Wednesday, October 16, 2013

የአስተዳደሩ ምርመራና ክስ ኤክስፐርት በቁጥጥር ሥር ውለው ፍርድ ቤት ቀረቡ


-በቦሌ ጉምሩክ ኃላፊና በአንድ ባለሀብት ላይ የተዘጋጀው ክስ ሳይነበብ ቀረ

በዋና ወንጀል አድራጊነት በፈጸሙት በሥልጣን ያላግባብ መገልገል የሙስና ወንጀል ክስ ተመሥርቶባቸው፣ በማረሚያ ቤት በሚገኙት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት

አስተዳደርና ግንባታ ፈቃድ ባለሥልጣን በነበሩት አቶ ቃሲም ፊጤ መዝገብ፣ በሌሉበት ክስ ተመሥርቶባቸው የነበሩት፣ የአስተዳደሩ ፍትሕ ቢሮ የምርመራና ክስ ኤክስፐርት አቶ ተስፋዬ ዘመድኩን በቁጥጥር ሥር ውለው ጥቅምት 4 ቀን 2006 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ቀረቡ፡፡
የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ዓቃቤ ሕግ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አንደኛ ወንጀል ችሎት ክስ የተመሠረተባቸው አቶ ቃሲም ፊጤ፣ አቶ ተስፋዬ ዘመድኩን፣ የሊዝ አሰባሰብ ክትትል ኦፊሰር አቶ ገብረየሱስ ኪዳኔና የመሬት አቅርቦት አፈጻጸም ንዑስ የሥራ ሒደት አቶ በቀለ ገብሬ መሆናቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ 
ሦስቱ ተከሳሾች ሐምሌ 29 ቀን 2005 ዓ.ም. የተጻፈ ክስ ቀርቦባቸውና ተነቦላቸው የዋስትና መብታቸው በመከልከሉ፣ ማረሚያ ቤት ቆይተው ጥቅምት 4 ቀን 2006 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ቀርበዋል፡፡ 
ከሦስቱ ተከሳሾች በተጨማሪ በሌሉበት ክስ ተመሥርቶባቸው የነበሩት አቶ ተስፋዬ አብረው በመቅረባቸው ቀደም ብሎ የተመሠረተው ክስ ተነቦላቸዋል፡፡ የዋስትና መብታቸውም ታልፎ በማረሚያ ቤት ሆነው ክሳቸውን እንዲከታተሉ ፍርድ ቤቱ በጽሕፈት ቤት በኩል ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
ከአቶ ተስፋዬ በስተቀር ሦስቱ ተከሳሾች ለጥቅምት 4 ቀን 2006 ዓ.ም. ተቀጥረው የነበሩት የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ የቅድመ ክስ መግለጫ እንዲያቀርብ የነበረ ቢሆንም፣ አቶ ተስፋዬ ተይዘው በመቅረባቸው ክሱ እንደ አዲስ ተነቦላቸው በሁሉም ላይ የቅድመ ክስ መግለጫ ለማቅረብና ተከሳሾች በጠየቁት የዋስትና መብት ላይ ብይን ለመስጠት ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡
ሌላው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጥቅምት 4 ቀን 2006 ዓ.ም. ከገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ ኃላፊዎች፣ ሠራተኞችና ነጋዴዎች ጋር በቁጥጥር ሥር ውለው በነበሩት በባለሥልጣኑ ቀድሞ የቦሌ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዮሴፍ አዳዩና በተለያዩ ንግድ ሥራዎች ላይ የተሰማሩት አቶ ማሞ ኪሮስ ላይ የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ክስ አዘጋጅቶ የመጣ ቢሆንም፣ ፍርድ ቤቱ በእድሳት ላይ በመሆኑ ዳኞች ቀድሞ ይሠሩበት ከነበረው ችሎት ወደ ሌላ ችሎት በመቀያየራቸውና ሳይሟሉ በመቅረታቸው ሳይነበብ ቀርቷል፡፡ 
አቶ ማሞ ኪሮስ ሐሰተኛ ሰነድ በማዘጋጀትና በተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች ተሳትፈዋል በሚል መጠርጠራቸውንና አቶ ዮሴፍ አዳዩ በሥልጣን ያላግባብ መገልገል፣ ፈቃድ የሌለው የጦር መሣሪያ ይዞ በመገኘትና በሌሎችም ወንጀሎች መጠርጠራቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ 
ethiopian reporter

No comments:

Post a Comment