ባለፉት ሃያ ሁለት አመታት ጋምቤላ፤ ኦጋዴን፤ ጉራ ፈርዳ፤ ቤንሻንጉል፤ አርባጉጉና አዲስ አባባ ዉስጥ ለፈጸሙት የዘር ማጥራትና የዘር ማጥፋት ወንጀል ተጠረርጠሪ የሆኑትን የዘረኛዉ የወያኔ አገዛዝ ባለስልጣኖች ለአለም አቀፉ ፍርድ ቤት ለማቅረብ የሚደረገዉ ጥረት በአዲስ መልክ ተጧጡፎ መቀጠሉን ሰሜን አዉሮፓ ዉስጥ የሚገኙ ዘጋቢዎቻችን በላኩልን ዜና ገለጹ። ኢትዮጵያ ዉስጥ በኦጋዴን ክልል የወያኔ አገዛዝ የሚፈጽመዉን የጦር ወንጀልና የሰብአዊ መብት ጥሰት የሚያሳዉና በወጣት አብዱላሂ ሁሴን አማካኝነት ከኢትዮጵያ ሾልኮ ከወጣዉ ቪድዮ ጋር ተቀነባብሮ የተሰራዉ ዘጋቢ ፊልም ሲዊድን ዉስጥ በቴሌቪዥን ከቀረበ በኋላ ፊልሙን የተመለከቱ ስዊድናዉያንና ሌሎችም አለም አቀፍ ጠበቆች ጉዳዩን ወደ አለማቀፍ ፍርድ ቤት ለመውሰድ እስካሁን ድረስ ያልታየ ትልቅ ንቅስቃሴ ጀመረዋል። ወጣት አብዱላሂ ለኢሳት ቴሌቪዥንና ሬድዮ በሰጠዉ ቃለመጠይቅ እንደተናገረዉ ፊልሙ በቴሌቪዥን ከተላለፈ በኋላ ሌሎች ብዙ የአገሪቱ ሚዲያዎች ሰፊ ሽፋን አንደሰጡትና ይህንኑ የተከታተሉት ስቴላም የተባሉ የ አይ ሲ ጄ ጠበቃ ጉዳዩን ፍርድ ቤት እንደሚያቀርቡት በሬዲዮ ይፋ አድርገዋል።የስዊድን የጦር ወንጀል ኮሚሽን ፍርድ ቤትም ማስረጃዎችን በመመርመር ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ለመውሰድ ከወጣት አብዲ ጋራ ቀጠሮ ይዘዋል። ጠበቆቹ ጄኔቫ ካለው አይሲጄ ጋር እና ከሌሎችም የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ጋር በጋራ በመሆን ጉዳዩን ወደ አለማቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት ለመውሰድ እንደሚሞክሩ ተናግሯል።
በዚህ “የአምባገነኖች እስረኞች” ተብሎ በተሰየመዉ ፊልም ዉስጥ ልዩ ፖሊስ እየተባለ በሚጠራው ሀይል የተፈጸመ የዘር ማጥፋት ወንጀልን የሚያሳይ መረጃና፣ የክልሉን ፕሬዚዳንት የተቸች አንዲት ሴት በኦበነግ አባልነት ስትፈረጅ የሚያሳይ መረጃ ተካቶበታል ። የክልሉ ፖሊስ ሀላፊው በእስር ላይ የሚገኙትን ሴቶች በመድፈር ብዙ ህጻናት በእስር ቤት ውስጥ መወለዳቸውን በፖሊሶች በራሳቸው ሲነገር የሚያሳይ መረጃም በፊልሙ ዉስጥ መካተቱትንና ፊልሙ ከዚህ በፊት በኢሳት ቴሌቪዥን ቀርቦ በታየዉ ቢድዮ ዉስጥ ያልተካተቱ መረጃዎችን ማቀፉን ወጣት አብዱላሂ ገልጿል።
ኦጋዴን ዉስጥ የሚፈጸመዉን ግፍ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳየዉን ፍልምና ፊልሙ ወንጀለኞቹን ለፍርድ በማቅረብ በኩል ያለዉን ፋይዳ አስመልክቶ ኢሳት ቴሌዥንና ሬድዮ ያናገራቸዉ የአለማቀፍ የህግ ባለሙያዎች ኮሚሽን በእንግሊዝኛ ኮሚሽነር የሆኑት ስቴላ ጋርደ ለኢሳት እንደገለጹት የወንጀሉን ፈጻሚዎች ወደ ፍርድ ለማቅርብ የሚችሉትን ሁሉ እንደሚጥሩ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የአለማቀፍ ወንጀል (ICC) ፈራሚ አገር ባለመሆኗ ማስረጃውን በቀጥታ ለፍርድ ቤቱ መላክ እንደማይቻል የገለጹት ኪሚሽነር ጋርደ፣ ይሁን እንጅ ሰቆቃን ለመከላከል የተቋቋመው ኮሚቴ (Committee Against Torture) ፈራሚ አገር በመሆኗ ጉዳዩን በዚሁ በኩል ለመከታተል እና የስዊድን ፖሊስ ምርመራ ጀምሮ እርምጃ ለመውሰድ እንዲችሉ ጥረት እንደሚያደርጉ ለኢሳት ገልጸዋል። ከዚህ በተጨማሪ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰብአዊ መብት ኮሚቴ እነዚህን ማስረጃዎች እንዲያገኙ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል። የኖርዌይ የቴሌቪዥን ጣቢያም ፊልሙን በቅርቡ ያሰራጫል ተብሎ ይጠበቃል። ፊልሙ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ተተርጉሞ በተለያዩ አለማቀፍ የመገናኛ ብዙሀን ይቀርባል።
No comments:
Post a Comment