Thursday, August 1, 2013

ሽብርንና ‘ፀረሽብር ሕግ’ን አልደግፍም .! (በፀረሽብር ሕጉ ተሸብረን) የመናገር ነፃነታችንን አሳልፈን አልሰጠንም


የኢህአዴግ መንግስት በኢቲቪ በኩል ስለ ‘ሽብር’ና የ‘ፀረሽብር ሕግ’ አስፈላጊነት ያወራል። አንዳንድ ተቃዋሚዎች ደግሞ ስለ ‘ፀረሽብር’ ሕጉ ኢ-ሕጋዊነት ይሰብካሉ።

እኔም የፀረሽብር ሕጉ ከማይደግፉ ሰዎች ጋር እንደምሰለፍ ካሳወቅኩ ከጥቂት ግዜ በኋላ አንድ የምወደው የህወሓት አባል የሆነ ጓደኛዬ እንዲህ ሲል በውስጥ መልእክት ላከብኝ፣

“ፀረሽብር ሕግ መቃወም ኮ ሽብርን መደገፍ ነው። አንዳንድ አክራሪዎች በሰላማዊ ሰልፍ ስም ሽብርተኝነትን ማስፋፋት ይፈልጋሉ። ዓመፅ ቀስቅሰው እስላማዊ መንግስት ማቋቋም ይፈልጋሉ። በኢትዮዽያ ዓመፅ ተቀሰቀሰ ማለት ደሞ ልክ እንደ ሶርያ ቀውስ ነው የሚሆነው።”

ሽብር ምንድነው? ሽብር ‘ኮ ሃይል ተጠቅሞ ወይ ሃይል የመጥቀም ዛቻ በማሰማት ሌሎች ሰዎች ሰግተው፣ ፈርተው የግል ዓላማውን እንዲያሳኩለት ማድረግ መቻል ወይ እርምጃ መውሰድ ነው።

እኔ ሽብርን አልደግፍም። የኢህአዴግ መንግስት ከተቃወምነው አንዳንድ ችግሮች ሊያደርስብን እንደሚችል አውቃለሁ። በዚህ መሰረት የመንግስትን ቅጣት (እነሱ የማይፈልጉትን ከሰራን ማለት ነው) ፈርተን፣ ሰግተን ገዢውን ፓርቲ እንድንደግፍ ወይ ቢያንስ እንዳንቃወም ጥረት እናደርጋለን። ይህ የሚቃወሙትን ሰዎች በማግለል መቃወማቸውን እንዲያቆሙ የማድረግ ተግባር በራሱ ዜጎችን ማሸበር ነው። መንግስት ዜጎችን ያሸብራል፤ ሳይፈልጉ ግን ፈርተው እንዲገዙ ያደርጋል። ስለዚህ የኢህአዴግ ተግባር የሽብር ተግባር ነው። ሽብር አልደግፍም። የሽብር ተግባር እቃወማለሁ። ለዚህም ነው የኢህአዴግን መንግስት የምቃወመው።
ሳንፈልግ ፈርተን፣ ሰግተን አንድ ነገር እንድናደርግ እያስገደደን ያለው ማነው? ፀረሽብር ሕጉ ፈርተን (በፀረሽብር ሕጉ ተሸብረን) የመናገር ነፃነታችንን አሳልፈን አልሰጠንም??? የፀረሽብር ሕጉ ከተደነገገ ወዲህ አልተሸበርንም? ፀረሽብር ሕጉ ኮ ‘እንዲህ ካረጋቹ፣ ወይ ከተናገራቹ ትጠየቃላቹ፣ ትታሰራላቹ’ እኮ ነው የሚለው። ከዚህ የባሰ ማሸበር አለንዴ? ፀረሽብር ሕጉ ኮ አሸብሮናል። ስለዚህ ፀረሽብር ሕጉ አሸባሪ ነው። ለዚህም ነው ፀረ ሽብር ሕጉን የተቃወምኩት። ስለዚህ ፀረሽብር ሕጉን የተቃወምኩት ሽብር ስለምደግፍ ሳይሆን ሽብርን ስለምቃወም ነው።

ሌላው ፀረሽብር ሕጉ የምቃወምበት ምክንያት የወጣው የፀረሽብር ሕግ ወይ አዋጅ ሕገወጥ ስለሆነ ነው። እንዴት ሕገወጥ ይሆናል? የሕግ የበላይነት በሰፈነበት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ማንኛውም ሕግ ወይ አዋጅ ወጥቶ፣ ፀድቆ፣ ተግባራዊ የሚሆነው ከሕገመንግስቱ ዓንቀፆች የሚፃረር ሓሳብ እንደሌለው ሲረጋገጥ ብቻ ነው። የፀረ ሽብር ሕጉ ግን ከሕገመንግስቱ መሰረታዊ ሓሳቦች (ለምሳሌ የመናገር ነፃነት) ይጣረሳል። ስለዚህ የፀረሽብር ሕጉ ሕግ ሁኖ መውጣት አልነበረበትም፤ ከሀገሪቱ ሕገመንግስት ይምታታላ። ስለዚህ የፀረሽብር ሕጉ ሕገወጥ ነው። ሕገወጥ ለሆነ ተግባር ወይ አዋጅ መቃወም የሁሉም ሰው ዜግነታዊ ግዴታ ነው። እኔ ዜጋ ነኝ። ስለዚህ መቃወሜን ትክክል ነው።

ሌላው የተነሳ ነጥብ የሰለማዊ ሰልፍና የሽብር ተግባር እንዲሁም ዓመፅ መቀሰቀስ ቁርኝት ነው። እንደኔ ከሆነ ሰለማዊ ሰልፍና የሽብር ተግባር የሚገናኙ አይደሉም። ሰለማዊ ሰልፍ እንደስሙ ሰለማዊ ነው። ሰለማዊ ሰልፍ የዜጎች ዴሞክራሲያዊ መብት ነው። መንግስት የዜጎችን መብት የመንጠቅ ስልጣን የለውም።

መንግስት የዜጎችን መብት ማፈን ከጀመረ ዜጎች መብታቸውን ለማስከበር ሌላ የሃይል አማራጭ እንዲጠቀሙ እያስገደዳቸው ነው ማለት ነው። ዜጎች ሃይል ተጠቅመው መብታቸው የሚያስከቡርበት መንገድ ሽብር ወይ ዓመፅ ሊሆን ይችላል። ዜጎች ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብታቸው በመንግስት ከተከበረ ግን በሽብር ወይ ዓመፅ የሚሰማሩበት አጋጣሚ አነስተኛ ነው። ምክንያቱም ሁለንተናዊ መብታቸው ከተከበረ ሽብር ወይ ዓመፅ ምን ያስፈልጋል?

ስለዚህ ሽብር ወይ ዓመፅ የሚወለደው ሰለማዊ ሰልፍ ከመፍቀድ ሳይሆን ከመከልከል ነው። ሰለማዊ ሰልፍ የዜጎች መብት እስከሆነ ድረስ እደግፋለሁ። ስለማዊ ሰልፍ መፍቀድ ሽብርና ዓመፅ ያስቀራል እንጂ መንግስት እንደሚለው ችግር ይፈጥራል ብዬ አላምንም። ለዚህም ነው ስለማዊ ሰልፍን የምደግፈው።

በሌላው በኩል ጉዳዩ ከሶርያ ግጭት አያይዘውታል (በኢትቪም ተመሳሳይ ነጥብ ሰምቻለሁ)። የሶርያ ሁኔታ አስከፊ ነው። ማንም አይመርጠውም ብዬ አስባለሁ። ግን አንድ ስህተት አለ። የሶርያ ግጭትኮ የተነሳው ሰለማዊ ሰልፍ ስለ ተፈቀደ አልነበረም። ሶርያውያን ወደ አስከፊ የእርስበርስ ጦርነት የገቡት ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብታቸው ስለተጠበቀላቸው አልነበረም። ዓመፁ የተቀሰቀሰው የሰብአዊ መብት ጥሰት ስለነበረ ነው። የሰብአዊ መብት ጥሰት የነበረው አምባገነናዊ ስርዓት ስለነበረ ነው። የሽብርና ዓመፅ መነሻ አምባገነናዊ አገዛዝ ነው። ለዚህም ነው አምባገነናዊ አገዛዝን የምቃወመው። ምክንያቱም አምባገነናዊ አገዛዝ ሽብርና ህዝባዊ ዓመፅን ይወልዳል። ዓመፅም ብዙ ሰብአዊ ኪሳራ ያደርሳል።

ስለ እስላማዊ መንግስት መመስረትም ተነስቷል። እኔ እስላማዊ መንግስት ወይ ማንኝውም ሀይማኖታዊ መንግስት አልደግፍም። በዴሞክራሲያዊ እሳቤ መሰረት ሀይማኖትና ፖለቲካ መለያየት አለባቸው። የኢትዮዽያ ሙስሊሞች ጥያቄ ‘እስላማዊ መንግስት’ መመስረት ነው ብዬ አላምንም። ምክንያቱም ጥያቂያቸው ‘መንግስት በሀይማኖታችን ጣልቃ አይግባብን’ የሚል ነው። ‘መንግስት ጣልቃ አይግባባን’ ብሎ ማለት ፖለቲካና ሀይማኖት መለያየት እንጂ ሀይማኖታዊ መንግስት መመስረት አያሳይም።

እስላማዊ መንግስት መመስረት ቢፈልጉ ኑሮ ሰለማዊ ሰልፍ አይወጡም ነበር። እኔ እስከገባኝ ድረስ ሀይማኖታዊ ጥያቄ መሆኑ ነው፤ ይሄም እደግፋለሁ። ምክንያቱም መብታቸው ነው። እንደዉም ትእግስታቸው አደንቃለሁ።

በመጨረሻም

ሽብር ወይ ህዝባዊ ዓመፅ ፀረሽብር ሕግ በማውጣትና ሰለማዊ ሰልፍ በመከልከል ማስቆም አይቻልም። ሽብርን ለመታገል ፍትሕ፣ እኩልነት፣ ነፃነት ማስፈን አለብን። ህዝባዊ ዓመፅ ለማስቀረት ደግሞ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ማክበር የተሻለ አማራጭ ነው። ሽብርና ዓመፅ ሕግ አይገድበውም።

ፀረሽብር ሕጉን የምቃወመው ሽብርን ስለምቃወም ነው። ፀረሽብር ሕጉ ሽብርን የሚያፋፍም እንጂ የሚገታ አይደለም።

No comments:

Post a Comment