‹‹የቀረበብኝ ክስ ብዙ በመሆኑ መቃወሚያ ለማቅረብ ረዘም ያለ ቀጠሮ ይሰጠኝ›› አቶ ገብረ ዋህድ ወልደ ጊዮርጊስ
- አቶ ጌቱ ገለቴና ሌሎች ተጠርጣሪዎች በጋዜጣ እንዲጠሩ ታዘዘ
በተጠረጠሩበት ከፍተኛ የሙስና ወንጀል፤ በፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ዓቃቤ ሕግ ክስ ተመሥርቶባቸው ላለፉት ስምንት ወራት በእስር ላይ የሚገኙት የቀድሞው የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መላኩ ፈንታ፣ ‹‹ክሴ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ይሁን ብዬ የጠየቅኩት እኔ አይደለሁም፤›› አሉ፡፡
አቶ መላኩ ተቃውሞአቸውን ያቀረቡት ጥር 6 ቀን 2006 ዓ.ም. የተጠረጠሩበትን ክስ እየመረመረው ለሚገኘው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 15ኛ ወንጀል ችሎት ነው፡፡ እሳቸው ሳይጠይቁና ምንም ሳይናገሩ በርካታ የመገናኛ ብዙኃን እሳቸው እንደጠየቁና እንደተከለከሉ አድርገው መዘገባቸውን በመቃወም፣ እንዲስተካከል ወይም ታርሞ እንዲዘገብ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ በበኩሉ በሰጠው ምላሽ እንደገለጸው፣ ጥያቄውን ያቀረበው ፍርድ ቤቱ ነው፡፡ የመገናኛ ብዙኃን ከፍረጃ ጋር በማያያዝ ዘገባ እንዳያስተላልፉ ከማስጠንቀቂያ ጋር የሰጠውን ትዕዛዝ ካስታወሰ በኋላ፣ ሁሉም የመገናኛ ብዙኃን በትክክል ባይዘግቡም ሁሉም ደግሞ ተሳስተዋል ማለት እንደማይቻል ገልጿል፡፡ ፍርድ ቤቱ ከዚህ በላይ የሚለው ነገር እንደሌለ በማሳወቅ ተከሳሾቹ ጠበቆቻቸውን አማክረው የስም ማጥፋት ወንጀል ተፈጽሞብናል የሚሉ ከሆነ፣ የሚመለከተውን አካል መጠየቅ እንደሚችሉ አስረድቷል፡፡
ሌላው ፍርድ ቤቱ በዕለቱ መዝገቡን ቀጥሮ የነበረው የአቶ መላኩን ክስ የማየት ሥልጣን ያለው ፍርድ ቤት የትኛው እንደሆነ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ከሕገ መንግሥት አጣሪ ኮሚሽን በደረሰው የምርመራ ውጤት ላይ ውሳኔ ሰጥቶ እንዲያሳውቀው የሰጠውን ትዕዛዝ ለመጠባበቅ እንደነበር ለችሎቱ አስታውቋል፡፡
በመሆኑም ፌዴሬሽን ምክር ቤት ታህሣሥ 24 ቀን 2006 ዓ.ም. ባደረገው ውይይት፣ የአቶ መላኩን ክስ የማየት ሥልጣን ያለው ከፍተኛው ፍርድ ቤት መሆኑን በማሳወቁ፣ በእነ አቶ መላኩ ፈንታ ላይ የተመሠረተው ክስ በመደበኛነት እንደሚቀጥል አሳውቋል፡፡
የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ የክስ መግለጫ እንደሚያስፈልገው በመጠቆም፣ ተከሳሾች የክስ መቃወሚያ ማቅረብ የሚችሉ መሆኑም በችሎት ተነግሯቸዋል፡፡ ተጠርጣሪ ተከሳሾቹ በክሱ ላይ ቅሬታ እንዳላቸውና መቃወሚያ እንደሚያቀርቡ ተናግረው፣ ከክሱ ስፋት አንፃር ረዘም ያለ ጊዜ እንዲሰጣቸው ሲያመለክቱ፣ የአዲስ ኢንተርናሽናል ካርዲያክ ሆስፒታል ባለድርሻ የሆኑት ተጠርጣሪ ተከሳሽ ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ ተቃውሞአቸውን ለፍርድ ቤቱ አቅርበዋል፡፡
‹‹ጠበቆች እየጠየቁ ያሉት ረጃጅም ጊዜ በመሆኑ እኛ የተፋጠነ ፍትሕ የማግኘት መብታችንን ያጣብብብናል፡፡ የምንፈልገው አጭር ቀጠሮ እንዲሆንልን ነው፤›› በማለት አመልክተዋል፡፡ አብዛኛዎቹ ተጠርጣሪ ድጋፋቸውን ሰጥተዋቸዋል፡፡
የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የሕግ ማስከበር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ገብረ ዋህድ ወልደ ጊዮርጊስ ግን የእነ ዶ/ር ፍቅሩን ተቃውሞ በመቃወም፣ ‹‹እኔ ብዙና ሰፊ ክስ አለብኝ፡፡ ጠበቆቼ በደንብ ተረድተውና አብራርተው የክስ መቃወሚያ እንዲያቀርቡ ረዘም ያለ ቀጠሮ ይሰጠን፤›› በማለት ለፍርድ ቤቱ አመልክተዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ የተጠርጣሪ ተከሳሾቹን ማመልከቻ ከሰማ በኋላ ብይን ሰጥቷል፡፡ በሰጠው ብይንም፣ በተጠረጠሩበት የተለያየ የሙስና ድርጊት ወንጀል ክስ ቢመሠረትባቸውም በችሎት ሊቀርቡ ያልቻሉት አቶ ጌቱ ገለቴን ጨምሮ ሌሎችም ግለሰቦች በጋዜጣ ጥሪ እንዲደረግላቸው ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ እንዲሁም በችሎት ተገኝተው ክሳቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙትና የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግን ክስ በሚመለከት መቃወሚያ እንዳላቸው ያመለከቱ ተጠርጣሪዎች ለጥር 29 ቀን 2006 ዓ.ም. ተቃውሞአቸውን እንዲያቀርቡ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
reporter
No comments:
Post a Comment