Wednesday, July 31, 2013

መረጃ በጨዋታ፤ በዱባይ ኤንባሲያችን ሆኗል አሉ “ገዳይ”

burj_khalifa_aka_burj_dubai-wide

መረጃ በጨዋታ፤ በዱባይ ኤንባሲያችን ሆኗል አሉ “ገዳይ”
ዱባይ ሆይ የእህቶቻችን ሀገር እንደምን ነሽ… ለመሆኑስ እህቶቻችንን እንዴት ናቸው…በሻርጃ እና አቡዳቢ ጉያዎችሽ የደበቅሻቸው ጎረምሶችሽ በዚህ ሰዓት ምን እያሏቸው ይሆን… “ማዳሞችሽስ” ስንቷን የሀገሬ ሴት እየገላመጡ ስነቷንስ እያመናጨቁ ይሆን…
በፌስ ቡክ የመልዕክት ሳጥኔ አንድ መልዕክት መጣ፡፡ እንዲህ ይላል “በዱባይ ኤንባሲያችን እየሆነ ስላለው ነገር ልነግርህ ነበር” እኔስ ማነኝ፤ እስቲ አምጪው አልኳታ፤
በዩናይትድ አረብ ኢምሬት ዱባይ ኢትዮጵያ ኤንባሲ አሰራሩ ከይሲ ቢባል ይቀላል፡፡ እህቶቻችን ፓስፖርት ለማሳደስ ወይም ለአንድ ጉዳይ ወደ ኤንባሲ ደጃፍ ልክ ሲደርሱ የድሮ ቀበሌ አቀባበል ይደረግላቸዋል፡፡ ቀበሌ ትዝ ይልዎታል ወዳጄ… ዘበኛውም ሊቀመንበሩም እኩል ሰው የማመናጨቅ ስልጣን የተሰጣቸው ቦታ እኮ ቀበሌ ነው፡፡ (በነገራችን ላይ አሁን ግን ቀበሌ ተሸሽሏል፡፡ እኔ ሽሮሜዳን ትቼ “ልነካው” የነበረ ሰሞን ቀበሌ የሄደ ሰው የሚደረግለት እንክብካቤ… እንደው ያ ደህንነት ወዳጄ “ወግሞ” ባይዘኝ ኖሮ ለቀበሌያችን ፀባይ መሻሻል ስልስ እዛው ብኖር እመርጥ ነበር፡፡)

እናልዎ ዱባይ ያለው ኤንባሲያችን መጀመሪያ ሲገቡ የሚቀበልዎ፤ ከድሮ ቀበሌ በበለጠ ደረጃውን ያልጠበቀ ማመናጨቅ አቅርቦ ነው፡፡ ከዛ ለምንም ጉዳይ ይሂዱ የመጀመሪያው ጥያቄ ቦንድ ግዢ የሚል ነው፡፡ በጣም ስናጋንነው ኤንባሲ የሚሰራ ሰው ሰላም ለማለት የሄደች እንኳ ቦንድ ግዢ መባል አይቀርላትም፡፡
ከዛ በተጨማሪ ደግሞ “የኮሚኒቲ አባልነት” የሚባል ነገር አለ፡፡ አባል ያልሆነ ሰው በኤንባሲው በኩል ምንም ግልጋሎት አያገኝም፡፡ እንደውም አሟሙቆ ማውራት ምን ጠቅማል ብለን እንጂ… የኤንባሲው ሰራተኞች “አባል ያልሆነ ሰው ባል እንኳ እንዳታደርጉ” ተብለዋል አሉ፡፡
ቀልዱ ቀልድ ነው… ይቺ ወዳጄ በቃለ ምህላ እንደነገረችኝ፤ (መቼም ምላ አትዋሸኝም) አንዲት ኢትዮጵያዊት በኤንባሲዋ በኩል የሆነ ግልጋሎት ከፈለገች የኮሚኒቲ አባል ለመሆን ከሚከፈላት አምስት መቶ ድርሃም ውስጥ መቶ ሰማኒያውን “ሆጭ” አድርጋ መክፈል አለባት፡፡
ታድያ የሀገራችን ኤምባሲ በዱባይ ሆኗል አሉ ገዳይ ብንል ምን ውሸት አለብን ይባላል…
እንደውም ይሄንን ያጫወትኩት አንድ ወዳጄ ይሄማ ኤምባሲ ሳይሆን “ካዚኖ” ነው ብሎኛል፡፡ (መጣች እንግዲህ የዲያስፖራ ቃል… “ካዚኖ” ቁማር ቤት ነው፡፡ ቁማር ቤትስ ምንድነው… የሚል ካለ፤ ትንሽ ሰው የሚጠቀምበት ብዙ ሰው የሚከስርበት ተቋም ማለት ነው፡፡)
ስለዚህ እንላለን በዱባይ ካዚኖአችን ፈርሶ ኤንባሲያችን ይሰራ!

No comments:

Post a Comment