Wednesday, January 29, 2014

በአንጀሊና ጆሊ ኤክስኪዩቲቭ ፕሮዲዩሰርነት የተሰራው ኢትዮጵያዊው “ድፍረት” መነጋገሪያ ሆኗል

A+AA-
በአንጀሊና ጆሊ ኤክስኪዩቲቭ ፕሮዲዩሰርነት  የተሰራው ኢትዮጵያዊው “ድፍረት” መነጋገሪያ ሆኗል

በአንጀሊና ጆሊ ኤክስኪዩቲቭ ፕሮዲዩሰርነት የተሰራው ኢትዮጵያዊው “ድፍረት” መነጋገሪያ ሆኗል

‘አንጀሊና ጆሊ’ የሚለው ስም፣ አሁንም ከኢትዮጵያ ጋር ተያይዞ ተነሳ፡፡ አሁንም በስፋት ተዘገበ፣ በብዙዎች ተሰማ፣ ብዙዎችን አነጋገረ፡፡ አሁን ይሄን ታዋቂ ስም ከኢትዮጵያ ጋር አያይዞ ያስነሳው፣ ያ የፈረደበት ማደጎ አይደለም፡፡ በሁለቱ መካከል ትስስር የፈጠረችው፣ ከአመታት በፊት ወደ አሜሪካ በማደጎ የተወሰደችው ዘሃራ አይደለችም - አበራሽ እንጂ፡፡ ከአዲስ አበባ ወጣ ብላ በምትገኝ አንዲት የገጠር መንደር ውስጥ ተወልዳ ያደገች የ14 ዓመት ልጃገረድ ናት- አበራሽ በቀለ፡፡
አበራሽንና አንጀሊናን ምን አገናኛቸው?... ህይወት!...
ከአመታት በፊት…
የገጠሯ ጉብል አበራሽ፣ አንድ ማለዳ ደብተሮቿን ሸክፋ ከጎጆዋ በመውጣት፣ ከመንደሯ ርቆ ወደሚገኘው ትምህርት ቤቷ የእግር ጉዞ ጀመረች፡፡ ዳገት ቁልቁለቱን እየወጣች እየወረደች ወደ እውቀት ቤቷ ፈጥና ለመድረስ ረጅሙን መንገድ ተያያዘችው፡፡ እንዳሰበችው ፈጥና ለመድረስ፣ ድካሟን ተቋቁማ ነጠቅ ነጠቅ ብላ መራመድ ይኖርባታል፡፡ ምክንያቱም ትምህርት ቤቷ ለመድረስ ገና ብዙ መንገድ ይጠብቃታል። ምክንያቱም እሷ እንደ ሰውየው ፈረስ የላትም - ዳንግላሳ እየጋለበ ከጥሻው ስር ብቅ ሲል እንዳየችው ሰውዬ!!...

አበራሽ ጉዞዋን ትታ በፈረሰኛው የምትቀናበት ጊዜ የላትም፡፡ እየረፈደ ነው፡፡ ስለዚህ ፍጥነቷን ጨምራ መጓዝ አለባት፡፡ ጉዞዋን ቀጠለች… ደብተሮቿን አቅፋ፣ ነጠቅ ነጠቅ እያለች…
ጥቂት እንደሄደች ግን፣ ከበስተኋላዋ የሆነ ድምጽ ተሰማት… የፈረስ ኮቴ ድምጽ… ጉዞዋን ሳታቋርጥ ዘወር ብላ ተመለከተች፡፡ ሰውዬው ፈረሱ ላይ ጉብ ብሎ ከራስጌዋ ተዘብቧል፡፡ ሌሎች በየጥሻው መሽገው የነበሩ ጓደኞቹም ከያሉበት ብቅ ብለው ዙሪያዋን ከበዋታል፡፡
ሰውዬው ልጓሙን ጨብጦ፣ አንዳች ጉጉት ፊቱ ላይ እየተንቀለቀለ፣ በጎመዠ አይን ቁልቁል እያያት ከኮርቻው ላይ ዘሎ ወረደ፡፡ አበራሽ በድንጋጤ ክው ብላ፣ ደብተሮቿን ጥላ በፍርሃት ተንቀጠቀጠች፡፡ በጭንቅ ተውጣ ተብረተበተች። የሆነ መጥፎ ነገር እየመጣባት ስለመሆኑ አልተጠራጠረችም፡፡ ከፈረሰኛው ሩጣ ለማምለጥ አቅም እንደሌላት የተረዳችው ጉብል፣ ባለችበት ቆማ ለጠለፋ ተዘጋጅተው የከበቧትን ወንዶች እያየች እሪታዋን አቀለጠችው፡፡
ጩኸቷን ሰምቶ የደረሰላት አልነበረም፡፡ ፈረሰኛው ልጅቷን አፈፍ አድርጎ አንስቶ ከኮርቻው ቀዳማይ ኋላ አስቀመጣት፡፡ እሷ በውጭ ነፍስ ግቢ ነፍስ እየቃተተች ስትወራጭ፣ እሱ በደስታ እየተፍለቀለቀ ፈረሱን ኮልኩሎ ሽምጥ ጋለበ፡፡ በለስ የቀናቸው ጓደኞቹ “ያሆ በል!...” በሚል የድል ዜማ አጅበው ሸኟቸው - ሰውዬውንና ጠልፎ ያገኛት ሚስቱን፡፡
ሰውየው ጨከነ፡፡
ቢወልድ የሚያደርሳትን ልጃገረድ፣ ያለርህራሄ ልብሷን ቦጫጭቆ እርቃኗን አስቀራት፡፡ ከጎኑ ባጋደመው ጠመንጃ አስፈራርቶ፣ አስገድዶ ደፈራት፡፡ እሷ በደም አበላ እየታጠበች ስትንሰቀሰቅ፣ እሱ ወንድነቱን አፍስሶባት እፎይ ብሎ ተነፈሰ፡፡ ወለል ላይ እንደተዘረረች ትቷት ተነሳ፡፡ ዘወር ብሎም አላያትም፡፡ ዘወር ቢል ኖሮ፣ የአበራሽ እጆች ሲንቀሳቀሱ ያይ ነበር፡፡ ከደቂቃዎች በፊት እሷን ሲያስፈራራበት የነበረውን የገዛ ጠመንጃውን ስታነሳ፣ አንስታም ወደ እሱ ስታነጣጥር፣ ቃታ ስባ ጥይት በእሱ ላይ ስትቆጥር ያይ ነበር፡፡
ድንገተኛ የተኩስ ድምጽ ተሰማ፡፡
ሰውዬው ወለል ላይ ወድቆ ደም ያጎርፋል፡፡ የቆሰለ አካሉን ይዞ እየተወራጨ ይቃትታል፡፡
አበራሽ በጠለፋትና አስገድዶ በደፈራት በዚህ ጨካኝ ሰው ላይ በተፈጸመው የግድያ ወንጀል ተጠርጥራ እስር ቤት ገባች፡፡ ዋስ ጠበቃ ሆኖ የሚቆምላት አልነበረም፡፡ የዋስ መብቷ ሳይከበርላት በለጋ እድሜ በእስር መማቀቅ ዕጣዋ ሆነ፡፡
ከጊዜያት በኋላ…
የህግ ባለሙያዋ መዓዛ አሸናፊ ስለ አበራሽ ሰማች፡፡ ጠልፎ የደፈራትን ወንድ በጠመንጃ ተኩሳ ገድላለች ተብላ ኢፍትሃዊ በሆነ መልኩ በእስር ቤት እየተሰቃየች ስላለችው አበራሽ መረጃ የደረሳት መዓዛ ጊዜ አላጠፋችም፡፡ ልጅቷን ተሟግታ ከስቃይ ነጻ ልታወጣት ተነሳች፡፡ እናም በስንትና ስንት ውጣውረድ ያሰበችው ሆነላት፡፡
አሁን …
ከአመታት በፊት ሰሚ አጥታ በእስር ቤት ስትሰቃይ የኖረችዋ ልጅ ታሪክ፣ በብዙዎች ተሰማ። ከዚያች የገጠር መንደር አልፎ ከተማ ደረሰ፡፡ አዲስ አበባን አልፎ ተሰራጨ፡፡ አሳዛኙ ታሪኳ አሁን ደግሞ፣ አሜሪካ ተሻግሮ ብዙዎችን ያነጋገረ አለማቀፍ ፊልም ሆነ፡፡
የአንጀሊና ጆሊንና የኢትዮጵያን ስም ዳግም አስተሳስራ ያስነሳችው አበራሽ ናት፡፡ መገናኛ ብዙሃን ባሳለፍነው ሳምንት እነዚህን ስሞች ደጋግመው ያነሱት፣ አንጀሊና ጆሊ በአበራሽ እውነተኛ ታሪክ ላይ ተመስርቶ የተሰራውን “ድፍረት” የተሰኘ የአማርኛ ፊልም በሚገርም ሁኔታ በማድነቋ ብቻም አይደለም፡፡ አለማቀፍ ዝና ያላት የሆሊውዷ ፈርጥ አንጀሊና፣ የዚሁ ኢትዮጵያዊ ፊልም ኤክስኪዩቲቭ ፕሮዲዩሰር የመሆኗ አስገራሚ እውነት እንጂ፡፡
በኢትዮጵያዊው የፊልም ባለሙያ ዘረሰናይ ብርሃነ መሃሪ የተሰራውና ባለፈው ሳምንት በአሜሪካ ፓርክ ሲቲ በተጀመረው ሰንዳንስ አለማቀፍ የፊልም ፌስቲቫል ላይ በ‘ወርልድ ሲኒማ ድራማቲክ ውድድር’ ዘርፍ በዕጩነት የቀረበው፣ “ድፍረት” የተሰኘ ፊቸር ፊልም በታዋቂዋ የሆሊውድ ተዋናይት አንጀሊና ጆሊ ኤክስኪዩቲቭ ፕሮዲዩሰርነት መሰራቱንና ከፍተኛ አድናቆት ማግኘቱን ቀድሞ የዘገበው ኢንዲዋየር የተባለው ድረገጽ ነው፡፡
“ልብ የሚሰቅል ድንቅ ታሪክ፣በሚያምር የፈጠራ ክህሎት ተውቦ የቀረበበት ፊልም ነው። እንዲህ ያለ ፊልም መመልከት መነቃቃትን ይፈጥራል፡፡ የኢትዮጵያን የባህል ብዝሃነት የሚያሳይ ከመሆኑም በላይ፣ ባህላዊ ልማዶችን ሳይጋፉ የህግ የበላይነትን ማስከበር ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነም ያመለክታል፡፡” ብላለች - አንጀሊና ጆሊ ስለፊልሙ ስትናገር፡፡
 የፊልሙ ታሪክ የኢትዮጵያን መጻኢ ዘመን ብሩህነት እንደሚያሳይ የገለጸችው አንጀሊና፣ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ልጃገረዶች በመሰል ሁኔታ ያለ ህግ ከለላ የሚያድጉባቸውን ሌሎች አገራትም ወደተሻለ አቅጣጫ እንዲጓዙ የሚያመላክት እንደሆነ  ተናግራለች፡፡ በፊልሙ ውስጥ ያለችውን የህግ ባለሙያ የመሳሰሉ ጀግና ሴቶች፣ አንድን ማህበረሰብ ለለውጥ እንዲነሳ የመቀስቀስ አቅም እንዳላቸው እንደሚያሳይም ገልጻለች፡፡
“የዚህ ፊልም መምጣት፣ በኢትዮጵያ ኪነጥበብ ውስጥ እንደ ታላቅ ምዕራፍ የሚቆጠር ነው” ብላለች - አንጀሊና ጆሊ ስለ ፊልሙ ያላትን አድናቆት ስትገልጽ፡፡ አንጀሊና ጆሊ ለፊልሙ ያላትን አድናቆት በይፋ መግለጧ፣ የፊልሙን ተቀባይነት ከፍ እንደሚያደርገውና ምናልባትም ከፌስቲቫሉ በኋላ በአሜሪካ ለሽያጭ የሚበቃበትን ትልቅ ዕድል ሊፈጥርለት እንደሚችል እየተነገረ ነው፡፡ ታዲያስ መጽሄት ከኒውዮርክ እንደዘገበው፣ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ በኡታህ ፓርክሲቲ በተጀመረው ሰንዳንስ የፊልም ፌስቲቫል ላይ እንዲሳተፍ የተመረጠውና የድራማ ዘውግ ያለው ፊልሙ፣ ካለፈው እሁድ ጀምሮ በኢጂብሽያን ቲያትር፣ በብሮድዌይ ሴንተር ሲኒማ፣ በላይብረሪ ሴንተር ቲያትርና በሆሊዴይ ቪሌጅ ሲኒማ ለተመልካች እየቀረበ ይገኛል፡፡
የ“ድፍረት” ደራሲና ዳይሬክተር ኢትዮጵያ ውስጥ ተወልዶ ያደገው ዘረሰናይ ብርሃነ መሃሪ ሲሆን ከአሜሪካ ዩኤስሲ ስኩል ኦፍ ሲኒማቲክ አርትስ በፊልም የመጀመሪያ ዲግሪውን አግኝቷል። በፊልም ስራ ከአስር አመት በላይ ልምድ ያካበተው ዘረሰናይ፣ ሃይሌ አዲስ ፒክቸርስ የተባለ የፊልም ኩባንያ በማቋቋም ነው ይሄን “ድፍረት” የተሰኘ የመጀመሪያ ሥራውን ለእይታ ያበቃው፡፡
ታዋቂዋ የሆሊውድ ተዋናይ አንጀሊና ጆሊ፣ ከአምስቱ የፊልሙ ኤክስክዩቲቭ ፕሮዲዩሰሮች አንዷ መሆኗ ታላላቅ አለማቀፍ የመገናኛ ብዙሃንን ትኩረት የሳበ ሲሆን ለፊልሙ ስኬታማነትም ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት እየተገለፀ ነው። ከአንጀሊና በተጨማሪ ጁሊ ምህረቱ፣ ጄሲካ ራንኪን፣ ፍራንሴስካ ዛምፒ እና ሌሲ ሽዋርዝም የፊልሙ ኤክስኪዩቲቭ ፕሮዲዩሰሮች እንደሆኑ ታውቋል፡፡  የፊልሙ ደራሲና ዳይሬክተር የሆነው ዘረሰናይ፣ ከኢትዮጵያውያኑ ምህረት ማንደፍሮና ሊላይ ደመወዝ ጋር የፊልሙ ፕሮዲዩሰር ነው፡፡
የታሪኩን ባለቤት አበራሽን በቀለን ሆና የተወነችውን ታዳጊ ትዝታ ሃገሬንና የአበራሽ ጠበቃ መዓዛ አሸናፊን በመሆን የተጫወተችውን  ሜሮን ጌትነትን ጨምሮ ከ371 በላይ አንጋፋና ወጣት ተዋንያን የተሳተፉበት “ድፍረት”፣ ቀረጻው በኢትዮጵያ እንደተከናወነ ለማወቅ ተችሏል፡፡
በፊልሙ ስራ ላይ ከተሳተፉት ባለሙያዎች ግማሽ ያህሉ ሴቶች መሆናቸውም በፊልሙ ፕሮጀክት ድረገጽ ላይ የወጣው መረጃ ይገልጻል። በሰንዳንስ የፊልም ፌስቲቫል ላይ የቀረበ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ፊልም እንደሆነ የተነገረለት የዘጠና ዘጠኝ ደቂቃ እርዝማኔ ያለው ፊልሙ፣በአማርኛ ቋንቋ የተሰራና የእንግሊዝኛ መግለጫ (ሰብታይትል) ያለው ነው፡፡
የፊልሙ ሲኒማቶግራፈር ሞኒካ ሌንዜውስካ ስትሆን አጄንስካ ግሊንስካም በኢዲተርነት ሰርታለች፡፡ የፕሮዳክሽን ዲዛይነርነቱን ስራ፣ ዳዊት ሻዎል ሲያከናውነው፣ የፊልሙን ማጀቢያ ሙዚቃ የሰሩት ደግሞ ዴቪድ ሾመርና ዴቪድ ኤጋር የተባሉ ታዋቂ የሙዚቃ ባለሙያዎች እንደሆኑ ታውቋል፡፡ ኢንዲዋየር  ፊልሙን በተመለከተ ባወጣው መረጃ መሰረት፣ የአበራሽ ጠበቃ የነበረችዋን መዓዛ አሸናፊን ወክላ በፊልሙ ላይ የተጫወተችው ተዋናይት ሜሮን ጌትነት፣ በፌስቲቫሉ ላይ እንዲሳተፉ ከተመረጡ የፊልሙ  አስር ተዋንያን መካከል አንዷ በመሆን ወደ አሜሪካ አቅንታለች፡፡

No comments:

Post a Comment