Thursday, February 6, 2014

ሰውነት ቢሻው፣ የኢትዮጵያ እግርኳስ እና አጨዋወት

ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝነታቸው የተሰናበቱት ሰውነት ቢሻው
ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝነታቸው የተሰናበቱት ሰውነት ቢሻው
በሶስተኛው የአፍሪካ ሀገሮች እግርኳስ ሻምፒዮና (ቻን) የተሳተፈው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በምድብ ሶስት ውስጥ ካደረጋቸው ሶስት ጨዋታዎች በሁሉም ተሸንፎ፣ አራት ጎሎች ገብቶበት እና አንድም ጎል ሳያስቆጥር ያለምንም ነጥብ ከምድቡ የመጨረሻ ደረጃን ይዞ ከሻምፒዮናው መሰናበቱ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በሀገር ውስጥ ክለቦች በሚጫወቱ ተጨዋቾች ብቻ የተገነቡ ብሄራዊ ቡድኖች ወደተሳተፉበት የአፍሪካ ሀገሮች ሻምፒዮና (ቻን) ውድድር ላይ ለመካፈል ወደ አስተናጋጇ ሀገር ደቡብ አፍሪካ ሲሄድ ለዋንጫ ባለቤትነት የገመቱት በርካቶች ነበሩ። ምክንያታቸው ብሄራዊ ቡድኑ በብራዚል አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የአለም ዋንጫ ለማለፍ በተካሄዱት የማጣሪያ ጨዋታዎች ላይ ባሳየው ብቃት እና አብዛኞቹ የቡድኑ ተጨዋቾች በሀገር ውስጥ ሊጎች የሚጫወቱ በመሆናቸው ቡድኑ ከአለም ዋንጫ ማጣሪያው ብሄራዊ ቡድን ጋር ተመሳሳይነት ስለነበረው ነው።
ሻምፒዮናው ከተጀመረ በኋላ ግን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በምድቡ አብረውት ከተደለደሉት ሊቢያ፣ ኮንጎ ብራዛቪል እና ጋና ብሄራዊ ቡድኖች ጋር ያሳየው የጨዋታ እንቅስቃሴ እና ያስመዘገባቸው ውጤቶች እንደተጠበቀው ለዋንጫ ባለቤትነት የሚያስጠብቁ ሳይሆኑ በጣም ደካማ እንቅስቃሴዎች ነበሩ።
አሰልጣኝ ሰውነት ቡድናቸው ለምን ጎል ማግባት እንደተቸገረ ሲጠየቁ ከሀገር ውጪ በሚገኙ ክለቦች የሚጫወቱት ሳልሀዲን ሰኢድ፣ ጌታነህ ከበደ እና ሽመልስ በቀለን የመሳሰሉ ቋሚ የብሄራዊ ቡድኑ ተጨዋቾች የቻኑ ብሄራዊ ቡድን ውስጥ አለመኖርን በተደጋጋሚ እንደምክንያት ቢያስቀምጡም በአጠቃላይ በሻምፒዮናው ላይ የተሳተፉት ብሄራዊ ቡድኖች ወሳኝ የሚባሉ ተጨዋቾቻቸውን (አንዳንዶቹ ሙሉ ለሙሉ) ሳይዙ ለሻምፒዮናው እንደመጡ ረስተውት ነው ወይ የሚያስብል ጥያቄን የሚያስነሳ ነበር።
በርግጥ የቻንን ውጤት እንደዋና መነሻ በማድረግ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻውን ለሁለት አመት ያህል በዋና አሰልጣኘት ከያዙት ብሄራዊ ቡድን ሀላፊነታቸው አሰናብቷቸዋል።
አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ምንም እንኳን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን ለአፍሪካ ዋንጫ ማሳለፍ እና ለአለም ዋንጫ ማጣሪያ ጥሎ ማለፍ ጨዋታ እንዲደርስ ቢያበቁትም ቡድኑ የሚከተለው የአጨዋወት ስታይል፣ የተጨዋቾች አመራረጣቸው፣ ከብሄራዊ ቡድኑ ጋር በተያያዘ በጋዜጣዊ መግለጫዎች እና በቃለ-መጠይቆች ወቅት የሚሰጧቸው የተዘበራረቁ አስተያየቶች ከተለያየ አቅጣጫ ትችቶችን ያመጡባቸው ክስተቶች ነበሩ።
የኢትዮጵያ እግርኳስ እና አጨዋወት
በዚህ ጽሁፌ እንደአስተያየት ማስቀመጥ የምፈልገው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በሰውነት ቢሻውም ሆነ ከሳቸው በፊት በነበሩት አሰልጣኞች ዘመን እኔ እግርኳስን ማየት ከጀመርኩበት ጊዜ አንስቶ የታዘብኩት የአጨዋወት ዘይቤን መነሻ በማድረግ ነው።
ኢትዮጵያዊያን የእግርኳስ ተጨዋቾች አብዛኞቹ አጨዋወታቸው ኳስን በመያዝ እና በአጭር ኳስ ቅብብል ላይ የተመሰረተ እንቅስቃሴ እንደሆነ በተለያየ ደረጃ ያሉ የሀገሪቷ ቡድኖች ያደረጓቸውን ጨዋታዎች በተለያየ አጋጣሚ እና መንገድ ያየ የሚያውቀው ነው።
ይሄንን አጨዋወት መነሻ በማድረግ ለረጅም ጊዜ በባለሞያዎች እና በስፖርቱ አፍቃሪ በተደጋጋሚ ከሚሰጡት አስተያየቶች መካከል ዋናዎቹ “ለምን ይሄንን አጨዋወት አንቀይርም?” የሚለው እና “ለምን ያለንን ችሎታ በደንብ አወቀን ያንን ችሎታችንን የበለጠ አናዳብረውም?” የሚሉት ናቸው።
በአፍሪክ ዋንጫ ጎል ያገባው አዳነ
በአፍሪክ ዋንጫ ጎል ያገባው አዳነ
በተለይ በደቡብ አፍሪካ አስተናጋጅነት በተካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አልፎ አልፎ ያሳያቸውን ፈጣን አጭር ቅብብል ጨዋታዎች የተመለከቱ የውጪ ሀገር ባለሞያዎች ለብሄራዊ ቡድኑ አድናቆታቸውን የገለጹ ሲሆን በአዲ አበባ ስታዲዬምም ሆነ በተለያዩ የክልል ከተሞች የኢትዮጵያ ቡድኖች የሚያደርጓቸውን ጨዋታዎች ለረጅም ጊዜ ሲከታተል የቆየው የስፖርት አፍቃሪ ግን (እኔን ጨምሮ) በዚህ አስተያየት አልተገረመም ነበር። ምክንያቱም እድሜ ልካችንን ስናየው የነበረው አጨዋወት ነበር እና ነው። የሀገሪቷ ቡድኖች በውጪ ቡድኖች ተሸንፈው ከውድድር ሲወጡ በአብዛኛው ከአፋችን ይወጣ የነበረው አስተያየት “ጥሩ እኮ ተጫውተን ነበር፤ ግን ውጤት እንቢ አለን” የሚለው ነው።
ብሄራዊ ቡድኑ ከዛምቢያ ጋር በአፍሪካ ዋንጫው ያደረገውን ጨዋታ አይተው አድናቆታቸውን የገለጹት የውጪ ዜጎች እና በሀገር ፍቅር ስሜት ብሄራዊ ቡድን ስለሆነ ብቻ እግርኳስን መከታተል የጀመሩት “አዲስ” ኢትዮጵያዊያን ተመልካቾች አድናቆታቸውን ያጎረፉለት ለረጅም ጊዜ የኢትዮጵያን እግርኳስ ለማየት ባለመታደላቸው ነው።
በደቡብ አፍሪካ አስተናጋጅነት በተካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ እና በቅርቡ በተጠናቀቀው የቻን ሻምፒዮና ላይ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ኳሱን ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣጠር ችሏል ከማለት ይልቅ አልፎ አልፎ ብልጭ ብለው በሚጠፉ አጋጣሚዎች ብቻ ኳሱን በበላይነት ከመቆጣጠሩ በተጨማሪ ያ ቁጥጥሩ የነበረው የራሱ ሜዳ ላይ ብቻ በመሆኑ እና ያንን የበላይነት ወደተጋጣሚ ሜዳ ይዞት ባለመሄዱ እና ተግባራዊ ለማድረግ አለመቻሉ ደካማነቱን የበለጠ አጉልቶታል።
እ.አ.አ በ1907 ዓ.ም የእንግሊዙ ኖርዝሀምተን ክለብ አሰልጣኝነት የተረከቡት ኸርበርት ቻፕማን በጊዜው “እግርኳስ ጨዋታን ለማሸነፍ ኳስን በቁጥጥር ስር ማድረግ ብቻ በቂ አይደለም፤ ኳሱን የት እንደተቆጣጠርከው እና የተቆጣጠርክበት ሁኔታዎች ወሳኝነት አላቸው” በማለት የተናገሩት ለምን የኢትዮጵያ ተጨዋቾች በደቡብ አፍሪካው የአፍሪካ ዋንጫ እና በሌሎች ሻምፒዮናዎች ኳሱን ቢቆጣጠሩም ያንን ቁጥጥራቸውን ወደውጤት መቀየር በተደጋጋሚ እንደተቸገሩ ፍንጭ የሚሰጥ ነው።
የቀድሞው የስዋንሲ ሲቲ ክለብ አሰልጣኝ እና በአለም እግርኳስ ውስጥ በተጨዋችነት በታላቅነታቸው ከሚደነቁት መካከል አንዱ የሆነው ዴንማርካዊው ማይክል ላውድሮፕ በተደጋጋሚ ሲል እንደሚሰማው ኳስን መቆጣጥር ብቻ ሳይሆን ዋናው መታየት ያለበት ኳሱን የት እና እንዴት ተቆጣጠርከው የሚለው ነገር ነው።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንም ሆነ ክለቦች በተደጋጋሚ ከውጪ ከመጡ ቡድኖች ጋር በተለያዩ ሻምፒዮናዎች ላይ ሲሳተፉ ሜዳ ላይ አልፎ አልፎ ኳሱን በፈጣን የአጭር ቅብብል ለመቆጣጠር ቢችሉም ያ ቁጥጥራቸው ግን በአብዛኛው የተጠና ሀሳብ እና አካሄድ እንደሚጎለው ይሰሩ ከነበሩት ስህተቶች መረዳት ይቻላል።
ምንም እንኳን አንዳንዶች ኳስ የያዘው ሰው የሚሰራውን ስህተት በማየት ኳሱን ያበላሸውን ሰው በተደጋጋሚ ለመተቸት ሲሞክሩ ቢታይም መተቸት የነበረበት ግን ኳሱን ላለመቀበል የሚሸሸጉት እና ያንን አጨዋወት ተግባራዊ እንዲሆን ታክቲኩን ወይም የአጨዋወት ዘዴውን የመረጠው አሰልጣኝ ነው። እናም ለምን ያንን አደረክ ብሎ አሰልጣኙን መጠየቅ ምኑ ላይ ነው ስህተቱ?
በርግጥ እግርኳስ እንዲህ በቀላሉ “ይሄ መሆን አለበት፣ ይሄ መሆን የለበትም” በማለት የሚተነተን ስፖርት አይደለም። ለዚህም በ1980 ዎች መጨረሻ እና በ1990 ዎቹ መጀመሪያ የአለም እግርኳስን ተቆጣጥሮ የነበረው የጣሊያኑ ኤሲ ሚላን ክለብን የገነቡት ታላቁ አሰልጣኝ አሪጎ ሳኪ “እግርኳስ በጣም የተወሳሰበ ስፖርት ነው” ያሉት።
አሪጎ ሳኪ ይህ አባባላቸውን እንዲህ ይተነትኑታል -
“ስታጠቃ በተጨዋቾችህ መሀል ያሉት ርቀቶች ትክክለኛ መሆን አለባቸው። ጊዜ አጠባበቅህ እና አጠቃቀምህ ልክ ሊሆን ይገባል። የያዘህን ተጨዋች ማስለቀቂያ ትክክለኛ መንገድ ሊኖርህ ይገባል። እነዚህ ነገሮች ከሌሉህ የምትጫወተው እግርኳስ ፍሰት አይኖረውም። ብዙውን ጊዜ ቡድኖች ቡድን ከመሆን ይልቅ ዝም ብለው የተጨዋቾች ስብስብ ሆነው ይቀሩና በአንድነት መንቀሳቀስ ሲቸገሩ ታያለህ” ያሉት።
ሁሉም የእግርኳስ ቡድኖች ከሳሞአ ብሄራዊ ቡድን እስከ ስፔን ብሄራዊ ቡድን፤ በሰፈር ውስጥ ከሚጫወቱ ቡድኖች እስከ ግዙፎቹ ባርሴሎና፣ ባየርን ሙኒክ፣ ማንቼስተር ዩናይትድ፣ ሪያል ማድሪድ ድረስ ተመሳሳይ አይነት ፍላጎት አላቸው። ጠንካራ ቡድን መሆን እና እንደ ቡድን መጫወት።
አሪጎ ሳኪ ይሄንን ቡድን የመሆን ፍላጎትን እና ቡድን መሆንን አስመልክተው ሲያስረዱ፦
“ምን አልባት ቡድን የመሆን እና በቡድን የመንቀሳቀስ ፍላጎት ሊኖር ይችላል። ፍላጎት ብቻውን ግን በቂ አይደለም። ስብስብን ወደ ቡድን የሚቀይረው ጨዋታ/አጨዋወት ነው። የምትከተለው የአጨዋወት ዘዴ ደግሞ በምታጠቃበትም ሆነ በምትከላከልበት ጊዜ ፍሰት ኖሮት ሊሰራ ይገባዋል። ይሄንን ለማብራራት ያህል ሁልጊዜም ቢሆን በመሀላቸው ሰፊ ርቀት ሳይኖር አብረው/ተጠጋግተው የሚንቀሳቀሱ ተጨዋቾች የተሰራ ቡድን ለሚፈጠሩበት ፈተናዎች በቀላሉ መልስ የማግኘት እድሉ ሰፊ ነው።
“አብረው ስል ተጠጋግተው (compact) ማለቴ ነው። ይሄን አይነት አጨዋወት የሚከተል ቡድን ኳሱን ቢነጠቅ እንኳን ቢበዛ 10 ሜትሮችን ብቻ ለነጠቃ ስለሚሮጥ 20 እና 30 ሜትሮች በመሮጥ የምታቃጥለውን ሀይል ያህል እንዳታቃጥል ያደርግሀል። ምክንያቱም እዛው አብረህ ኳሱን የነጠቀህ ቡድን ላይ ጫናን እንድትፈጥር እና መፈናፈኛ እንድታሳጣው ያደርግሀል። በምታጠቃበት ጊዜ ደግሞ የቡድን አባሎችህ አጠገብህ ስለሚገኙ ኳስን ለማቀበል ብዙ አማራጮች እንዲኖርህ ያደርጋሉ። ምክንያቱም ሁልጊዜም እንቅስቃሴ ላይ በመሆናችሁ። እነዚህ ናቸው እንግዲህ ተግባቢነት ባላቸው ተጨዋቾች በተገነባ ቡድን እና በተጨዋቾች ስብስብ የተገነባ ቡድን መካከል ያሉ ዋና ልዩነቶች።”
በአፍሪካ ዋንጫው ላይ እና በአለም ዋንጫ ማጣሪያው ወቅት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በአብዛኛው ሳልሀዲን ሰኢድን ፊት ላይ አቁሞ ኳስን በረጅሙ እየጠለዘ ሲጫወት እና ኳሱም ተመልሶ ራሱ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ላይ ጫናን ሲፈጥር ነበር በተደጋጋሚ የታየው። ታዲያ ያ ተመልሶ የመጣ ኳስ ድንገት ከተቆጥረ ጨዋታውን በቴሌቪዥን የሚያየው አብዛኛው ተመልካች በረኞችን ሲተች በተደጋጋሚ ይሰማ ነበር። ግን እስከመቼ ነው በረኛን እየሰደብን፣ በቀጥታ በአይን የሚታዩ ስህተቶችን ብቻ የሰሩ ተጨዋቾችን እየተቸን የምንኖረው።
በኢትዮጵያ እግርኳስ ውስጥ በረኞችን መተቸት ምን አልባትም ባህል ሆኗል ብል እያጋነንኩ አይደለም። በርግጥ በረኞቻችን ሙሉ ለሙሉ መተቸት የለባቸውም እያልኩ አይደለም። በረኛው ሊያከሽፍው የሚችለው ኳስ ሲገባ እና ሌሎች እሱ መስራት የሌለባቸውን ስህተቶች ሲሰራ ከታየ መተቸት አለበት። እነዚህ ሁኔታዎች የሚከሰቱት ግን በጣም በጥቂት አጋጣሚዎች ነው።
ዋናው ትኩረት መደረግ ያለበት ኳሱ እንዴት በረኛችን ጋር ደረሰ፣ ለምንስ ከበረኛው ፊት የቆሙት ተከላካዮች፣ አማካዮች እና አጥቂዎች ኳሱን በረኛው ጋር ከመድረሱ በፊት ሊያቆሙት አልቻሉም? ለምንድነው ተጨዋቾች ኳሱ በቁጥጥራቸው ስር እያለ ይዘውት በመጫወት ቀዳዳዎችን ከመፈለግ ይልቅ ያንን ኳስ እየጠለዙ ተጋጣሚያቸው በአካል ብቃት ለሚበልጣቸው ተጨዋቾች ሁኔታዎችን ቀላል የሚያደርጉላቸው?
ተጨዋቾችን የመረጡት እና ሜዳ ውስጥም ገብተው የሆነ አጨዋወትን ተግባራዊ እንዲያደርጉ የሚያደርጓቸው አሰልጣኞች ናቸው። ለምንድነው የተነደፈው አጨዋወት ዘዴ ሲበላሽ አሰልጣኞች የማይተቹት? ለምንድነው ግለሰብ ተጨዋቾች ለቡድን ውጤት ሁልጊዜ የትችት ማምለጫ ተደርገው የሚወሰዱት? እስከመቼ አብዛኞቹ አንጋፋ አሰልጣኞቻችን የሚታይ ስህተቶችን ከሰሩ ተጨዋቾች ጀርባ ተደብቀው እያጭበረበሩ ይኖራሉ?
ኢትዮጵያዊያን ተጨዋቾች በተፈጥሮ የግል ኳስ ችሎታቸው ከማንም አያንሱም። ታዲያ ለምን ቡድን ሆነው ሲመጡ ወይም ሜዳ ላይ ሲገቡ ከተጋጣሚዎቻቸው አንሰው ይገኛሉ? መልሱ አንድ እና አንድ ነው – የሚከተሉት የአጨዋወት ዘዴ። ያንን የአጨዋወት ዘዴ የሚነድፈው ማነው? አሰልጣኙ። ያ አሰልጣኝ የነደፈው የአጨዋወት ዘዴ መነሻው ማንን ያደረገ ነው? ተጋጣሚ ቡድንን ወይስ ራሱን?
ተጋጣሚ ቡድንን መሰረት አድርገው ቡድናቸውን የሚሰሩ አሰልጣኞች ያላቸው ችግር ምንድነው? የራሳቸው ልጆች ያላቸውን ችሎታ ይተዉና ተጋጣሚ ቡድን እንዲጫወቱ እንደሚፈልገው ይጫወታሉ። ታዲያ ያ ሲስተም ሲበላሽ እና ውጤት ሲጠፋ አሰልጣኞች ስህተት የሰራውን ተጨዋች ይተቹና ራሳቸውን ከትችት ነጻ ለማውጣት ይሞክራሉ።
ኢትዮጵያዊያን ተጨዋቾች በአብዛኛው ኳሱን ቢችሉትም የታክቲክ ችግር እንዳለባቸው ይነገራል። እነዚህ ታክቲካል ዲሲፕሊኖች ኳስን ለመቀበል ወደክፍት/ባዶ ቦታ መሮጥ፣ የሜዳውን ስፋት እና ርዝመት ግምት ውስጥ አስገብቶ የሚቆምባቸውን ቦታዎች ማወቅ፣ ከቡድን አባል ጋር መቀናጀት፣ ኳሱን ለመቀበል ክፍት ቦታዎች ላይ መገኘት፣ በራስ እና በተጋጣሚ ሜዳ ላይ ኳስን በበላይነት መቆጣጠር፣ እንቅስቃሴዎችን ኳስ እግር ስር ከመግባቷ በፊት ቀድሞ ማንበብ፣ መቼ ኳስን ማቀበል እና በግል እያንከባለሉ መሄድ እንዳለባቸው ትክክለኛ እርምጃን መውሰድ፣ ኳስን ለጓደኛ ሲያቀብሉ እና ሲያንከባልሉ ከተጋጣሚ ቡድን ተጨዋች እይታ/ንባብ መሸፈን፣ የተጋጣሚ ቡድን ሊጠቀምበት የሚችለውን አደገኛ ቦታ እና ሰው መከላከል እና መሸፈን የሚሉት በዋናነት የሚጠቀሱ የታክቲክ ስርአቶች በኢትዮጵያ እግርኳስ ቡድኖች ላይ በተደጋጋሚ የሚታዩ ታሪካዊ ችግሮች ናቸው።
እናም እነዚህን ታሪካዊ ችግሮች በስልጠና የሚገኙ በመሆናቸው፣ እነዚህን አሻሽሎ ተጨዋቾቹ በተፈጥሮ ከታደሏቸው ችሎታዎች ጋር በማዋሀድ ለተሻለ ውጤት መስራት ነው እንጂ አንድ ሰው ትችት የሚመስል አስተያየት በሰነዘረ ቁጥር “ከ31 አመታት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ ያለፍነው” በማለት ድፍን ባለ ሁኔታ አስተያየቶችን መደምሰስ ለማንም አልጠቀመም። አይጠቅምም።
ከዚህ በኋላ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻውን ተክቶ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ የሚሆንውም (ከውጪም መጣ ከሀገር ውስጥ) እየተደነቀ እና እየተተቸ ስራውን መስራቱን ይቀጥላል። እግርኳስን አስደሳች የሚያደርገው ነገር ጥበበኛ ተጨዋቾቹ እና ወበት ያለው ጨዋታን የሚጫወቱት ቡድኖች ብቻ ሳይሆኑ፣ እያንዳንዳችን እንደይታችን የራሳችን አስተያየቶች እንዲኖረን ማድረጉ ነው።

No comments:

Post a Comment