Monday, September 30, 2013

“ፕሬዚዳንት እንድሆን ብጠየቅ በቅድሚያ ምን ያህል ላገለግል እችላለሁ እላለሁ – ወ/ሮ ሰሎሜ ታደሰ


የቀድሞዋ የመንግስት ቃል አቀባይ ወ/ሮ ሰሎሜ ታደሰ ሃገር ቤት ከሚታተመው ሎሚ መጽሔት ጋር ቃለ ምልልስ አድርጋለች። የዘ-ሐበሻ አንባቢዎች ግንዛቤ ይረዳቸው ዘንድ ቃለ ምልልሱን እንደወረደ አስተናገድነው…

ሁሉ ነገር ራዕይ ሆኖ ይቀጥላል እንዲባል አልፈልግም
በሥልጣን የሚመጣ ክብር ደግሞ ከሥልጣን ጋር አብሮ ይቀራል

ሎሚ፡- አምባሣደር ዮዲት እምሩ በሕይወትሽ ከፍተኛ መነቃቃት እንደፈጠሩብሽ ይሰማል፤ እንዴትና ለምን?
ወ/ሮ ሰሎሜ፡- እሳቸው ከፈጠሩብኝ መነሣሣትና መነሳሳት ይልቅ አባቴ እሳቸውን ምሣሌ በማድረግ ውስጤ የፈጠረው መነሣሣት ነው የሚበልጠው፡፡ ልጅ እያለሁ እሣቸው አምባሣደር ነበሩና በቴሌቪዥን በተደጋጋሚ ይታዩ ነበር፡፡ የዛን ጊዜ እኔ አራተኛ ክፍል ነበርኩ፡፡ ሁልጊዜም በቴሌቪዥን ሲመጡ አባቴ ይጠራኝና “…በቃ አንቺ ስታድጊ እሣቸው ስራ የላቸውም” ይለኝ ነበር፡፡ የእሱ አባባል ስታድጊ ስራቸውን ትወስጅባቺዋለሽ ዓይነት ነበር፡፡
የመጀመሪያዋ ሴት እንደዚህ ታላቅ የሚባል ስራ ይዘው በቴሌቪዥን መጥተው ያየኋቸው እሳቸው ናቸው፡፡ እሣቸው ላይ ይበልጥ ትኩረት እንድሰጥና እንድነቃቃ ያደረገው ደግሞ አባቴ ነው፡፡
ሎሚ፡- ያኔ ልጅ እያለሽ አምባሣደር ዮዲት የፈጠሩብሽ አይነት ስሜት አሁን በሌሎች ትናንሽ ሴት ልጆች ላይ መፍጠር ችያለሁ ብለሽ ታስቢያለሽ?
ወ/ሮ ሰሎሜ፡- እንደዚያ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ሁሌም የምለው ነገር ነው፤ ሁሉም ሰው እዚህች ምድር የመጣው ለምክንያት ነው በሚለው አምናለሁ፡፡ ምክንያት ደግሞ የሆነ ተፅእኖ የሚያሣድር ማለት ነው፡፡ ያ ተፅእኖ ደግሞ ጥሩ ነገር ለመስራትና ለማነሳሳት አርአያ ለመሆን ቢሆን ደስ ይለኛል፡፡ ወጣት ሴቶች እሷን አይቼ ነው ይህን የሆንኩት ቢሉ ደስ ይለኛል፡፡ ከዚህ ሌላ ደግሞ ከአንዳንድ ሴቶች ጋር ስንገናኝ… “አንቺ በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅት ቃል አቀባይ በነበርሽበት ወቅት የምትናገሪውን እሰማ ነበር፤… በዛ ምክንያት እንዲሕ አድርጌ…” ሲሉኝ ደስ ይለኛል፡፡ በርግጥ እነሱ ይህንን ይላሉ፣ ወደፊት እንዲሕ እባላለሁ… ብዬ ባልንቀሳቀስም… መንገዱ ግን ያንን ፈጥሮ ከሄደ በጣም ደስ ይላል፡፡ እናም እፈጥራለሁ የሚል እምነት አለኝ፡፡
ሎሚ፡- የሕይወት ፍልስፍናሽ ምንድን ነው?
ወ/ሮ ሰሎሜ፡- ከባድ ጥያቄ ነው ብዙ ጊዜ የሚከብደኝ ጥያቄ የሕይወት ፍልስፍናሽ ምንድነው የሚለው ነው፡፡ በአንድ ወቅት የነበረ ፍልስፍና በሌላ ወቅት ሊቀየር አይችልም ወይ ብዬ አስባለሁ፡፡ በተለይ የራሴን ወደኋላ መለስ ብዬ ሳስታውስ… ከልጅነቴ ጀምሮ የያዝኩት ፍልስፍና ነው ለማለት ይከብደኛል፡፡ ምክንያቱም ፍልስፍናን ራሱን ለመተግበር አቅም ይጠይቃል፡፡ ግን አሁን ዛሬ በአጭሩ ምንድነው ፍልስፍናሽ ብትለኝ በዚህች ምድር ላይ ዱካ የጣለ፣ ኮቴ የነበረው ሰው፣ ኮቴው የተሰማ ሰው ሆኖ ማለፍ፡፡ ሁልጊዜ ሁለት አይነት ሰዎች አሉ ብዬ አስባለሁ፡፡ አንዳንዶቹ ነበሩ ሄዱ የሚባሉ ናቸው፤ አይሞቅም አይበርድም፤ እኔ እንደዛ ባልሆን ደስ ይለኛል፡፡
ሎሚ፡- በሕይወትሽ የገጠመሽን ከባድ ፈተና እንዴት ትገልጪዋለሽ?
ወ/ሮ ሰሎሜ፡- እንግዲህ ፈተና ይኖራል፡፡ ግን አንድ ፈተና ለዘላለም ይደጋገማል ብዬ አላምንም፡፡ የሰው ልጅ ፈተና ሊገጥመው ይችላል፡፡ ግን በተለያዩ ወቅቶች ፈተና የሚመስሉ ነገሮች ይገጥሙሀል፡፡ ለኔ የመጀመሪያው ፈተና ብዬ የማስበው በ14 አመቴ አባቴ ሲሞት ነው፡፡ ይህንን ዓለም ቀየር ባለ ሁኔታ በሚነቀንቅና በሚሰማ መልኩ ሲፈጠር ያ ፈተና ነው፡፡ እናም የፈተናዬ መጀመሪያ ካልኩት የአባቴ ሞት ነበር፡፡ እሱም እንዴት አለፈ ብዬ የማስበው በፍቅር፣ በድጋፍ በሆነ መልኩ ነው፡፡ ለእኔ ፈተና ማለት በሕይወትህ ዘንበል ማለት ነው፡፡ ሌላው ፈተናዬ ብዬ የማስበው ከራሺያ ወደ ጀርመን ሀገር ስጠፋ ወደ ስደት የገባሁበት ጊዜ ነው፡፡ ከዛ በኋላ ግን ምን ፈተና ገጠመኝ?… ለክፉ የሚሰጥ ነገር የለም፤ …/ሳቅ/…
ሎሚ፡- አብዛኛው ሰው የሚያውቅሽ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት የመንግስት ቃል አቀባይ ሆነሽ ስትሰሪ ነው፤ ያኔ ኮከብ ቃል አቀባይ ሆነሽ ወጥተሻል ቢባልም ለሥራው ልምድ እንዳልነበረሽ ይታወቃል፤ በአጠቃላይ ሥራውን እንዴት ተወጣሽው?
ወ/ሮ ሰሎሜ፡- ደስ የሚል ነበር፤ በጣም ፈተና ነበረው፤ እኔ ደግሞ መፈተን የሚለውን ቃል በጣም እወዳለሁ፡፡ ፈተና ነው ወይ? አዎ! አንደኛ ኢልአዴግ ሥልጣን ከያዘ ወዲሕ ሀገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ጦርነት የገባችበት ጊዜ ነው፡፡ ሁለተኛ እኔ ከአሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ ከመጣሁ ገና አንድ ወር ብቻ ነበር ያሳለፍኩት፡፡ ከበርካታ ዓመታት የውጪ ሃገር ቆይታ በኋላ ብዙ ሰው የማላውቅበት፣ ብዙ ሲስተሞችን ወደማላውቅበት ሁኔታ ውስጥ ነው የገባሁት፡፡ ሦስተኛ ነገሮች በሙሉ በጣም አጣዳፊ ነበሩ፤ አንድ ቃል ከአፌ ወጣ ማለት መመለሻ አይኖርም፡፡ ዓለም አቀፉ ሚዲያ ወዲያው ወዲያው መረጃ ይፈልግ ስለነበር ጭምር ነው ሥራውን ፈታኝ ያደረገው፡፡ በታሪክ እንደምንሰማው ድሮ በጦርነት ጊዜ ጀግኖቻችን እንዲህ አደረጉ፣ እንዲህ ፈፀሙ… የሚል ነገር ነበር የምውቀው፡፡ ይሄ ደግሞ ለኔ ይበልጥ ሣልቸገር እንድሰራ አድርጐኛል፡፡ ከዛ ባለፈ ደግም እኔ ብዙም አልፈራም፡፡ “የሞኝ ደፋር ነኝ” /ረጅም ሳቅ/… አመዛዝኖ የሚገባ ደፋር ሣልሆን በቃ የአቅሜን እሰጠሁት ድረስ የመጣው ነገር ላይ አልጨነቅም፡፡ የኔ ኃላፊነት ነው ብዬ የማምነው ከኔ ያልተቆጠበ አቅም መስጠት ነው፡፡ ከዛ ውጤቱን ለሁሉም ነው የምሰጠው፡፡
ሎሚ፡- በወቅቱ ዛቻ ይሰነዘርብሽ ነበር?
ወ/ሮ ሰሎሜ፡- ከማን?
ሎሚ፡- ለምሳሌ ከሻዕቢያ?
ወ/ሮ ሰሎሜ፡- ከዚያ ወገንማ ሁሌም ዛቻ ነበር፤ በኢ-ሜል… በጣም ብዙ ዛቻዎችና ዘለፋዎች ይደርሱኝ ነበር፡፡ “እንደዚህ ትደረጊያለሽ፣ እንደዚህ ትሆኛለሽ” የተለመደ ነው፡፡ የምጠብቀው ነገር ነው፡፡ ሌላ ብዙም አላይም ነበር፡፡ በእነሱ ቴሌቪዥንና ሬዲዮ የተለያዩ ድራማዎች ይሰሩብኝ ነበር፡፡
ሎሚ፡- የኢቲቪ ሥራ አስኪያጅ በነበርሽበት ወቅት ምን ለውጥ አስመዝግቤያለሁ ትያለሽ?
ወ/ሮ ሰሎሜ፡- ምን ለውጥ አስመዝግቤያለሁ እላለሁ?
ሎሚ፡- በኔ በኩል የማውቀው ይኖራል፤ መመለስ ግን ያለበት ባንቺ ነው…
ወ/ሮ ሰሎሜ፡- ይቻላል የሚል አይነት አሠራር አጭሬ ነበር ብዬ አስባለሁ፡፡ ጥሩ ጥሩ ፕሮግራሞች መስራት ይቻላል፣ ፈጣሪ መሆን ይቻላል፣ ነፃ መሆን ይቻላል… የሚል የመነሳሳት ሁኔታ የነበረ ይመስለኛል፡፡ ያንን አስተሳሰብና ስሜት ፈጥሬ ነበር የሚል ሀሣብ አለኝ፡፡
ሎሚ፡- በኢቲቪ ካስጀመርሻቸው ፕሮግራሞች አንዱ “ዓይናችን” ነበር፡፡ ሳሙኤል ፍቅሬ ያን ፕሮግራም ይሰራ በነበረበት ወቅት የፕሮግራሙ አካሄድ ከመንግስት ወይም ከፓርቲው ሰዎች የፈጠረብሽ ጫና አልነበረም?
ወ/ሮ ሰሎሜ፡- በጣም የሚገርምህ ነገር ምንም ጫና አልነበረም፡፡ አቁሙ፣ አታድርጉ የሚል አልነበረም፡፡ በፕሮግራሙ ያልተደሰቱ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ግን ነበሩ፡፡ ለምሣሌ የሄርሜላን ጉዳይ ስንሰራ ፍትሕ ሚኒስቴር ቅር ተሰኘ፡፡ እንዲሕ ዓይነት ነገር ሁሌም ግራ ይገባኛል፡፡ መንግስት ማለት ሚኒስቴር፣ ተቋም፤ እንደ መንግስት መመሪያ ሲሰጣቸው ነው የሚሰሩት፡፡ ሁሌም ግራ የምጋባበት ነገር ነው፡፡ ለምሣሌ ፕሮግራሙ በጣም መልካም ነው የሚሉ በርካታ ባለስልጣናት ነበሩ፡፡ ፕሮግራሙ ያጋለጣቸው ደግሞ ሚዛናዊ አይደላችሁም ይሉ ነበር፡፡
ሎሚ፡- አሁን ያለውን የኢቲቪ አሠራር እንዴት ታዪዋለሽ?
ወ/ሮ ሰሎሜ፡- እኔ እንጃ፤ አላውቅም፡፡
ሎሚ፡- እንዴት?
ወ/ሮ ሰሎሜ፡- ማለቴ ውስጡን አላውቅም፡፡
ሎሚ፡- ከላይ ያለውስ?
ወ/ሮ ሰሎሜ፡- ይለያል፡፡
ሎሚ፡- በምን?
ወ/ሮ ሰሎሜ፡- ለምሣሌ አሁን አንዳንዴ “ዓይናችን” ሲመለስ አያለሁ፡፡ ይሄን ይሄን ስመለከት ቀጣይነት አለው እንዴ ይሄ ነገር ብዬ አስባለሁ፡፡ ግን በይበልጥ እኔ ከነበርኩበት የተለየ አቅጣጫ ይዞ የሚሄድ ይመስለኛል፡፡
ሎሚ፡- ከመንግስት ስራ የለቀቅሽው ከአንዳንድ ባለስልጣናት ጋር በመጋጨትሽ ነው ይባላል፤ ለመልቀቅሽ ምክንያቱ የገዢውን ፓርቲ አቋም ባለመቀበልሽ ወይስ በሌላ?
ወ/ሮ ሰሎሜ፡- ይሄንን ነገር በተመለከተ ብዙ ጊዜ ተፅፎ አይቻለሁ፡፡ ሰምቻለሁ፡፡ ግን ከመንግስት ባለስልጣናት ጋር አልተጋጨሁም፡፡ እኔ የምሰራው አንድ ነገር ዋጋ አለው ብዬ ሣምን ብቻ ነው፡፡ ምንም ዓይነት ስራ ቢሰጠኝ ለገንዘብ፣ ለሥልጣን፣ ስለሚያዋጣ ነው ብዬ ሰርቼ አላውቅም፡፡ በእርግጥ በነፃ ኢኮኖሚ እንደዚህ ማሰብ የፋራ ነው፤ አውቃለሁ፡፡ በዚህ እኔ ፋራ ልሁን፡፡ ልቤ የወደደውን ነው የምሰራው፤ ያ ነገር በተለያየ ነገር እየተሸራረፈ የሚሄድ ከመሰለኝ አቅም አይኖረኝም፡፡ እንደዚያ ስለተሰማኝ ነው የለቀቅኩት፡፡ ከማንም ጋር አልተጋጨሁም፡፡ በርግጥ ሁሌም እንደተጋጨሁ ነው፤ ግጭት የኔ መካከለኛው ስሜ ነው፡፡ ግን ግጭት በራሱ መጥፎ አይደለም፡፡ /ረጅም ሣቅ/…
ሎሚ፡- የአቶ መለስ ዜናዊን ሕልፈት በተመለከተ በሚዲያ ቀርበሽ ምንም አስተያየት ስትሰጪ አልታየሽም፤ የቀድሞውን ጠ/ሚ ሕልፈትና፣ ከዚያ በኋላ ያለውን የገዢውን ፓርቲ አካሄድ እንዴት አገኘሽው?
ወ/ሮ ሰሎሜ፡- በአቶ መለስ ሞት በጣም ነው ያዘንኩት፡፡ መለስ የራሱ ዕይታ ያለው ሰው ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ወደዚሕች ዓለም መጥተው ሹልክ ብለው የሚሄዱ አሉ፡፡ ወይ ሞቀው ወይ በርደው የሚሄዱ ሰዎች አሉ፡፡ መለስ ለኔ እንደዛ ነው፡፡ መለስን ውደደውም ጥላውም አትርቀውም፡፡ መውደድና መጥላት ሌላ ነው፤ መደገፍ ሌላ ነው፡፡ ነገር ግን ይታገላል፤ ኃይል አለው፡፡ በዚህ በጣም አደንቀዋለሁ፡፡ ስለዚህ በእሱ ሕልፈት በእጅጉ አዝኛለሁ፡፡ በዚያ ላይ ዕድሜው ገና 57 ነበር፤ ብዙ በሚሰራበት ዕድሜው ነው ያለፈው፤ መለስ በእምነቱ ፀንቶ በዚያው ቀጥሎ ነው ያለፈው፡፡ ይሕም ያሳዝናል፡፡ እንደማንኛውም ሰው እንደዚህ ያሉ ነገሮች ሐዘን ፈጥረውብኛል፡፡ ከሕልፈቱ በኋላ ያለው ነገር ደግሞ በሠላም ሽግግር መካሄዱ ነው፡፡
ሎሚ፡- ከመለስ በኋላ ለውጥ ታይቷል?
ወ/ሮ ሰሎሜ፡- ይህንን ለመመለስ ጊዜው ገና ነው፡፡
ሎሚ፡- እስካሁን የታዩ ሂደቶችን ስንመለከትስ?
ወ/ሮ ሰሎሜ፡- ሂደቱ ሲተች በራሱ ይገርመኛል፤ መለስ ካለፈ ገና አንድ ዓመት ነው፡፡ ያን ያህል ግዙፍና ትልቅ መለያ ለጐደለበት ሀገር ገና ጊዜ መጠበቅ አለበት፡፡
ሎሚ፡- የመለስ ራዕይ የሚባለውንስ እንዴት ትመለከቺዋለሽ፤ በራዕይ ታምኛለሽ?
ወ/ሮ ሰሎሜ፡- ሕልም አለ ብዬ አምናለሁ፡፡ ለምሣሌ ማርቲን ሉተር ኪንግ ሕልም አለመ፡፡ በዚየ ሕልም መሰረት ኦባማ ኋይት ሐውስ ገባ፡፡ ለእኔ ሕልም እንደዚያ ነው፡፡ ኪንግ I have a dream ነበር ያለው፡፡ አንድ ሰው ያልማል፤ ከዚያ የሚቀጥሉ የተለያዩ ትግሎች ይኖራሉ፡፡ ሕልምን ያለመው ሰው አይጨርሰውም፤ ሌላ ትውልድ ነው የሚያሳካው፡፡ ሰሞኑን 50ኛው አመት የማርቲን ሉተር ኪንግ ሕልፈት ሲከበር ዋሽንግተን ነበርኩ እና ተከታትዬዋለሁ፡፡ እዚያው አሜሪካ ሆኜ ሕልም ማለት ለካ ይሄ ነው የሚለውን ነበር ያሰብኩት፡፡ እና የመለስ ራዕይ ቢባል ብዬ የማስበው ኢትዮጵያ መካከለኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ ትደርሳለች የሚለውን ነው፡፡ እሱ ለኔ ሕልም ነው፡፡ ያንን ሕልሙን እናሳካለን ብሎ መናገሩ ደስ ይለኛል፡፡ ሁሉ ነገር ራዕይ ሆኖ ይቀጥላል እንዲባል አልፈልግም፡፡ እንደማሳሰቢያ መሆንም የለበትም፡፡ ከወቅቱ ጋር ሆኖ ምን ማለት ነው ብሎ ማሰብ መቻል ያስፈልጋል፡፡ ራዕይ መኖሩ ጥሩ ሆኖ ሳለ… እንዲያው ዝም ብሎ በራዕይ መኖር አይገባም፡፡
ሎሚ፡- “የኛ” በተሰኘ ፕሮጀክት ዙሪያ እየተንቀሳቀስሽ ነው፤ “የኛ” ዓላማው ምንድነው? በአሁኑ ወቅት የሚያደርገው እንቅስቃሴስ ምን ይመስላል?
ወ/ሮ ሰሎሜ፡- “የኛ” የወጣቶች ፕሮግራም ነው፡፡ በተለይ ደግሞ የወጣት ሴቶች ፕሮግራም፡፡ ለሴቶች ብቻ ሣይሆን በአጠቃላይ ለሕብረተሰቡ አንድ ወጣት ሴት ትምህርት ቤት ብትገባ፣ ያለ እድሜዋ ባትዳር፣ ምንም አይነት ፆታዊ ትንኮሣ ባይደርስባት፣ ሠርታ ገቢ ብታመጣ ለእናንተ ለወንዶቹም ይመቻችኋል፡፡ (…ረዥም ሳቅ…) እናም “የኛ” ይሕን ለማሳካት ነው እየሰራ የለው፡፡
ሎሚ፡- ሰሎሜ በፖለቲካ እንቅስቃሴ መሳተፍ አይመችሽም?
ወ/ሮ ሰሎሜ፡- ፖለቲካ ስትል?…
ሎሚ፡- በፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ ገብቶ መሳተፍ፣ ንቁ እንቅስቃሴ ማድረግ…
ወ/ሮ ሰሎሜ፡- አልወድም… ልበል? ትንሽ የሚያስፈራኝ ምን መሠለህ? እኛ ሀገር ፖለቲካ ወይ ነጭ ወይ ጥቁር ነው፡፡ ወይ እዚህ ወይ እዚያ ነው፡፡ ይሕ ደግሞ ማመዛዘን የማይፈቅድ ይሆናል፡፡ የየትኛውም ፓርቲ አባል ሆነህ ኦ… ይሕንን እደግፋለሁ፣ ይሕ ደግሞ መስተካከል አለበት የምንልበት ደረጃ ላይ ገና አልደረስንም፡፡ ለምሣሌ አንድ ሰው ኢህአዴግ እኮ መንገድ ሰርቷል ቢል… ኦ እሱማ ኢሕአዴግ ነው የሚል ፍረጃ ይመጣል፡፡ ተቃዋሚው እንዲህ ቢያደርግ ስትል ደግሞ የኢሕአዴግ ተቃዋሚ ናት ይልሀል፡፡ እና ፖለቲካ ወይ ጥቁር ወይ ነጭ ነው፡፡ ይሄ ይመስለኛል የኢትዮጵያ ፖለቲካ ችግር፡፡ ነፃ አስተሳሰብ ላለው ሰው ይሕ አካሄድ የሚከብድ ይመስለኛል፡፡
ሎሚ፡- ኢትዮጵያ በታሪኳ የመጀመሪያ ሴት ፕሬዚዳንት ያስፈልጋታል የሚል አቋም ያላቸው ወገኖች ቀዳሚ ምርጫቸው አንቺን በማድረግ መወያያ ሲያደርጉሽ ሠንብተዋል፤ ከገዢው ፓርቲ ሠፈር ከዚህ ጋር የተያያዘ ጥያቄ ቀርቦልሻል?
ወ/ሮ ሰሎሜ፡- ኧረ በፍፁም!… ማንም ሰው በዚህ ዙሪያ አላናገረኝም፡፡ /…ሣቅ…/
ሎሚ፡- መወያያ መሆንሽንስ እንዴት አገኘሽው?
ወ/ሮ ሰሎሜ፡- ማንም ሰው በሕዝብ ለትልቅ ቦታ ሲታጭ ደስ ይላል፡፡ ለዚህ ደረጃ ትበቃለች ተብሎ መታሰብም ያስደስታል፡፡ በተለይ ለረጅም ጊዜ ከሚዲያ የጠፋሁ ቢሆንም፣ እስካሁን ድረስ ሰዎች አልረሱኝም ብዬ አስባለሁ፡፡ ለዚህ ቦታ ሰሎሜ ትመጥናለች ብሎ መነጋገሩ በራሱ በጣም ደስ የሚል ነው፡፡
ሎሚ፡- ከዚህ በኋላ ፕሬዚዳንት እንድትሆኚ ብትጠየቂ ምላሽሽ ምን ይሆናል?
ወ/ሮ ሰሎሜ፡- አንድ አቋም ነው ያለኝ፡፡ አቋሜ ስልጣን ሕዝብን ማገልገያ ቦታ ነው የሚል ነው፡፡ ሥልጣን ለኔ የስለት ቦታ አይደለም፡፡ የገንዘብ፣ የመታያ፣ የመከበሪያ ቦታ አይደለም፡፡ ክብር ከፍቅር ይመጣል ብዬ ነው የማምነው፡፡ ከፍርሃት አይመጣም፡፡ ብዙ ጊዜ በሥልጣን የሚመጣ ክብር ደግሞ ከሥልጣን ጋር አብሮ ይቀራል፡፡ በፍቅር የሚመጣን መከበር ነው ይበልጥ የምወደው፡፡ ስለዚህ ፕሬዚዳንት እንድሆን ብጠየቅ መልሴ ምን ያህል ላገለግልበት እችላለሁ የሚለውን ጥያቄ ነው ቀድሜ የማነሳው፡፡
ሎሚ፡- በሀገራችን የሴቶች ፖለቲካዊ ተሣትፎ ምን ደረጃ ላይ ይገኛል ትያለሽ?
ወ/ሮ ሰሎሜ፡- በሴቶች ጉዳይ ሁለት አመለካከት ነው ያለኝ፡፡ አንዳንድ ሰዎች ጤና ጣቢያ ያገኛሉ ወይ፣ ትምህርት ቤት ይገባሉ ወይ፣ መንገድ ተሰርቷል ወይ… የሚሉትን መሰረታዊ የሴቶች ጥያቄ አድርገው ያቀርባሉ፡፡ እንደኔ አይነቱ ደግሞ የሴቶች ጥያቄ የሥልጣን ጥያቄ ነውም ብለን እናምናለን፡፡ ያ እንደተጠበቀ ሆኖ ሴቶች በሥልጣን ረገድ በቂ ውክልና ቢያገኙ አንደኛ ራሱ መንግስት ይጠቀማል ብዬ አምናለሁ፤ አገርም ይጠቀማል፡፡ የተለያዩ መነፅሮች መኖራቸው ጠቃሚ ነው፡፡ በዚህ አንፃር ኢትዮጵያውያን በጣም ወደኋላ ነን፡፡
ሎሚ፡- ሰሎሜ ለኢትዮጵያ ምን ትመኛለሽ?
ወ/ሮ ሰሎሜ፡- ተስፋ ማድረግ የሚችል፣ ሕልም ማለም የሚችል ሕብረተሰብ ሲኖር አገር ያድጋል፡፡ ለኢትዮጵያ የምመኘው ተስፋ ማድረግና ማለም ቋሚ የሆነባት ሀገር እንድትሆን ነው፡፡
ሎሚ፡- የቤተሰብት ኃላፊነት ተመቸሽ ወይስ ይከብዳል?
ወ/ሮ ሰሎሜ፡- ደስ ይላል፡፡ ሁለት ልጆች አሉኝ፡፡ መንታ ናቸው፡፡ ምክንያቶች ናቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ ለሕይወት ትርጉም ይሰጣሉ፡፡ ስትደክም ቀና ያደርጋል፤ ደጁ አስጠልቶህ ቤትህ ስትገባ በግድ ወሬህ ይቀየራል፡፡ ባለቤቴ በጠም ደጋፊዬ ነው፤… የቤተሰብ ኃላፊነት የውጪውን ሕይወት ብዙም አልቀየረብኝም፡፡
ሎሚ፡- የሰርግሽ እለት ምን ዓይነት ስሜት ተሰማሽ?
ወ/ሮ ሰሎሜ፡- ፓርቲ፤ /ረጅም ሳቅ/ …የእውነት የተሰማኝ እንደዛ ነበር፡፡
ሎሚ፡- የጫጉላ ወቅትሽንስ የት ነበር ያሳለፍሽው?
ወ/ሮ ሰሎሜ፡- ሲሸልስ፡፡
ሎሚ፡- አሁን ባለስዳር ነሽ፤ ማታ በስንት ሰአት ወደ ቤት ትገቢያለሽ?
ወ/ሮ ሰሎሜ፡- ያው እንደስራዬ ነወ፡፡ ጥሩ ስገባ ለሁለት ሩብ ጉዳይ፣ ሁለት ሰአት፤ በጣም በሥራ ከተወጠርኩ ደግሞ ከዚያም በላይ ላመሽ እችላለሁ፡፡
ሎሚ፡- ልጆች የማሣደግ ኃላፊነት ከበደሽ እንዴ?
ወ/ሮ ሰሎሜ፡- አይከብድም፡፡ ልጆቼ ፍቅር ናቸው፡፡ ለሰው ልጅ ደግሞ ፍቅር በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ በልጅነትህ ያ መሠረት ካለህ አይከብድም፡፡ ለልጆቼ መፍጠር የምፈልገው በፍቅር እንዲደገፉ፣ መውደድን እንዲያውቁ፣ በራሣቸው እንዲተማመኑ ነው፡፡ በራስ መተማመን ለሚለውም እንደ ሰው ነው የማወራቸው እንጂ እንደ ልጅ አይደለም፡፡
ሎሚ፡- በሰርግሽ ላይ ከተገኙ ሰዎች መካከል ላንቺ ከተላለፉ መልእክቶች የትኛው ትዝ ይልሻል?
ወ/ሮ ሰሎሜ፡- ነገርየው ብዙም ግድ አልሰጠኝም ነበር፤ እውነት ለመናገር ሰው ያለውን ነው የተከተልኩት፤ በተለይ ጓደኞቼ ሲያገኙኝ “ፈረንጅ ነው የምታገቢው አይደል?” እያሉ ነበር የሚጠይቁኝ፡፡ ሰሎሜ ለሀበሻ አትሆንም ብለው ነበር እንዴ? /ሣቅ/…. ከመልዕክቱ ይልቅ ያ ነበር የሚገርመኝ የነበረው፡፡
ሎሚ፡- ቤትሽ ውስጥ በቤተሰብሽ የምትበለጪበት ቋንቋ አለ?
ወ/ሮ ሰሎሜ፡- በጣም! ፈረንሣይኛ… አሁንማ ጦጣ ሆኛለሁ፡፡ ባለቤቴም ሁለቱም ልጆቼ ፈረንሳይኛውን ይሉታል፡፡ እሱ በጣም ቅናት ሁሉ አሣድሮብኛል፡፡ አብዛኛውን ነገር አልሰማም፡፡
ሎሚ፡- ለመማር አልሞከርሽም?
ወ/ሮ ሰሎሜ፡- አሊያንስ ገብቼ ለመማር ሞክሬ ነበር
ሎሚ፡- ታዲያ…
ወ/ሮ ሰሎሜ፡- ሰለቸኛ፡፡
ሎሚ፡- የሕይወቴ ዋናው ምዕራፍ የምትዪው የትኛውን ጊዜ ነው?
ወ/ሮ ሰሎሜ፡- ከስደት ወደ ኢትዮጵያ የተመለስኩበት ጊዜ፡፡
ሎሚ፡- ውጪ ሃገር ምን ያህል ጊዜ ቆየሽ?
ወ/ሮ ሰሎሜ፡- ራሺያ፣ ጀርመን፣ አሜሪካ ተደማምረው 16 ዓመት፡፡
ሎሚ፡- በ2006 ምን አዲስ ነገር አስበሻል?
ወ/ሮ ሰሎሜ፡- በጤና ላይ ትኩረት ማድረግ፤ በሁለተኛ ደረጃ መፅሐፍ ለመፃፍ ልሞክር ነው፡፡
ሎሚ፡- ሰሎሜ ለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ፤
ወ/ሮ ሰሎሜ፡- እኔም በጣም አመሰግናለሁ፡፡

No comments:

Post a Comment