የሞት “ድግስ”
መስከረም 4 ቀን 1996ዓ.ም ለኢትኦጵ ጋዜጠኛ የስልክ ጥሪ ይደርሰዋል። “ በነገው እለት ከቀኑ 6ሰአት መስቀል አደባባይ በሚገኘው የትግራይ ልማት ዋና ቢሮ 4ኛፎቅ እንድትገኝ” የሚል ማስጠንቀቂያ አዘል ጥሪ ነበር የደረሰው። ከዛ በፊት ለስድስት ወር የአየር መንገድ የደህንነት ሃላፊ ሃይሌ ጋዜጠኛውን ሲያስጨንቀው፣ የተለያዩ የማግባቢያ ወይም መደለያ ሃሳቦችን ሲያቀርብለት ቆይቷል። መስከረም 2 ቀን ደግሞ በቀበሌ 06/07 መ/ር ቢሮ እንዲገኝ የሚገልፅ መጥሪያ ቢደርሰውም በአጋጣሚ ጋዜጠኛው ስላልተመቸው አልሄደም። በማግስቱ የቀበሌውን ሊ/መ አቶ ቢሻው አበጋዝን ያገኘውና « ትላንት ፈልጋችሁኝ ነበር፤ ለምን ነበር?» ሲል ይጠይቀዋል፤ ቢሻውም « እኛ አይደለንም የፈለግንህ፤ ከደህንነት ቢሮ የመጡ ሰዎች ናቸው የፈለጉህ፤ ባለመምጣትህ ተናደው ነው የሄዱት፤ ለምን እንደፈለጉህ አልነገሩንም፤» በማለት መለሰ። …ከዛ በኋላ ነው - የመስከረም 4 ጥሪ የደረሰው፤ በማግስቱ በተባለው ቢሮ ተገኘ። ከ30 ደቂቃ ቆይታ በኋላ የማህበሩ ዳይሬክተር « ከሚፈልጉህ የበላይ አካላት ጋር አገናኝሃለሁ» በማለት ለጋዜጠኛው ተናግሮ በሚያሽከረክራት ኒሳን መኪና ተያይዘው ቦሌ በሚገኘው የደህንነት ቢሮ አመሩ።.. ከአንድ ግዙፍና አስፈሪ ገፅታ ካለው ሰው ጋር ጋዜጠኛውን አገኛኝቶት ወጥቶ ሄደ። ..« እሺ ኢየሩሳሌም አርአያ..» አለ ንቀት በተሞላበት ሁኔታ፤ አስከተለና፥ « ወ/ስላሴ እባላለሁ፤ ....ከእኛ ባልደረባ ጋር ስትገኛኝ ነበር፤ መንግስት ብዙ አማራጮችን አቅርቦልህ..አንተ ግን አሻፈረኝ ብለሃል። ለመሆኑ የምታወጣቸው መረጃዎች ተፅፈው ነው የሚሰጡህ?...ለምንድነው መረጃ የሚሰጡህን የሕወሐት ሰዎች የማትነግረን?..የምናስራቸው፣ የምንጠይቃቸው መስሎህ ነው?...» ሲል ሹሙ ሲናገር፣ ጋዜጠኛው ግን የቀረቡትን መደራደሪያዎች እንደማይቀበል ተናገረ። ለሁለት ሰአት ተኩል ከደህንነት ሃላፊው ጋር ውዝግብ የተቀላቀለበት ቃላት ተለዋወጡ። በተለይ የደህንነት ሹሙ « ..የትግራይ ተወላጅ ያውም ቤተሰብህ አድዋ ሆነው..እንዴት ፀረ-ሕወሐት ትሆናለህ?..ከጠላቶቻችን አንዱ ከሆነው ኢትኦጵ ጋዜጣ ጋር እንዴት ትሰራለህ?..» እያለ ከመናገሩ በተጨማሪ « እንዳንተ የተለማመጥነውና የታገስነው የለም። ብንገድልህስ?..» ሲል በንቀት ሲጠይቅ፣ ጋዜጠኛውም « ምንም ጥያቄና መልስ አያስፈልገውም፤ አሁኑኑ ሽጉጥህን መዘህ ልታደርገው ትችላለህ። እኔ ብእር እንጂ የያዝኩት - ከጀርባዬ ያሰለፍኩት ሰራዊትና መሳሪያ የለም። ..ደግሞም ለስልጣን ያበቋችሁን 36ሺህ ታጋዮች ላይ ምን እንደፈፀማችሁ ስለማውቅ..» አላስጨረሰውም፤ ..« እሱ አይመለከትህም፤ ከማን ጋር ምን እያወራህ እንዳለህ እወቅ!?..ከዚህ በኋላ እንድታስብበት የ15 ቀን ጊዜ ብቻ ሰጥተንሃል። በነዚህ ቀናት አቋምህን አስተካክለህ፣ የተባልከውን ካልፈፀምክ ግን…እንገድልሃለን!! ማንም አያድንህም!! ጨርሻለሁ።» በማለት አምባረቀበትና አሰናበተው። ..ከአስራ አምስት ቀን በኋላ ረቡዕ መስከረም 20 ቀን 1996ዓ.ም ከምሽቱ 3፡30 ሰአት ገደማ በመኖሪያ ቤቱ አቅራቢያ ወ/ስላሴ ያሰማራቸው ሰባት የፌደራል ፖሊስ አባላት “አቦ ድልድይ” አቅራቢያ ጋዜጠኛውን ጥብቀው በያዙት ዱላ የቻሉትን ያክል ቀጥቅጠውና ከፍተኛ ጉዳት አድርሰው ወደ ድልድዩ ወረወሩት። ሶስት ጥርሱ ተሰበረ፣ ጭንቅላቱ 5 ቦታ ተፈነካከተ፤ ሁለቱ እጆቹ፣ ግራ እግሩ፣ ወገቡ፣..አጠቃላይ አካሉ ተጎዳ። ...እነ ወ/ስላሴ ከድርጊቱ በኋላ ለጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና 5 ጊዜ ስልክ ደውለው « የኢየሩሳሌምን ሬሳ ሂድና ከምኒሊክ ሆስፒታል ውሰድ..» ሲሉ ተሳለቁ።…ከጨካኞች፣ ገዳዮችና አምባገነኖች ..የሚጠብቅ ፈጣሪ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባትን የጋዜጠኛውን ነፍስ በኪነ-ጥበቡ ታደጋት። እነሆ ከአስር አመት በኋላ የቀድሞ የደህንነት ሹም ወ/ስላሴ ወ/ሚካኤል እስር ቤት ሲወረወር፥ በእርሱ “ሞት የተደገሰላት” የጋዜጠኛው ነፍስ በህይወት ቆይታ ለማየት በቃች። ሁሉም የዘራውን ሊያጭድ ግድ ነው!! …ይህ ታሪክ የእኔ ነው። (በምስሉ የሚታየው ለስድስት ወር ያልጋ ቁራኛ የዳረገኝ የግድያ ሙከራ ከተፈፀመብኝ በኋላ፣ )
No comments:
Post a Comment