Sunday, October 13, 2013

የፖለቲካ ፓርቲዎች ሥር ነቀል የአስተሳሰብና የአቋም ለውጥ አስፈላጊነት


ከእንጉዳይ በቀለ፣ አዲስ አበባ ሕወሐት/ኢህአዴግ ኢትዮጵያን በጉልበትና በግፍ መግዛት ከጀመረ 22ኛ ዓመቱን ይዟል፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ እንደ ሟርትአይታይብኝና ይህ ቁጥር አሁን ካለው እውነታ በመነሣት ወደ ሠላሳና አርባ ብሎም ሃምሳ የማይዘልቅበት ምንም ምክንያት ያለ አይመስልም.. ይህን ለመገመት ውስብስብ ስሌት ወይንም የሂሣብ ቀመር አይጠይቅም፡፡ በአገር ቤት ያለውን አያያዝና በተቃዋሚዎች በኩል ያለውን እንቅስቃሴ በመቃኘት ስህተት ነው ሊባል ከማይችል ድምዳሜ ላይ ሊደረስ ይቻላል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በአገራችን ፖለቲካ በእጅጉ ከመሰላቸቱ የተነሣ መፃዒ ዕድል ፈንታውን ከእግዚአብሔር እንጂ ከተቃዋሚዎች ወይንም ከፖለቲካ ድርጅቶች ተስፋ ማድረግ ከተወ ሰነባብቷል፡፡ አንደኛው ምክንያቱም ተስፋ ሊጥልበት

የሚያስችለውና ከወሬ በቀር በተግባር የሚያየው የተቃዋሚዎች እንቅስቃሴ አለመኖሩ ሲሆን በዋነኛነት የሚጠቀሰው ሁለተኛው ምክንያት ግን በሕይወት አለን የሚሉት ተቃዋሚዎች ሕወሐት/ኢሕአዴግን ሊያስወግድ የሚችል እዚህ ግባ የሚሉት (ጠንካራ) አቋምም ዝግጅትም ስለሌላቸው፤ እንዲያውም ጊዜ ባለፈበት አቋማቸው ሕዝቡን ከመከፋፈላቸው በተጨማሪ የግፈኛውን ገዢ ሥልጣን እያጠናከሩት በመሆናቸው ነው፡፡ ሕዝባችን በዚህ ሁኔታ በጣሙን ተጎድቷል፡፡ ተስፋም ቆርጧል፡፡ በምርጫ 97 እና በጦሱ የተሠበረው ቅስሙ ገና አልሻረም፡፡ በወቅቱ በሚገርም ደረጃ ለዓለም ኅብረተሰብ አሳይቶት
የነበረው ስሜቱ አሁንም ወደፊትም በውስጡ ተዳፍኖ የሚኖር እቶን እሣት ቢሆንም ያንን እምቅ ሕዝባዊ ኃይል ግን ተቃዋሚዎች በጥበብ ሊመጠቀሙበት አልቻሉም፡፡ አንዳንዶች ገና ከታሪክ ስላልተማሩና በሕዝቡ ፍላጎት ላይ የተመሠረተ አዲስ የትግል ስልት ባለመነደፋቸው እነሆ ጊዜና ጉልበት እየባከኑ፣ በሕዝቡ ስሜት ውስጥ የተዳፈነው ረመጥ (ፍም) ይበልጥ እየተቀበረ፣ ግፈኛው ገዢም በዕድሜ ላይ ዕድሜ እያገኘ ሊሄድ ችሏል፡፡ አዲስ ሥልት ሲባል በመሠረታዊ የአስተሳሰብ ለውጥ ላይ የሚገነባ ሥልት ማለት ነው፡፡ መሠረታዊው የአስተሳሰብ ለውጥ ሊመጣ የሚገባው ደግሞ ያለፈው
የሃያ ሁለት ዓመታት ተሞክሮ ካስገኘው ውጤት በመነሣት ነው፡፡ ያለፈው የሃያ ሁለት ዓመታት ተሞክሮ ለኢትዮጵያ ሕዝብ መልካም ትምህርቶች ሰጥተውታል፡፡ እነዚያም ትምህርቶች
ከአደገኛው የጎሣ ፖለቲካና በመዘዙ የተማራቸው ሲሆኑ፣ እርሱም (የጎሣ ፖለቲካው) ለዘመናት በፍቅር አብረው የኖሩ ሕዝቦችን እርስ በርሳቸው እንዲገፋፉ ምክንያት መሆኑን፣ በሕዝቦች መካከል ጥላቻን ያነገሠ፣ መተማመንን ያጠፋ መሆኑን፣ አንዱን ጎሣ ከሌላው ጋር ጤናማ ያልሆነና አላስፈላጊ ፉክክር ውስጥ ያስገባ መሆኑን፣ የዜጎችን ከቦታ ወደ ቦታ እንደልብ ተዘዋውሮ የመኖርና የመሥራት መብትን መገደቡን፣ ከልክ ያለፈ የሙስና ባሕልን ማስፈኑን፣ የጥቂቶችን በዪነትና የብዙኀንን ተመልካችነት ትርዒት ያጎለበተ መሆኑን፣ መሣሪያ የያዙና ሥልጣንን በሞኖፖል የተቆጣጠሩ ሰዎች የብዙኀንን የዜግነት
መብት በመጋፋት ቋንቋንና የፖለቲካ ታማኝነትን መለኪያ /መመዘኛ/ እያደረጉ የብዙኀንን መብት ለጥቂቶች ብቻ እንዲያውሉ ያደረገ መሆኑን፣ በአጠቃላይ ያልተመጣጠነ የሀብትና የሥልጣን ክፍፍልን ያነገሠ የተረገመ ሲስተም መሆኑን በሚገባ ተምሮበታል፡፡ ሕዝቦች በጎጥ ጠብበው አስተሳሰባቸውንና አቅማቸውን በትናንሽ ክፍሎች/ክልሎች/ ከፋፍለው እንዲቀጭጩ ያደረገ፤ ቅኝ
ገዢዎች አፍሪካን እንደልብ ለመግዛትና ሃብቷን ለመቦጥቦጥ በተንኮል የሠሩት ሲስተም መሆኑን በሚገባ ተምሯል፡፡ ትምሀርቱንም በወሬ ሳይሆን ኖሮበት የተማረው ነው፡፡ በተግባር!!! ስለዚህ ሕዝቡ ከዚህ እኩይ የሰይጣን ሲሰተም ለመገላገል ይፈልጋል፡፡ ከላይ የተጠቀሰው አዲሱ ሥልት መመሥረት የሚገባው ከዚህ በላይ በተቀመጠው እውነታ ላይ መሆን ይኖርበታል፡፡ ሥር
ነቀል የአስተሳሰብ ለውጥ ሳያደርጉ የዛሬ ሃያ ሁለት ዓመት ከነበረው አስተሳሰብ ሳይለወጡ፣ በለስ ከቀና የጎሣ ፖለቲካ ዱላውን ከሕወሐት/ኢሕአዴግ ላይ ተቀብሎ በተራዬ እሮጣለሁ ማለት ወይንም አሁን ያለውን ሕዝቡን ያንገሸገሸውን የጎሣ ፖለቲካ ጉልቻ ቀይሮ ብቻ ለመቀጠል ማሰብ የሚያዋጣም የሚሳካም አይሆንም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብን ድጋፍ ለማግኘት
ከዚያ ዓይነቱ አስተሳሰብ መለወጥ የግድ ነው፡፡ ሕዝባችንን በቋንቋ የመከፋፈሉን ተንኮል (ከፋፍለህ ግዛውን) ገና ከጠዋቱ የጠነሰሱ ቅኝ ገዢዎች ነበሩ፡፡ ኋላ ግን በነጻነት
ስም በአገራችን ውስጥ በሥራ ላይ እንዲውል ያደረጉት ሕወሐትና ሻዕቢያ ሲሆኑ እንደ ቅኝ ገዢዎቹ እነርሱም ለድብቅ ፕሮግራሞቻቸው ማስፈፀሚያ እንዲሆናቸው በተንኮል ያጠመዱት ወጥመድ (መርዝ) እንጂ በውኑ ለሕዝቦች ነፃነትን የሚያመጣ፣ በሌሎች አገሮች ተሞክሮ የሠራ የሕዝቦች ነፃነት ማስከበሪያ (መፍትሔ አምጪ) መሣሪያ ሆኖ አልነበረም፡፡
ይሄንንም ሕዝቡ በሚገባ ተረድቶታል፡፡ ይልቁንም በተለያዩ የዓለም ክፍሎች እንደተመሰከረለት በቋንቋ ላይ የተመሠረተ የህዝቦችና የአስተዳደርና አደረጃጀት ውጤቱ የዘር ማጥፋት ወንጀል የሚጫርበት (የሚነሳበት) የሲዖል ተምሳሌትነት ያለውና የርስ በርስ የዕልቂት ሁኔታዎችን የሚያመቻች አደረጃጀት መሆኑን ከነሩዋንዳ እንዲሁም ባለፈው ሃያ ሁለት
ዓመታት ከራሱ ሕይወት አረጋግጦታል፡፡ ሕዝባችን ሆደ ሰፊና አርቆ አስተዋይ በመሆኑና በቋንቋ መርዝነት የታቀደው
ተንኮል አልሠራ በማለቱ በሃይማኖትም እየተፈተነ ያለ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ እርግጥ ነው “የሠላማዊ ትግል በቃኝ!! መንግሥትን በኃይል እጥላለሁ” ብለው በመነሣት የትግል ሥልትና የአቋም ለውጥ
ያደረጉ አሉ፡፡ ያ ግን በራሱ ሕዝቡን ለማነቃቃትና ለማነሣሣት (ሞቢላይዝ ለማድረግ) በቂ አይደለም፡፡ በቋንቋ የተደራጁ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሥር ነቀል የአስተሳሰብ ለውጥ ማድረግና ትግሉን በትክክለኛ አሰላለፍ መቀላቀል አለባቸው፡፡ ሥር ነቀል ለውጥ ሲባልም በሕዝቡ ፍላጎት ላይ የተመሠረተ የትግል ስልትን መከተል ማለት ነው፡፡ ያም አንድና አንድ ነው…
ከብሔራው (የጎሣ ) አደረጃጀት ወደ ሕብረ ብሔራዊ (በኢትዮጵያዊነትን ብቻ መሥፈርት ወደአደረገ) አደረጃጀት መሻገር፡፡ ሕዝባችን የሚፈልገውና እንታገልልሃለን ከሚሉት ከፖለቲካ መሪዎቹ የሚጠብቀው ይህንን ብቻ ነው፡፡ ይህ ከሆነ ሕዝቡ ለትግል ይነሣል፣ ሕወሐት/ኢሕአዴግም ያኔ በትክክል ያበቃለታል ያበቃለታል፡፡
አንድ ሰው እንደተናገሩት ሕወሐት/ኢሕአዴግ በሰደድ እሣት ይመሰላል፡፡ የሰደድ እሣት ደግሞ አውሬ በመሆኑ በከፍተኛ ጥበብ ካልተያዘ (ኮንቴይን ካልተደረገ) በመንገዱ ላይ ያገኘውን መብላቱ አይቀርም፡፡ በመሠረቱ እሣት በሕይወት መቆየት የሚችለው የሚበላው ነገር (ነዳጅ) እስካገኘ ድረስ ብቻ ነውና ሰደድ እሣትን ለማጥፋት የሚቻለው ይህን መሠረታዊ
ባሕርዩን የሚቀይር ነገር ላይ ብቻ አትኩሮ ማርከሻውን መድኃኒት መሥራት ሲቻል ነው፡፡ አንዳንዴ ዶፍ እየወረደም ሰደድ እሣት ላይጠፋ ይችላል፡፡ የነዳጁ ዓይነት ለሰደድ እሣቱ የተመቸ ከሆነ እንኳንስ በዶፍ ውስጥ ይቅርና ውቅያኖስም ላይ ሆኖ ሊንቀለቀል፣ ሊንበለበል ይችላል፡፡ የሰደድ እሣትን ለማጥፋት መፍትሔው ከእሣት ማጥፊያ ቴክኒኮች አንዱን የሆነውን (ማስራብ የሚባለውን) ቴክኒክ በሥራ
ላይ ማዋል ብቻ ነው ፡፡ እሣት ለመንደድ ሦስት ነገሮች እንደሚያስፈልጉ ግልጽ ነው፡፡ ከእነኢህም አንደኛው፣ አቃጣዩ እሣት፣ ሁለተኛ፣ ተቃጣዩ ነዳጅና ሦስተኛ፣ አቀጣጣዩ (አናዳጁ) ኦክስጅን ናቸው፡፡ ከነዚህ ከሦስቱ አንዱ ከጎደለ እሣት በሕይወት ሊኖር አይቻለውም፡፡ ይሁን እንጂ የሰደድ እሣት በተነሣ ጊዜ አቀጣጣዩን ኦክስጅንን ማስወገድ የማይታሰብ ነገር
ነው፡፡ ስለዚህ አንዱና ብቸኛው ቀሪ አማራጭ ተቃጣዩን (ነዳጁን) በማስወገድ እሣቱን ማስራብ ብቻ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ነው በሰደድ እሣት የሚፈተኑ መንግሥታት ያላቸውን ኃይል በሙሉ አስተባብረው እሣቱ ያገኘውን እየበላ በሚነጉድበት አቅጣጫ ከፊቱ ቀድመው ደኑን ባገኙት ነገር በሙሉ (በዶዘርና በመሣሠሉት መሣሪያዎች) እየመነጠሩ እሣቱ
የሚበላውን ነገር በሙሉ (ነዳጁን) ከፊቱ ገለል የሚያደርጉበት፡፡ ያን ጊዜ እሳቱ የሚበላውን በልቶ በልቶ የተመነጠረው ሥፍራ ላይ ሲደርስ ምግቡ ስለሚያልቅበት አማራጭ የለውምና የግዱን ይጠፋል፡፡ የእሣት ነገር ደግሞ የሚገርመው ከጠፋ  ጠፋ ነው፡፡ ያገኘውን ሲበላና ሲያግበሰብስ ቢቆይም ከክፉ ቀን ራሱን ሊያቆይ የሚችልበት ነገር አያስቀምጥምና ቅሪቱን
(አመዱን) ትቶ ይሠወራል፡፡እንግዲህ ሰውየው ሕወሐት/ኢሕአዴግንም እንደ ሰደድ እሣት ያስቀመጡት በምክንያት ነው፡፡ ሕወሐት/ኢሕአዴግ ለብቻው
ያወጣውን ሕዝብን መከፋፈያ የዘር በሉት የጎሣ ፖሊሲውን አሜን ብሎ ተቀብሎ በዚያ ፖሊሲ የሚመራና የመከፋፈሉን አየር የሚያራግብ ብሎም እርስ በራሱ የሚከፋፈልና ልክ ወያኔ በሚፈልገው ዓይነት ሕዝቡን የሚከፋፍልለት የፖለቲካ ድርጅትና ማኅበራዊ ተቋም (ተቃጣይ) እስከተገኘ ድረስ በሕይወት መኖር ይችላል፡፡ ሰደድ እሣት የሚበላው ነገር ተቃጣይ (ነዳጅ) እስካገኘ ድረስ ሕያው እንደሚሆን ሁሉ ሕወሐት/ኢህአዴግም በሕይወት ሊያቆየው የሚችለውን ብቸኛ የመከፋፈል ፖሊሲሰውን ማለትም የጎሣ ፖለቲካውን ተቀብለው በሥራ ላይ የሚያውሉለት (ተቃዋሚዎችም ይሁኑ ደጋፊዎች ምንም
የሚያመጣው ለውጥ የለም) እስካሉለት ድረስ ሕያው ነው፡፡ እናም የሕወሐት/ኢህአዴግን እስትንፋስ ቀጥ ሊያደርገው የሚችለው ብቸኛ ማስራቢያው መንገድ አንድነት ብቻ ሲሆን ያ አንድነት የሚባለው ነገር ደግሞ የሕወሐት/ኢህአዴግን ፖሊሲ ወደ መቃብር መክተት የሚችል ፍፁም አንድነት መሆን ይኖርበታል፡፡ የሰደድን እሳት ለማጥፋ የተለያዩ ቴክኒኮች እንዳሉ ሁሉ ሕወሐት/ኢሕአዴግንም ለማስወገድ የተለያዩ መንገዶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ አንዱ ብዙዎች እንደሚሉት የሰላማዊ ትግሉን በማጧጧፍ ሊሆን ይችላል፡፡ ሌላው፣ በጦር መሣሪያ ትግል ሊሆን ይችላል፤ በዲፕሎማሲውም በመጠቀም ሕወሐት/ኢሕአዴግን ማስወገድ ይቻላል ብለው የሚያምኑ እንዳሉ ሁሉ በዚህም ስኬት ሊገኝ ይቻል ይሆናል፡፡ ዋናው ቁም ነገር ግን በየትኛውም መንገድ ቢሆን ስኬት ሊመጣ የሚችለው የሕዝቡን ድጋፍ
ማሸነፍ ሲቻል ብቻ ነው፡፡ አንዳንድ የዋኆች ሕወሐት/ኢህአዴግን ሕዝብ ስለሚጠላው ብቻ የሆነ አጋጣሚ ነገር ቢገኝ የሕዝብን ድጋፍ በቀላሉ ማግኘት የሚችሉ ይመስላቸዋል፡፡ በእርግጠኝነት መናገር የሚቻል ነገር ቢኖር የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዳለፈው ጊዜ በስሜት ተነስቶ እሣት ውስጥ አይገባም፡፡ የቅንጅትን ውድቀት ከዚያም ተከትሎ መሪዎቹ የፈፀሙትን የርስ በርስ መጠላለፍና
መጠፋፋት ከታዘበ በኋላ እነዚያ ሰዎች ሥልጣል ያላገኙት እግዚአብሔር ሕዝቡንና አገሪቱን ስለሚወድ በጥበቡ ያደረገው የፈጣሪ የቸርነት ሥራ እንደሆነ አድርጎ ተቀብሎታል፡፡ ከእንግዲህ በኋላ ያለፈው ዓይነት አገርንም ወገንንም የማይጥቅም ቅስም ሠባሪ ነገር ውስጥ የሚገባ አይመስልም፡፡ ስለዚህ የሕዝቡን አመኔታ፣ ድጋፍና ተሣትፎ ማግኘት የሚቻለው ባለፉት
ሃያ ሁለት ዓመታት ሕወሐት/ኢህአዴግ በአገሪቱ ላይ የጫነው የተረገመ ፖሊሲና በዚያም ሳቢያ በሕዝባችን ላይ ያደረሰውን ሰቆቃ በጭራሽ የማያስደግም፣ ታሪክን የሚያድስ፣ ፍፁም ብሔራዊ አንድነትን የሚያመጣ አካሄድን በደንብ ሲመለከትና ሲያረጋግጥ ብቻ ነው፡፡
እንዳለመታደል ሆኖ ግን ከሃያ ሁለት ዓመታት በኋላ እንኳን ገና ከእንቅልፋቸው ያልነቁ፣ ሕዝቡን እናውቀዋለን እያሉ ነገር ግን የማያውቁት፣ ሕወሐት/ኢህአዴግን ከሥልጣን ካባረሩ በኋላ ሥልጣን ጨብጠው ያንኑ የጠባብ ጎሰኝነት ለሌላ ሃያና ሰላሣ ዓመት (ከዚያም አልፎ እስከተቻላቸው ድረስ) ያንኑ የሕወሐት/ኢህአዴግን ፖሊሲ በራሳቸው መንገድ ለመቀጠል
ወረፋ ይዘው የሚጠባበቁ ብሔራዊ ፓርቲዎች በአውሮፓና በአሜሪካ ውስጥ ዘንድሮም ይገኛሉ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ግን
ቀድሞአቸው መሄዱን ገና አልተገነዘቡም፡፡ ሕዝባችን በምርጫ ዘጠና ሰባት ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ በአንድ ቃል እንደመከረ ሁሉ ድምፁን
ለቅንጅት የሰጠው እኮ ፓርቲው የኅብረ ብሔራዊ አጀንዳ ስለያዘ፣ ከጎሣ ፖለቲካ እገላግላችኋለሁ ስላለ፣ ከኦሮሞም፣ ከአማራም፣ ከትግሬም፣ ከጉራጌም…. ዥንጉርጉር ሆኖ ስለተገኘ እንጂ ሕወሐት/ኢህአዴግን ስለጠላ ብቻ አልነበረም፡፡ ቅንጅት በመላ አገሪቱ መቶ በመቶ ያሸነፈው የሕዝቡ ፍላጎት አንድ ስለነበር ነበር፡፡ በኦሮሚያ ክልልም በነፍስ ወከፍ  ተመርጧል፡፡ በዚያ ምርጫኮ ለሕወሐት/ኢህአዴግ ድምፃቸውን የነፈጉት የራሱ የሠራዊቱ አባላት ጭምር ናቸው፡፡ እንወክለዋለን የሚሉለት የትግራይ ሕዝብም ጀርባውን ነበር የሰጣቸው፡፡ ይህም የሆነው የጎሣ ፖለቲካ በስሙ በመላው
የአገራችን ሕዝብ ጫንቃ ላይ የተጫነው የትግራይ ሕዝብ የብሔር አደረጃጀትን ጥቅምና ጉዳት ስለለየና የፈየደለት ነገር አለመኖሩን አረጋግጦ እንዲያውም በሌሎች ወገኖቹ ጥላቻን ያተረፈለት መሆኑን በመገንዘቡ ነው፡፡ የትግራይ ሕዝብ የጎሣ ፖለቲካ ፖሊሲ ሐቀኛ ነጻ አውጪ ፖሊሲ ሆኖ አግኝቶት ቢሆን ኖሮ ቢያንስ ቢያንስ በክልሉ ሕወሐትን በመረጠው ነበር፡፡
ነገር ግን ሕወሐትን ያለመረጠበት ምክንያት የጎሣ ፖለቲካን ስለለካው፣ ስላየው፣ ስለበቃው፣ ስላንገሸገሸው ነበር፡፡ ሕወሐት የደርግ ተቃዋሚ በነበረበት ጊዜ የትግራይ ሕዝብ ስለ ነፃነት የተነገረውን በሙሉ አሜን ብሎ ተቀብሎ በጉያው ሸሽጎ፣ የደርግን ዱላ አሜን ብሎ እየተቀበለ፣ በጫካ ላሉት ልጆቹ ስንቅ እያቀበለ፣ በተስፋ ታግሎ ለሥልጣን አብቅቶታል፡፡ በተግባር ያየው ነገር ግን እንደጠበቀው ስላልነበርና እስኪበቃው ድረስ ስለተማረ ትክክለኛውን ነገር ለማድረግና ታሪክን ለማደስ በምርጫ 97 ከሌሎች ወገኖቹ ጋር እጅ ለእጅ ተያያዞ አዲስ ታሪክ ሠራ፡፡ ሁላችንም እናስተውል፣ ይሄ በምርጫ ዘጠና ሰባት የታየው የህዝቡ አንድነት የኢትዮጵያ ሕዝብ የጎሣ ፖለቲካን መጠየፉን እንጂ ሌላ ምንን ሊያሳይ ይችላል? ብዙዎች ግን ይህንን አይገነዘቡም፡፡ ገና በአውሮፓና በአሜሪካ ቁጭ ብለው
ሕወሐት/ኢህአዴግ ሲፈነገል በጎጥና በቋንቋ እንደተቧደኑ ወደ አገር ገብተው ሥልጣን ለመያዝ ካሁኑ ወረፋ ይዘው ቁጭ ብለዋል፡፡ የጎሣ ፖለቲካ ሕዝቡን ቋቅ እንዳለው ገና አልተረዱትምና ያሳዝናል፡፡
ሕዝባችንኮ አንዴ በትግራይ አንዴ በኦሮሞ አንዴም በሌላው ብሔር በየተራ የዘር ፖለቲካ የሚፈተንበት የቤተ ሙከራ (የላቦራቶሪ) አይጥ አይደለም፡፡ ላለፉት ሃያ ሁለት ዓመታት በሕወሐት/ኢህአዴግ የተሞከረበት አሣፋሪ ሙከራ በበቂ ሁኔታ አስተምሮታል፣ አንገሽግሾታል፡፡ ሕወሐት ኢህአዴግ ከወደቀ ወደዚያ የመመለስ ፍላጎት የለውም፡፡ ቀን እየጠበቀ ያለው ጨርሶ ለመዳን (ለመፈወስ) እንጂ በተመሳሳይ መልኩ ስሙን ብቻ የቀየረና የጎሣ ፖለቲካን ያነገበ ሌላ ጉልበተኛ በሚያመጣው ተመሣሣይ በሽታ እንደገና ለመጠቃት አይደለም፡፡ እንኳንስ ሕዝቡና ሕወሐት ራሱ በአሁኑ ጊዜ ከዚያ
ፖሊሲው እያፈገፈገ ለመሆኑ መረጃዎች አሉ፡፡ በደንብ ሳያስብበት ራሱን በትግራይ ብቻ መወሰኑ እንደጎዳው የኋላ ኋላ ስለተረዳው እርሱም የአቋም ለውጥ እያደረገ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ሌላ ጊዜ በሌላ ጽሑፍ በሰፊው እመለስበታለሁ፡፡ አና በአጭሩ ለመናገር፣ ሌላ በቋንቋ ተገድቦ የተቋቋመ የፖለቲካ ድርጅት መጥቶ ሥልጣን ላይ ከሚወጣ ከማያውቀው መልአክ ነኝ ከሚል ሌላ ጎጠኛ ድርጅት ሚያውቀውን ሠይጣን ሕወሐት/ኢህአዴግን እንደሚመርጥ ጥርጥር የለም፡፡ ስለዚህ ብሔራዊ ፓርቲዎች በተለይም ኦነግና ሌሎች በቋንቋ የተደራጁ የኦሮሞም ይሁኑ የትግራይ ወይንም የሌሎች ጎሣዎች ድርጅቶች ወደ ኅብረ ብሔራዊ አደረጃጀት ሊሸጋገሩ (ተራንስፎርም ሊያደርጉ) የግድ ነው፡፡ ያን ጊዜ ብቻ ነው የኢትዮጵያንም ሕዝብ ሐቀኛ ድጋፍ ማግኘታቸውን የሚያረጋግጡት፡፡ ያን ጊዜ ብቻ ነው ሕወሐት/ኢህአዴግ በራሱ መጥፋት የሚጀምረው፡፡ የሚራበው፣ የሚጠማው፡፡ ኦነግ ፈርሶ አባላቱ እንደየግለሰብ እምነታቸውና አስተሳሰባታቸው በሌሎች ኅብረ ብሔራዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ (ለምሣሌ አንድነት፣ ሰማያዊ ፓርቲ፣ ኢዴፓ… ወዘተ) ገብተው (ተሣግተው) ከሌላው ወገናቸው ጋር ኢትዮጵያዊነትን ብቻ መሠረት አድርገው ሲዋሀዱ ያን ጊዜ ሕወሐት/ኢሕአዴግ ወደ
መቃብሩ ይወርዳል፡፡ አዎን በቋንቋ መደራጀት ዲሞክራሲያዊ መብት ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ግን አይጠቅማትም፡፡ ሕዝቡም አይደግፈውም፣ አይፈልገውም!!! ተሞክሯል አላዋጣም!!! ተሞክሯል አክስሮታል!!! ስለዚህ በቅቶታል!!! ሕወሐት/ኢህአዴግ የዛሬ ሃያ ሁለት ዓመት ሥልጣን በያዘ ጊዜ አማራውንና ኦሮሞውን ለይተናቸዋል (ትግላችን ግቡን
መትቷል!!!) ብሎ ለመግለጽ ሲል የተናገረውን ቃል እዚህ ላይ መጥቀስ ያስፈልጋል፡፡ ”ዛቢያውን ከመጥረቢያው ለይተነዋል” ነበር ያለው፡፡ ሕወሐት በጣም የፈነደቀበት አባባል ነበር፡፡ አባባሉ ከአባባልነት
የዘለለ አለመሆኑን ግን በምርጫ 97 ላይ ተረድቶታል፡፡ ከዚያን ጊዜ ወዲህም እነሆ የበቀል ዥራፉን ገምዶ ሲያበቃ አማራውንም ኦሮሞውንም አሁን ድረስ ያለ ይሉኝታ እኩል እየሸነቆጣቸው ይገኛል፡፡
የ “ዛቢያውና የመጥረቢያው” ታሪክ ደግሞ በራሱ አንድ ሺህ አንደምታ አለው፡፡ አጠቃላይ ትርጓሜው ግን አማራውና ኦሮሞ ከተለያዩ የሕወሐት/ኢህአዴግ ዓላማ ግብ ይመታል፡፡ መልሰው ከገጠሙ ደግሞ ዓላማው ይቀለበሳል ማለት ነው፡፡  የኢትዮጵያ ሕዝብ ደግሞ የሚጠብቀውም የሚናፍቀውም ይህ እስኪሆን፣ እስኪፈፀም ድረስ ነው! ያ ቀን ሲመጣ ሕወሐት/ኢህአዴግ ወዮለት የምጽአቱ ቀን ደረሰ ማለት ነው፡፡ ያቺ የቁርጥ ቀን እንዳትደርስ ግን የተቻለውን ያህል መፍጨርጨሩ አይቀርም፡፡ ይሁንና ግን ቀኒቱን ማቅረብም ሆነ ማራቅ የሚቻለው በትናንሽ ክፍሎች ራሳቸውን
ያጠበቡበት የጎሣ ፓርቲዎች ወደው ገቡበትን የጎሣ /የቋንቋ/ ቅርፊት (ሼል) ሰብረው ወጥተው ወደ ትልቁ የአንድነት ዓለም  ውስጥ ሲገቡና ሁላችንም እንደ ጥንታችን በሰፊዋ ኢትዮጵያ ውስጥ ስንቀላቀል፣ እንዲሁም በነፃነት መንቀሳቀስ ስንችል ብቻነው፡፡ ሕወሐት/ኢህአዴግ የኢትዮጵያን ሕዝቦች እንደ ክብሪት በየትናንሽ ሳጥኖች ውስጥ አስገብቶ እንደፈለገ ሲያጓጉዝ
ኖሮአል፡፡ ሁላችንም እንደ ጥንቱ በትልቁ የኢትዮጵያዊነት ሣጥን ውስጥ ስንቀላቀል ግን ለብቻው እንደፈለገ ሊያደርገን አይቻለውም ይልቁንም ያን ጊዜ ራሱ በኛ ውስጥ ይዋጣል፡፡ ያን ጊዜ ትልቅ እሳት መፍጠር ስለምንችል እኛ ብዙዎች እንደምንፈልገው ለመሆን ይገደዳል፣ አማራጭ አይኖርም፡፡
የአጋጣሚ ጉዳይ  ይህን ጽሑፍ በዚህ ላይ አገባድጄ ባበቃሁበት ሰዓት ላይ ዳኛ ወልደ ሚካኤል መሸሻ ተስፋዬ ገብረ አብና ሻዕቢያ የተሸፈኑበትን (የተጠቀለሉበትን) መጎናፀፊያ ገፍፈዋቸው ከነነውረኛው ሥራቸው አደባባይ ማውጣታቸውን አየሁና ተገረምኩ ተደነቅሁ፡፡ ዳኛው ሰውዬ እውነተኛ የዳኝነት ሥራ ለመሥራት (ፍትሕን ለማንገሥ) የግድ ችሎት መሠየም
እምደሌለባቸው አስመስክረዋልና ጥልቅ ምሥጋና ይገባቸዋል፡፡ ከላይ ለማስረዳት የደከምኩበትን ጭብጥ ነገር ይበልጥ አጉልቶ የሚያሳይ ቁም ነገር ስላገኘሁበት ስል ብቻ ይህችን ጨምሬ
መሞነጫጨር አስፈለገኝ፡፡ በነገራችን ላይ ብዙ የተቃዋሚ ድረ ገፆች ይህን የመሰለውን ዐቢይ ዜና አልዘገቡትም፡፡ አሳዛኝ ነው!!! ምክንያታቸውም ሻዕቢያን ላለማስቀየም ነው፡፡ ሻዕቢያ ከተቀየመ በኤርትራ ምድር የሚደረገው የተቃውሞ እንቅስቃሴ ሣንካ ይገጥመዋል፡፡ ስለዚህ በተቻለ መጠን ዘገባው እንዳይዘገብ በሆነ ኃይል ጥረት ተደርጓል፡፡ አይ ፖለቲካ!!!!
የኢትዮሚዲያ ድረ ገፅ ግን በእጅጉ ሊመሰገን ይገባዋል፡፡ የተስፋዬ ገብረ አብ ተንኮል የተጋለጠው በእግዚአብሔር ጥበብ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ትንሣዔ መቃረቡን አመላካች ነው፡፡
ምክንያቱም የአማራውና የኦሮሞው መለያየት ለሻቢያና ለወያኔ ምን ያህል አስፈላጊ ነገር እንደሆነ የምናረጋግጥበት ነገር ስለሆነ ነው፡፡ ነገሩን በጥሞና ተመልከቱት፤ የሁለቱ ወንድማማች ሕዝቦች (የአማራውና የኦሮሞው) አንድነት እንኳንስ ለሕወሐት/ኢሕአዴግ ለሻዕቢያ ህልውና ፀር መሆኑን እንመለከታለን፡፡ የጎሣ ፖለቲካን በኢትዮጵያ ማሰፈን ያስፈለገው
ሁለቱን ሕዝቦች ለመለያየት ሲባል ብቻ ለመሆኑ ከዚህ የበለጠ የሚጨበጥና የሚዳሰስ ግዙፍ ማስረጃ የለም፡፡ እነዚህ ሁለት ሰይጣኖች ፕላናቸውን በተግባር ለማዋልና ለስኬት ሊበቁ የቻሉትም ከራሳችን ከአማራና ከኦሮሞ አብራክ በወጡ ጥቂት ሆዳሞች መሣሪያነት ለመሆኑ እነ ሌንጮና ታምራት ላይኔ ጥሩ ናሙናዎች ናቸው፡፡ ነገሬን ለመጠቅለል ያህል በኢትዮጵያ ውስጥ ይታዩ የነበሩትን ጥቃቅን ችግሮችን በተንኮል እያገዘፉ፣ ያልሆነ መልክና ቅርጽ  እየሰጡ ሁለቱን ሕዝቦች (አማራውንና ኦሮሞውን) ለማጣላት ብለውም አማራው ከያለበት ተጋብቶና ተዋልዶ ይኖር ከነበረበት የኦሮሞ ቀዬ ሁሉ እየተቀጠቀጠ እንዲሰደድ ያደረጉ ሻዕቢያና ሕወሐት የራሳቸውን ፕሮግራም ለማስፈፀም እንጂ ለኦሮሞ ሕዝብ ተቆርቁረው፣ አዝነው እንዳልነበረ ዛሬ በሚገባ ሊረዱ የግድ ነው፡፡ ከዚህ መማር ያለብን እውነት ቢኖር
ያለፉት ሃያ ሁለት ዓመታትና ከዚያ በፊት በነበረው 17 – 30 የሚገመቱት በነፃነት ስም የተሰዉ ዓመታት በእውነት ለነፃነት የተደረጉ ሳይሆኑ ሻዕቢያና ሕወሐት ከኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር ተሰልፈው የውሸት ታሪክ እየፈጠሩ ሕዝብን ከሕዝብ (በተለይም አማራውን በሌላው ሕዝብ እንዲጠላ) ለማናቆርና የየራሳቸውን ኢትዮጵያን የማጥፋት ዓላማ ለማሳካት ድራማ የሠሩበት (ሕዝቡን ቁጭ በሉ የሠሩበት) ጊዜ እንደነበር ነው፡፡ ኦሮሞው የቅኝ ገዥዎችን ፊደል (ላቲንን ወይንም ቁቤን) ከአገሩ ተወላጅ ቋንቋ ከግዕዝ በላይ መርጦ መገልገያ እንዲያደርገው የተደረገበት ምክንያቱ ሁሉም ሊገነዘበው ያሻል፡፡ የቅኝ ገዢዎቹ የላቲን ፊደል በኦሮሞውና በአማርኛ ቋንቋ ተገልጋዮች መካከል ጥላቻን በከባዱ ያሰፍን ዘንድ ሆን ተብሎ የተቀመመ መርዝ መሆኑን ልብ ልንል ይገባል፡፡ በዚህ ጉዳይም በሌላ ጽሑፍ በሰፊው እመለሳለሁ….. ሕወሐቶች ኦሮሚያ ብለው በከለሉአቸው ቦታዎች አማሮች በገደል እንዲወረወሩ እያስደረጉ በነበረ ጊዜ ትዕይንቱን በቪዲዮ
እየቀረፁ ለሌላ ወጥመድነት ያስቀምጡ እንደነበር ማወቅ ግዴታችን ነው፡፡ ዳኛ ወ/ሚካኤል ከሰሞኑ ያቀረቡልን ይህ በመረጃ የተጠናቀረ ዜና ኦሮሞውና አማራው ለምን እንደ ጥንቱ ተመልሰው መዋሀድ እንደሚገባቸው እጅግ በጣም ትልቅ ነጥብ ሰጥቶኛልና በድጋሚ ዳኛውን ላመሰግን እወዳለሁ፡፡
እንኳንስ ኦሮሞውና አማራው፣ ኢትዮጵያና ኤርትራ የተለያዩት በሕዝቦቻቸው ፍላጎት ወይንም እነ ሻዕቢያ እንደሚናገሩት እርትራን ከኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት ነጻ ለማውጣት አይደለምና ሥር ነቀሉን የአቋም ለውጥ ማምጣት ከሐዲዱ የወጣውን  የኢትዮጵያን ታሪክ ወደ ሥፍራው ለመመለስ ሊደረግ የሚገባው ሂደት ዋነኛ ክፍል ነው፡፡ ተስፋዬ ገብረአብ ለአዲሱ
የኤርትራ ወጣትና ለመጪው ትውልድ ጽፎ ሊያስቀምጥ የሚፈልገው የፈጠራ ታሪክ ተመሳሳዩ በኢትዮጵያ ውስጥ ወያኔ የትምህርት ካሪኩለም ቀርፆለት ለአዲሱ ትውልድ በመደበኛ የትምህርት ገበታ ላይ በሰፊው ተሰጥቶአል፡፡ እየሰጠውም  ይገኛል፡፡ አዲሱ ትውልድ ስለ ኢትዮጵያ ቅኝ ገዢነት፣ ስለ አማራው ጨቋኝነት፣ ስለ ኦሮሞው ተጨቋኝነት፣ ስለ ሕወሐት
ጀግንነትና ቅድስና፣ ስለ ደርግ አውሬነት፣ ስለ መቶ ዓመት ታሪካችን.. ወዘተ በሰፊው እንዲማር ተደርጓል፡፡ በአንፃሩ አማርኛ፣ አንድነት፣ ባንዲራ የመሳሰሉት የኢትዮጵያዊነት መገለጫዎ እሴቶቻችን እንዲቀጭጩና እንዲጠፉ ጠንካራ ፖሊሲ ነድፎ በተግባር ላይ አውሏል፡፡
ስለዚህ በብሔር የተደራጃችሁ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሁላችሁም የሕዝቡን ስሜት ጠይቃችሁ ተረዱ፣ ከዚያም በኢትዮጵያዊነት ብቻ መሥፈርት ተደራጅታችሁ የማይቀረውን የትንሣዔ ትግል ተቀላቀሉ፡፡ ይህን እንድታደርጉ የኢትዮጵያ
አምላክ ይርዳችሁ፡

No comments:

Post a Comment