Wednesday, November 6, 2013

ህወሀት በእነ አቶ ስየ ላይ የጀመረውን ዘመቻ ቀጥሎበታል


 ኢሳት ዜና :-ህወሀት በውስጡ የተነሳበትን መከፋፈል ለማስቀረት በእነ አቶ ስብሀት ነጋ የሚመራው ቡድን የቀድሞ ታጋዮችን በማሰባሰብ ህወሀትን ለማዳን በሚረባረብበት ጊዜ፣ በአቶ ስየ አብርሀ እና ቤተሰቦቻቸው ላይ የተጀመረው ዘመቻ ግን እንደቀጠለ መሆኑ ታውቋል። አቶ ስየ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴያቸው በእጅጉ የተገታ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ( ኢቲቪ) ” የነቀዙ ሀይሎች” በሚል በእርሳቸውና በአቶ ታምራት ላይኔ ላይ የዶክመንታሪ ፊልም ሰርቶ ማዘጋጀቱ ታውቋል። ፊልሙን ለምን አሁን ለመስራት እንደተፈለገ የታወቀ ነገር የለም። ይሁን እንጅ በህወሀት እና በመንግስት ኮሚኒኬሽን ቢሮ ሀሳብ አመንጭነት ፊልሙ መዘጋጀቱን ለማወቅ ተችሎአል።

የአቶ ስየ ታናሽ ወንድም አቶ ምረተአብ አብርሀ በሙስና ተከሰው በእስር ላይ ከሚገኙት ከአቶ ገብረውሀድ ጋር ግንኙነት አላቸው ተብሎ ዘብጥያ ቢወርዱም፣ ሰሞኑን በዋለው ችሎት ግለሰቡን በሙስና የሚያስከስስ መረጃ ሊገኝ አልቻለም። አቃቢ ህግ አቶ ምርተአብን ለመልቀቅ ባለመፈለጉ ፣ በምርመራው ወቅት ታክስ እንዳጭበረበሩ ተደርሶበታል በሚል ከሙስና ጋር ባልተያያዘ ክስ ተመልሰው እንዲታሰሩ አድርጓል። ፍርድ ቤቱ ጉዳዩ ምክር ያስፈልገዋል በማለት አቶ ምረተአብን ለመፍታት ሳይደፍር ቀርቷል።
በጉዳዩ ላይ አቶ ስየ አስተያየት የሚሰጡ ከሆነ ለማነጋገር ዝግጁ መሆናችንን እንገልጻለን።

No comments:

Post a Comment