መስፍን ወልደ ማርያም
ኅዳር 21/2006
በ1996 ዓ.ም. የክህደት ቁልቁለት በሚል ጽሑፌ ውስጥ ‹‹ማንነት ምንድን ነው፤ በሚል ንዑስ ርእስ ስር ከገጽ 98 ጀምሮ በተቻለኝ መጠን አፍታትቻለሁ፤ የሪፖርተር ጋዜጠኛ ይህንን ለማንበብ ጊዜ አላገኘም፤ ወይም የተገለጠለት ዱሽ ቅንጫቢ በቅቶት ይሆናል፤ የምጠቅሰውም ለሱ ሳይሆን ለሌሎች ነው፡፡
በቅርቡ በፌስቡክ ላይ አንድ አውቀቱ ይሁን ጤንነቱ፣ ወይም ኪሱ የተቃወሰበት ሰው በትግርኛ ስለማንነት ጽፎ ነበር፤ ከዚህ በፊትም ጽፎ አስተሳሰቡ ሁሌም የተወላገደ በመሆኑ አልፌው ነበር፤ አሁን ደግሞ ሲጽፍና በአንዳንድ የሱ ቢጤዎች አበጀህ! አበጀህ! ሲባል ሳይ አደገኛነቱን ተገነዘብሁ፤ አንዱን ጎባጣ ሀሳብ ቶሎ ካላስተካከሉት ብዙ ጎባጦችን ያፈራል፤ የተጣራና ቀና የሆነ ሀሳብን ለመግለጽ በጣም ያስቸግራል፤ ማሰብ መጨነቅን፣ ማበጠርን፣ ማጣራትን ይጠይቃል፤ አፍ እንዳመጣ መልቀቅ ቀላል ነው፤ በተለይ የሚዳኝ ከሌለ!
በመጀመሪያ ሀሳብን ለመግለጽ የተመረጠው ቋንቋ ጠበብ ያለና የተፈለጉ አድናቂዎች ዘንድ ለመድረስ ብቻ ከተፈለገ ሀሳቡም እንደቋንቋው ለተወሰኑ ሰዎች የተመጠነ ይሆናል፤ በዚህ ዓይነት የቀረበው ቅንጣቢ ሀሳብ በሌላ ቋንቋ ሊተረጎም አይቻልም፤ ደንቆሮነትን ማጋለጥ ይሆናል፤ ለምሳሌ በትግርኛ ‹‹ኢትዮጵያዊ ዝበሃል መንነት የለን፤›› የሚለውን ‹‹ኢትዮጵያዊ የሚባል ማንነት የለም፤›› በማለት፣ በእንግሊዝኛ ደግሞ ‹‹There is no identity called Ethiopian.›› ተብሎ ሊተረጎም ነው፤ እንግዲህ ይህ አወቀች፤ አወቀች ሲሏት መጽሐፉን አጠበች እንደተባለችው ሴትዮ፣ ወይም ደግሞ አላዋቂ ሳሚ እንትን ይለቀልቃል! የሚባል ነው፤ ‹‹ኢትዮጵያዊ ዝበሃል መንነት የለን፤›› ብሎ በትግርኛ የጻፈው ሰው የአለማወቁ አዘቅት ዓለምን በሙሉ የሚያናጋ መሆኑን አልተገነዘበም፤ (አሜሪካን፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ ኢጣልያን … የሚባል ማንነት የለም ሊለን ነው፤) የመንደር ማንነትን በሁለት እጆቹ ይዞ፣ አእምሮውን በመንደር ማንነት ጨቅጭቆ በየፓስፖርቱ ላይ የማንነት መግለጫ ተብሎ የተሰየመውንና በዓለም አቀፍ ደረጃ የታወቀውን ማንነት ካደው፡፡
በፍጹም ያልገባውን የፈረንሳዩን ፈላስፋ፣ የሩሶን ሀሳብ አበለሻሽቶ ከቆሻሻ መጣያ ውስጥ ያገኘው ቡትቶ ሊያደርገው ይከጅላል! ከጥራዝ-ነጠቅም አጉል ጥራዝ-ነጠቅ! ትግራይን የመገንጠል ዓላማ ያለው ሰው በእውነትና በግልጽ ዓላማውን ቢያራምድ በበኩሌ አልደግፈውም እንጂ አልቃወምም፤ መብቱ ነው፤ ነገር ግን በሰንካላ አስተሳሰብና በተንኮል ወጣቶችን ለመመረዝ የሚፈልገውን ሰው አጥብቄ እቃወማለሁ፤ ትግራይን እንደኤርትራ ካስገነጠለ በኋላ እንደኤርትራ ለትግራይም የኢትዮጵያዊነት ማንነትንን ማገድ ይቻላል፤ ከዚያ በፊት ግን ተንኮል ይቅር፡፡
ኢትዮጵያዊነትን ለማጥፋት የሚደረገው ሙከራ አዲስ ኤደለም፤ ኢጣልያኖች በሰፊው ዘርተውት የሄዱት ጉዳይ ስለሆነ የአባቶቻቸውን ውርስ የሚከተሉ ዛሬም ይኖራሉ፤ ኢትዮጵያዊነትን ለማጥፋት ብዙ ገንዘብና ሌላም የሚከፍሉ ብዙ የተለያዩ ድርጅቶች መኖራቸው የታወቀ ነው፤ ዱሮ የኢጣልያ ወኪሎች ተጠቅመውበታል፤ ዛሬ ደግሞ ሌሎችም ተጨምረው ያንኑ ተልእኮ የሚያራምዱ አሉ፤ በየዋህነት እንደበፊቱ እንዳናስተናግዳቸው እንጠንቀቅ!
No comments:
Post a Comment