ኢሳት ዜና :-በኦጋዴን የሚፈጸመውን የሰብአዊ መብት ጥሰትና የጦር ወንጀል የሚያሳየው ዘጋቢ ፊልም በቅርቡ በስዊድን ቴሌቪዥን መለቀቁን ተከትሎ ዛሬ አርብ፣ የስዊድን የጦር ኮሚሽን ማስረጃዎችን ተረክቧል።
ማስረጃዎችን ለኮሚሽኑ ያስረከቡት ሂደቱ ዋና ተወናይ የሆነው ወጣት አብዱላሂ የሱፍና የአለማቀፍ የህግ ባለሙያዎች ኮሚሽን ኮሚሽነር የሆኑት ስቴላ ጋርደ ናቸው።
የጦር ኮሚሽኑ የቀረበለትን ማስረጃ በማየት አፋጣኝ ውሳኔ እንደሚሰጥ መግለጹን ወጣት አብዱላሂ ለኢሳት ተናግሯል።
ይህ በእንዲህ እንደላ በስልጣን ላይ የሚገኙ የአፍሪካ መሪዎች ያለመከሰስ መብታቸው እንዲከበር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጠየቁ
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም የአፍሪካ ህብረት 15ኛው አስቸኳይ የመሪዎች ስብሰባ ላይ በጉዳዩ ላይ በመምከር ያስተላለፈው ውሳኔም ተግባራዊ እንዲደረግ ጠይቀዋል።
ዶክተር ቴዎድሮስ ተቀማጭነታቸው አዲስ አበባ ከሆኑ የዓለም አቀፉ የፀጥታው ምክር ቤት አባል ሀገራት አምባሳደሮች ጋር ባደረጉት ውይይት አለማቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት የፊታችን የፈረንጆች ህዳር 12 ቀን የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬኒያታንና ምክትላቸውን ዊሊያም ሩቶን ለመክሰስ የያዘውን እቅድ መሰረዝ አለበት በማለት መናገራቸውን የጊዜው ፓርቲ ልሳን ፋና ዘግቧል።
በውይይቱ ላይ በፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ ያላቸው አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ሩሲያ፣ ቻይናና ፈረንሳይን ጨምሮ የ10 ቋሚ ያልሆነ መቀመጫ ያላቸው አባል ሀገራት አምባሳደሮች ተሳትፈዋል።
ታዋቂው ደቡብ አፍሪካዊ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ሊቀጳጳስ ዴዝሞንድ ቱቱ የአፍሪካ መሪዎች በፍርድ ቤቱ ላይ የሚያሰሙት ተቃውሞ ” እንደፈለጉ ሲግድሉና ሲያሰቃዩ እንዳይጠየቁ ነው” ብለዋል።
የቀድሞው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሀፊ በበኩላቸው ፣ ጥያቄውን ያቀረቡትን “ማፈሪያዎች” ብለዋቸዋል።
ዶ/ር ቴዎድሮስ ያቀረቡት ጥያቄ የኢህአዴግ ባለስልጣናት በፍርድ ቤቱ እንቅስቃሴ ስጋት ላይ እየወደቁ መምጣታቸውን የሚያሳይ ነው።
No comments:
Post a Comment