“አውሮፕላኑ አየር ላይ እያለ ሊፈነዳ ይችል ነበር”
ከአዲስ አበባ ወደ አክሱም ይጓዝ የነበረ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ረቡዕ ለት በጭንቅ እንዲያርፍ መደረጉ ተገለጸ፡፡ አደጋው ከአምስት ደቂቃ በፊት ቢከሰት ኖሮ አውሮፕላኑ አየር ላይ እያለ ሊፈነዳ ይችል እንደነበር ባለሥልጣናት አስታወቁ፡፡
78 መንገደኞችንና ሠራተኞችን አሣፍሮ ይጓዝ የነበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ (Bombardier Q400) አውሮፕላን ከክንፎቹ በአንዱ ጭስ መነሣቱን የሚጠቁም ማስጠንቀቂያ በመደወሉ እጅግ አስጨናቂ በሆነ መልኩ እንዲያርፍ መደረጉን ሱዳን ትሪቢዩን ዘግቧል፡፡ ጋዜጣው ስማቸው ከመግለጽ የተቆጠቡ ባለሥልጣንን ጠቅሶ እንደጻፈው አውሮፕላኑ ከማረፉ ከአንድ ደቂቃ በፊት የግራው ክንፍ እየጨሰ መሆኑን ማስጠንቀቂያው ማመልከቱንና አንዱ ሞተር ደግሞ እንደሚገባው ይሰራ እንዳልነበረ ገልጸዋል፡፡
ሱዳን ትሪቢዩን በስልክ ያነጋገራቸው ተሳፋሪ ጭስ ከአውሮፕላኑ ክንፍ ሲወጣ መመልከታቸውን፤ ተሳፋሪው ሁሉ በጭንቅ ውስጥ የነበረ መሆኑንና ሁኔታው በጣም አስደንጋጭ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ የአቪዬሽን ባለሙያዎችን በመጥቀስ የአየር መንገዱ ባለሥልጣናት እንደሚሉት ከሆነ አደጋው አውሮፕላኑ ከማረፉ አምስት ደቂቃ በፊት ተከስቶ ቢሆን ኖሮ አውሮፕላኑ አየር ላይ እያለ ሊፈነዳ ይችል ነበር፡፡
ሁኔታውን በጥንቃቄ ያስተዋለው የአውሮፕላኑ አብራሪ ካፒቴን ፈጣን እርምጃ በመውሰድ አውሮፕላኑ ወደ ዋናው ማቆሚያ ከመድረሱ በፊት በማቆምና ተሣፋሪዎቹ በፍጥነት እንዲወጡ በማድረግ ሊከሰት የነበረውን የእሣት አደጋ መከላከሉ ሱዳን ትሪቢዩን ዘግቧል፡፡ የካፒቴኑ ውሳኔ የሚደነቅ መሆኑን ባለሥልጣናቱ የገለጹ ሲሆን ተሣፋሪዎቹም ህይወታቸውን ከአደጋው በመታደጉ የጀግና ክብር በመሥጠት ማመስገናቸው ጨምሮ ተጠቅሷል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባለሥልጣናት የጭሱ መነሻ እየተመረመረ ነው ቢሉም አየር መንገዱ አደጋውን አስመልክቶ እስካሁን ይፋዊ መግለጫ አላወጣም፡፡
ባለፈው ሳምንት በቆመበት እሣት የተነሳበት ሌላ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን አደጋው ከታወቀ ጀምሮ የውጭ አገር የዜና ወኪሎች በየደቂቃው ዘገባ ሲያቀርቡበት የነበረ መሆኑ ቢታወቅም ከዚህ በባሰ መልኩ በርካታ ተሣፋሪዎችን ጭኖ ለአደጋ ተጋልጦ የነበረው አውሮፕላን ጉዳይ አደጋው ከተከሰተበት ረቡዕ ጀምሮ እስካሁን በመንግሥትም በኩል ሆነ በአየር መንገዱ ይፋ አለመሆኑ በበርካታዎች ዘንድ ጥያቄ መጫሩ የማይቀር ነው፡፡
No comments:
Post a Comment