Monday, December 16, 2013

በደቡብ ሱዳን የተደረገው መፈንቅለ መንግስት መክሸፉን የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ተናገሩ

በደቡብ ሱዳን የተደረገው መፈንቅለ መንግስት መክሸፉን የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ተናገሩ የአዲሲቷ አገር መሪ የሆኑት ሳልቫኪር የቀድሞው ምክትል ፕሬዚዳንት ሪክ ማቻር ታማኝ ወታደሮች መፈንቅለ መንግስት ለማድረግ ሌሊቱን ተኩስ መጀመራቸውን ተናግረዋል። ችግሩ በቁጥጥር ስር መዋሉን የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ እንዲህ አይነቱን ድርጊት
እንደማይታገሱትና ሙከራውን ባደረጉት ላይ ሁሉ አስፈላጊውን ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስዱ ተናግረዋል። የአገሪቱ ቴሌቪዥን ከጠፋ ከሰአታት በሁዋላ እንደገና ስራ ጀምሯል። እስካሁን ድረስ ምን ያክል ሰዎች እንደሞቱ አልታወቀም። በደቡብ ሱዳን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለኢሳት እንደገለጹት 1 ኢትዮጵያዊ በተኩሱ ልውውጥ ተገድሏል። በደቡብ ሱዳን ከ50 ሺ ያላነሱ ኢትዮጵያውያን እንዳሉ ይነገራል። አንዳንድ ታዛቢዎች ግጭቱ ሊቀጥል ይችላል ይላሉ። በዲንቃና ንዌር ጎሳዎች መካከል ያለው የቆየ ፉክክር ለአሁኑ ግጭት መነሳት ምክንያተ ነው ተብሎአል። ፕሬዚዳንቱ ከዲንቃ ሲሆኑ፣ ምክትላቸው የነበሩት ደግሞ ንዌር ናቸው። ፕ/ት ሳልቫኪር የራሳቸውን ጎሳ አባላት ወደ ስልጣን በማምጣት ሀይላቸውን እያጠናከሩ የሚል ትችት በተቃዋሚዎቻቸው ይቀርብባቸዋል።

No comments:

Post a Comment