Wednesday, November 27, 2013

በኢህአዴግ አባላት ስም ፓርላማውን በመቆጣጠር ኢህአዴግን ሊጎዱት ይችላል ሲሉ የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትር ተናገሩ

የግንቦት7 እና አክራሪ የእስልምና ሀይሎች 

ኢሳት ዜና :-ሚኒስትር ዶ/ር ሽፈራው ተክለማርያም ይህን የተናገሩት ” በክርስትና እና በእስልምና ሃይማኖት ሽፋን የሚካሄደው የፖለቲካ እንቅስቃሴ የመንግስት ቀጣዩ የምርጫ ፈተና” በሚል ርእስ ለኢህአዴግ ከፍተኛ አመራሮች ባቀረቡት ጽሁፍ ነው።ኢሳት የሚኒስትሩን  ሙሉ ንግግር የያዘ ሰነድ የደረሰው ሲሆን፣ በሰነዱ ግርጌ ላይ ” ለመደበኛ አባላት የማይነገር፣ ለከፍተኛ አመራሮች ብቻ” የሚል ተጽፎበት ይታያል።  በዚህ ርእስ ስር ደግሞ ” ቀጣዩ የምክር ቤት አባላት ምርጫ የግንቦት ሰባት እና አክራሪ እስልምና ሀይሎችን የሚያስቀጥሉ አባላት ወንበሩ በኢህአዴግ አባላት ስም ሊነጠቅ ይችላል። ” ብሎአል። ሚኒስትሩ ለዚህ አስተሳሰባቸው የምርጫ 97ትን ሁኔታ እንደማጠቃሻ ተጠቅመዋል። ” የ97 የቅንጅት አሸናፊት አካሄድ ስልት ማለትም የተቃዋሚ አባላት ሁነው በህቡእ ተደራጅተው በኢህአዴግ የአባላትን ካርድ ሙሉ በሙሉ ፓርቲውን ሊጎዱት ይችላሉ” ሲሉ ሚኒስትሩ ጽፈዋል።

ሚኒስትሩ በዚህ ጽሁፋቸው፣ ቅንጅት በ97 ምርጫ ማሸነፉን እንዲሁም የኢህአዴግ አባላት ሆነው ለቅንጅት በውስጥ ይሰሩ የነበሩ ሰዎች እንደነበሩ ጠቅሰዋል። በክርስትና እና በእስልምና ሀይማኖት ሽፋን የሚካሄደውን የፖለቲካ እንቅስቃሴ ሚኒሰትሩ በዝርዝር አቅርበዋል።
Image
በክርስትና ሀይማኖት በኩል ” መንግስት በሃይማኖት አባቶች ሹመት ላይ እጁን ያስገባል፤ የዋልድባ ገዳም ተደፈረ፤ አልፎ አልፎ በአጋጣሚ ቤተክርስታያን ባለበት አካባቢ ከድርቅ ጋር ተያይዞ በሚነሳ ቃጠሎ ሆነ ተብሎ እንደተደረገ ማስወራት፤ ይህን የሚያግዝ የውጭ ሚዲያ መኖር ኢሳት በቀዳሚኒት ፣ የደርግ ስርዓት ደጋፊዎች የሆኑት ቪኦኤ በቀጣይነተወ የሚያራግቡት አካሄደ ጉዳዩን ትኩረት እንዲያገኝ ” ማድረጉን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
የሙስሊሙ እንቅስቃሴንም በተመለከተ ሚኒሰትሩ ሲገልጹ”  ከቅንጅት እስከ ህብረት፣ ከቪኦኤ እስከ ቲቪ አፍሪካ፣ ከጀርመን ድምጽ እስከ ቢላል ሬዲዮ፣ ከጅሃዳዊ ሀረካት እስከ ግንቦት ሰባት፣ ከኢትዮጵያ ሙስሊሞች ዓለም አቀፍ እስከ መድረክ እስከ ስደተኛው ሲኖዶስ ያሉ ሀይሎች በተናጠልና በህብረት” ተሳትፈውበታል ብለዋል።
የሙስሊሙ እንቅስቃሴ በከፍተኛ ፍጥነት በመዳከም ሂደት ውስጥ የገባው በቡድኑ ቀንደኛ መሪዎች ላይ ህጋዊ ስርአቱን ተከትሎ የእስራት እርምጃ ከተወሰደ በሁዋላ ነው ብለዋል።
በሃይማኖት ሽፋን የሚካሄዱ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ውለው አድረው እየተጋለጡና እየተዳከሙ መሄዳቸው ባይቀርም ባለፉት ሁለት ዓመታት ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱን በሀይል ለመፈታተን ከሞከሩት የሁከት ሀይሎች ዋነኞቹ ነበሩ ማለት ይቻላል ብለዋል ሚኒሰትሩ።
“በሃይማኖት ስም የሚካሄደውን ንግድ ውጤታማ እንዲሆን በማድረግ ረገድ  የድህነት መንሰራፋትና የመልካም አስተዳደር  እጦት ወይም ጉድለት ተጠቃሽ ናቸው” የሚሉት ዶ/ር ሽፈራው በተለይ ከድህነትና ኋላቀርነት መውጫውን ትክክለኛ መንገድ የሚያመላክት መሪ ድርጅት በሌለበት ፣ በሃይማኖት ሽፋን የሚነግዱ የፖለቲካ ሀይሎች አንዱን በሌላው ላይ ማነሳሳት የፅድቅ መንገድ እንደሆነ አስመስለው በማቅረብ ዜጐችን ወደጥፋት ይመራሉ” ብለዋል።
መሪ ድርጅቱም ኖሮ በአመራርም ሆነ በአባላት ደረጃ በአንድ በኩል ከፀረ ድህነትና ኋላቀርነት ትግሉ ላይ ጽናትና ብቃት ያለው አመራር መስጠት ካልተቻለ፣ በሌላ በኩል ደግም የፓርቲና የመንግስት መሪዎች ስራቸውን ከየትኛውም ሃይማኖት ገለልተኛ በሆነ መንገድና ሁሉን ሃይማኖቶች እኩል በሚያስተናግድ አግባብ ካልፈፀሙ ይኸው ችግር ተባብሶ መቀጠሉ አይቀርም ሲሉ ዶ/ር ሽፈራው አስጠንቅቀዋል።
አሁንም ድህነትና ኋላቀርነት በመኖሩ፣ በፓርቲና በመንግስት አመራራችን የሚታዩ የመልካም አስተዳደር ጉድለቶች በመኖራቸውና የእምነት ጉዳይ ለሚዛናዊ አስተሳሰብ ያለው ተጋላጭነት ዝቅተኛ በመሆኑ አልፎ አልፎ የተካረረ ፍጥጫ እያጋጠመ መሆኑንም ሚኒስተሩ በጽሁፋቸው አብራርተዋል።
ዶ/ር ሽፈራው ተክለማርያም ለኢህአዴግ ባለስልጣናት ያቀረቡትን ሙሉ ጽሁፍ በድረገጻችን መመልከት የምትችሉ መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን።
በክርስትና እና በእስልምና ሃይማኖት ሽፋን የሚካሄደው የፖለቲካ እንቅስቃሴ የመንግስት ቀጣዩ የምርጫ ፈተና
ዶ/ር ሺፈራው ተክለ ማርያም
 ህዳር 2006 ዓ.ም
አዲስ አበባ

No comments:

Post a Comment