Wednesday, November 6, 2013

አይ አበሻ! አበሻና ሆድ፤ አንድ (ፕ/መስፍን ወልደ ማርያም)



ወያኔና የነፖሊቲካ አጋሮቹ የሚያደርጉትን ለእነሱ የሚመች አከፋፈል ትተን አበሻን ለሁለት እንክፈለው፤ ሆድ ያለውና ሆድ የሌለው፤ ወይም የሚበላና የማይበላ፤ ዛሬ የምናገረው ሆድ ስላለው ወይም ስለሚበላው አበሻ ነው፤ አታውቁት እንደሆነ ተዋወቁት፤ በአጠቃላይ ስንመለከተው ግን የአበሻ ፍቅርም ሆነ ጠብ ለሆድ ነው፤ አበሻን የሚያጣላው፣ የሚያነታርከው፣ የሚያቧጭቀው የሆድ ነገር ነው፤ ለመብላት ነው፤ አንዳንዴም ሎሌውን ለማብላት ነው፤ ግብር ለማግባት ነው።
አዳም አበሻ ሳይሆን አይቀርም፤ ሁሉንም ነገር ብላ ከተከለከለው በቀር ብሎ ያስቀመጠው ይመስላል፤በላባችሁ ወዝ ብሉ ተብለው አዳምና ሔዋን መረገማቸውን አበሻ ገና አልሰማም፤ አበሻ የተፈጠረው ገነት ውስጥ ቁጭ ብለህ ያለውን ሁሉ ብላ በተባለበት ጊዜ ነው፤ እግዚአብሔር አበሻን ሁሉንም ብላ ሲለው ምናልባትም በጆሮው ጭራሽ አታስብ ብሎት ይሆናል፤ እስቲ በመጀመሪያ ስለምግብ እንነጋገር።

በሌላው ነገር ሁሉ ኋላ-ቀር ቢሆንም በምግብ ጉዳይ አበሻን የመበልጠው ያለ አይመስለኝም፤ የዓለም ሕዝቦች ሁሉ የምግብ ውድድር ቢያደርጉ በምግብ ዓይነት፣ በጣዕም፣ በአሠራሩ ጥበብ አበሻ በቀላሉ እንደሚያሸንፍ በፍጹም አልጠራጠርም፤ የቱ አገር ነው ወዝ ያለውና ለስላሳ እንጀራ ያለው? በነጭ ጤፍ በሠርገኛው፣ በጥቁር ጤፍ፣ በስንዴውና በገብሱ፣ በማሽላውና በዘንጋዳው፣ በበቆሎው በእጅ ለመጠቅለል፣ በጉሮሮ ለማውረድ እንደአበሻ አመቻችቶ የሚሠራ የቱ ሕዝብ ነው? እንጀራው ሲፈለግ ቃተኛ፣ ሲፈለግ አነባበሮ እየሆነ በቅቤና በአዋዜ ርሶ ሆድ የሚያርስ ምግብ ማን ይሠራል፣ ከአበሻ በቀር?
የዳቦው ዓይነትስ ቢሆን ብዛቱና ጣዕሙ! ድፎው፣ የዶሮ ዳቦው፣ አምባሻው፣ ሙልሙሉ፣ ቂጣውስ ቢሆን ስንት ዓይነት ነው?
አበሻ ከጥንትም ጀምሮ የእግዚአብሔር ሰው ነው፤ ስለዚህም ይጾማል፤ ለእግዚአብሔር ሲል፣ መንግሥተ ሰማያት ለመግባት ሲል ከወዳጁ ከምግብ፣ በተለይም ከሥጋና ከቅቤ ይለያል፤ መጾም ዓላማው ለነፍስ ቢሆንም ለሥጋም ትልቅ ጠቀሜታ አለው፤ በአካል ውስጥ የተጠራቀመውን ጮማና ሞራ ለማራገፍ ይረዳል፤ አበሻ ግን ምኑ ሞኝ ነው፤ በሆድ ቀልድ የለም! የጾም ምግብ የሚባል ነገር ፈጥሮ ሆዱን ያስደስተዋል፤ ሥጋና ቅቤ ቀረብኝ ብሎ እንዳይጠወልግ ተቆጥሮ ብዛቱ የማይታወቅ ዓይነት የጾም ወጥ አለው፤ ስንት ዓይነት የአትክልት ምግብ፣ በዚያ ላይ ሹሮው፣ ክኩ፣ ስልጆው፣ ተልባው፣ ሱፉ፣ የሽምብራ ዓሣው፣ አዚፋው፣ ስንቱ ይቆጠራል!
ጾሙ ያልፍና ፍስኩ ሲመጣ አበሻ ፊቱን ከአትክልት ዓለም ወደእንስሳት ዓለም ያዞራል፤ ከዶሮ ጀምሮ እስከበሬው ኡኡ እያለ ለእርድ ይሰለፋል፤ የዶሮው ወጥ፣ የበጉ ወጥና አልጫው፣ ቅቅሉ፣ ምንቸት አብሹ፣ ክትፎው፣ ጥብሱ፣ ዱለቱ፣ ጥሬ ሥጋው፣ ምኑ ቅጡ!
የአበሻ ምግብ በዚህ ብቻ አይቆምም፤ አንዳንድ አበሻን የማያውቁ ሰዎች አበሻ ፍቅር አያውቅም ይላሉ፤ አበሻ ሌላ ቀርቶ በምግብም ፍቅሩን ይገልጻል፤ የመዝናኛና የፍቅር ምግብም አለ፤ እነቅንጬ፣ እነጨጨብሳ፣ እነግፍልፍል እዚህ ውስጥ የሚመደቡ ናቸው።
አበሻ የመንገድ ምግብም አለው፤ አገልግሉ፣ ቋንጣው፣ በሶው፣ ጭኮው፣ ጭኮው፣ የቡና ቁርስ እያለ ቆሎውን፣ ንፍሮውን፣ በቅቤና በአዋዜ የራሰ ቂጣውን፣ አነባበሮውን፣ አሹቁን ይከሰክሳል፤ አበሻ ከተመቸው መቼ ነው ከመብላት የሚያርፈው? የቱ አገር ነው በዚህ ሁሉ ምግብ ተወዳድሮ አበሻን ማሸነፍ የሚችለው?
አበሻ ምግብ ስለሚወድ የሚያስበላው ነገርም ይወዳል፤ ቃሪያን መብላት ልዩ ጥበብ ያደረገው ለዚህ ነው፤ ቂሉ ፈረንጅ አፐረቲቭ እያለ (ከሣቴ ከርስ መሆኑ ነው፤) አንጀቱን የሚጠብሰውን አረቄ ይጠጣል፤ በቅመማቅመምና በድልህ የተቁላላውን ወጥ በእንጀራ እየጠቀለለ ቢጎርስ እያላበው ይበላ ነበር!
የአበሻ ምግብ የሚበላው ወገን በፈረንጅ አገር ሲኖር አገሬ የሚለውና የሚናፍቀው የአበሻ ምግብ ነው! ስለዚህም በሄደበት የአበሻ ምግብ አይለየውም! አበሻ ሆዱን ትቶ አይሰደድም! እንዴት ብሎ!

No comments:

Post a Comment