች አማካኝነት ኮንሰርቶችን በማዘጋጀት ኪሳቸውን አደልበው ወደ አገር ቤት ይመለሳሉ፣ አንዳንዶቹም ዶላሩ ጥሟቸው በወጡበት ቀርተው ኑሯቸውን ይመሰርታሉ፡፡

  ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ከሁሉም የሙዚቃ ሰዎቻችን በአውሮፓ፣ በአሜሪካና በመካከለኛው ምስራቅ በዛ ያሉ ኮንሰርቶችን በማዘጋጀት ግምባር ቀደም ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ የቴዲ ኮንሰርቶች በብዛት ብቻ ሳይሆን በተመልካች ቁጥርም ወደር ያልተገኘላቸው ለመሆናቸው ሲነገር መስማት አዲስ ነገር አይደለም፡፡
‹‹ፊዮሪና እና ካብ ዳህላክ›› የተሰኙ ተወዳጅ ዘፈኖቹም ቴዲን በኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳይሆን በኤርትራዊያንም ኮንሰርቶቹ የሚናፈቁ እንዲሆኑ አድርገውለታል፡፡ ለምሳሌ በቅርቡ ሆላንድ አምስተርዳም ውስጥ አዘጋጅቶት በነበረው ኮንሰርት ለመዝናናት ከገቡ ታዳሚዎች መካከል ግማሽ ያህሉ ኤርትራዊያን እንደነበሩ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ሁለቱን ዘፈኖች በመዝፈንም ቴዲ ኤርትራዊያኑን ‹‹እንኳን ለአዲሱ ዓመት አደረሳችሁ›› ብሏቸዋል፡፡ ኤርትራዊያኑም ለአቀንቃኙ የአገራቸውን ባንዴራ በመሸለም ለእርሱ ያላቸውን ፍቅርና አክብሮት ገልጸውለታል፡፡
      ቴዲ አፍሮ የአምስተርዳሙን የአዲስ አመት ዝግጅት ከማከናወኑ ቀደም ብሎ በአሜሪካ ዋሽንግተን ከተማ ኤኮ ስቴጅ ደማቅ የተባለለትን ኮንሰርት አዘጋጅቶ ነበር፡፡ አዲሱን የሙዚቃ አልበሙን ከስራ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በዋሽንግተን ከሚገኙ አድናቂዎቹ ጋር የተገናኘው ቴዲ ኮንሰርቱን የማዘጋጀት ኃላፊነት በአትላንታ ነዋሪ ለሆነው መሐመድ ከድር ለተባለ ኢትዮጵያዊ ሰጥቶ ነበር፡፡ ኃላፊነቱን የወሰደው መሐመድ በወቅቱ አሜሪካ የነበረውን ታላቁን አቀንቃኝ መሐመድ አህመድን በመገናኘት በኮንሰርቱ ላይ የሙዚቃ ስራዎቹን እንዲያቀርብ ይጋብዘዋል፡፡ 
      ጋሽ መሐሙድ ኮንሰርቱ የቴዲ አፍሮ መሆኑን መረጃ እንዳልነበረው የሚጠቅሱ የላይፍ የዋሽንግተን ምንጮች መሐሙድ ግብዣውን በመቀበል በዕለቱ በኤኮ ስቴጅ መገኘቱን ያወሳሉ፡፡፡ ኮንሰርቱን ለመጀመር ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩት ቴዲ አፍሮ ጋሽ መሐሙድን በማግኘት ኮንሰርቱ የእርሱ መሆኑንና ታዳሚዎቹም በዋናነት እርሱ (ቴዲ) እንደሚመጣ ተነግሯቸው እንደመጡ በመንገር የኮንሰርቱን የመክፈቻ ዘፈኖች እንዲጫወት መሐሙድን ይጠይቀዋል፡፡
      ጋሽ መሐሙድ ከቴዲ በሰማው ነገር በመገረም ‹‹ኮንሰርቱ በመሐመድ ከድር መዘጋጀቱ ከተነገረው ውጪ በቴዲ ለቴዲ መዘጋጀቱን እንዳልሰማ በመጥቀስ ነገር ግን በዕድሜና ሙዚቃን ረዘም ላሉ አመታት ከመጫወቱ አንጻር የኮንርሰቱ የመዝጊያ ሰዓት ሲደርስ የሙዚቃ ስራዎቹን ማቅረብ እንደሚገባው ይገልጻል፡፡ ቴዲ በመሐሙድ አባባል ደስተኛ ባይሆንም መሆን የሚገባው መሐሙድ የሚለው መሆኑን በመገንዘብ ስምምነቱን በመግለጽ በናፍቆት ሲጠብቁት ከነበሩት የኮንሰርቱ ታዳሚዎች ጋር ይገናኛል፡፡
      ቴዲ ውሃ ለመጠጣት ወይም ትንፋሽ ለመሰብሰብ ከመድረክ ሳይወርድ 14 ዘፈኖችን ይጫወታል፡፡ በእያንዳንዱ የቴዲ ዘፈን የሙዚቃ ስልቱን እየተከተለ ሲናጥ ያመሸው ታዳሚ ለዕረፍት የሚጠጣ ነገር ፍለጋ እንደተሰማራ መሐሙድ ወደ መድረክ እንዲወጣ ይጋበዛል፡፡ ታዳሚው ለጋሽ መሐሙድ የሙዚቃ ስራዎች አክብሮትና ፍቅር ያለው ቢሆንም ለረዥም ሰዓት ከቴዲ ጋር ሲጨፍር በመቆየቱ ተዳክሞ ነበር፡፡ ሁኔታውን የተገነዘበው ጋሽ መሐሙድ ከአራት ያልበለጡ ዘፈኖችን በመጫወት ከእረፍት መልስ ሌሎች ዘፈኖችን እንደሚያቀርብ ለታዳሚው ቃል በመግባት ከመድረኩ ይወርዳል፡፡ ለግማሽ ሰዓት ያህል በዲጄ ለስላሳ ሙዚቃዎች ሲያዳምጥ የቆየው ታዳሚ እረፍት በማግኘቱ የምሽቱ የመድረክ ፈርጥ የነበረው ቴዲ አፍሮ ‹‹እህህ ስለናፈቀችኝ የእኔ አይናማይቱ›› የሚለውን የጋሽ መሐሙድን ተወዳጅ ዘፈን እየተጫወተ ወደ መድረኩ ወጣ፡፡
      ጋሽ መሐሙድ ቴዲ አፍሮ የተጫወተውን ዘፈን ይዞ ለመቅረብ እየተዘጋጀ በነበረበት ሰዓት እርሱ በአካል በተገኘበት መድረክ ዘፈኑ በሌላ ሰው መቅረቡና እንደገና የመጫወት ዕድል በመነፈጉ በመበሳጨት ታዳሚውን ሳይሰናበት ኮንሰርቱን ጥሎ መሄዱ ታውቋል፡፡
   ቴዲ አፍሮ በሞት ለተለየን ለጋሽ ጥላሁን ከፍተኛ አድናቆትና አክብሮት እንደነበረው የሚያስታውሱ የዝግጅቱ ታዳሚዎች የጥላሁን ወዳጅና የሞያ እኩያ ለነበረው መሐሙድ ክብር አለመስጠቱ አግራሞት እንደጫረባቸው በስፍራው ለታደመው የላይፍ ምንጭ ነግረውታል፡፡ ቴዲ አፍሮ በጉዳዩ ዙሪያ የሚሰጠውን ምላሽ ለማካተት ሙከራ ያደረግን ቢሆንም የእርሱም ሆነ የማናጀሩ (የባለቤቱ) አምለሰት ሙጬ ተንቀሳቃሽ ስልኮች አገልግሎት የማይሰጡ በመሆናቸው ሙከራችን አልተሳካም፡፡
source: dawitsolomon.wordpress.com

No comments:

Post a Comment