ከ33ቱ ፓርቲዎች የተሰጠ መግለጫ
በአሁኑ ወቅት መንግሥት የአዲስ አበባ የቤቶች ልማት ቁጠባ ፕሮግራምን ይፋ አድርጓል፡፡ በፕሮግራሙ መሠረት 1.3 ሚሊዮን የዋና ከተማው ነዋሪዎች ባጭር ጊዜ ውስጥ ዝግ የቁጠባ የሂሳብ ደብተር በመክፈት እንደ ፕሮግራሙ ዓይነት ይሳተፋሉ፡፡ ፕሮግራሙ የሚጠይቀው የገንዘብ መጠን 87 ቢሊዮን ብር ሊደርስ እንደሚችል ሲገመት ዝግ የቁጠባ ሂሳብ ደብተሩ የሚከፈተው ደግሞ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብቻ ነው፡፡ መንግሥት የግል ባንኮችን ከፕሮግራሙ ሙሉ በሙሉ አግልሏቸዋል፡፡
ይህ መግለጫችን መንግሥት የግል ባንኮችን ከፕሮግራሙ ሙሉ በሙሉ ያገለለበትና እድሉን በስሩ ለሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብቻ የሰጠበት እርምጃ በነፃ የገበያ መርህና በግል ባንኮች እንቅስቃሴ እንዲሁም በግሉ ሴክተር የደቀነውን አደጋ ይመለከታል፡፡
የሀገሪቱ ሕገ መንግሥት የሀገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት ፍልስፍና የነፃ ገበያ መርህ እንደሚከተል ይደነግጋል፡፡ ይህንንም ተከትሎ የግል ክፍለ ኢኮኖሚው ከተሳተፈባቸው በርካታና የተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች መካከል በፋይናንስ ዘርፉ የግል ባንኮች ይገኙበታል፡፡ በሀገሪቱ የኢኮኖሚ ታሪክ ቁጥራቸው የላቀ የግል ባንኮች ተከፍተው ሲንቀሳቀሱ የሚታዩትም ይህንኑ ሕገ መንግሥታዊ መብት መሠረት በማድረግ ነው፡፡
የግል ባንኮች የተቋቋሙት ከመነሻው ሁሉም ነገር በተመቻቸበት ሁኔታ አልነበረም፡፡ በሕግ ረገድ በር የተከፈላቸው ቢሆንም የባንክ አገልግሎት ፈላጊው የሕብረተሰብ ክፍል ለዘመናት በመንግሥት ስር የሚተዳደሩ ባንኮች ደንበኛ ሆኖ በመቆየቱ ሥነ-ልቡናው በግል ባንኮች ለመተማመን የተዘጋጀ ነበር ለማለት አያስደፍርም፡፡ የተዛባውን ሥነ-ልቡና ለማስተካከልና በባንክ አገልግሎት ፈላጊዎች ዘንድ አመኔታ ለማትረፍ የግል ባንኮች መጣር ነበረባቸው፡፡ ባለ አክሲዮኖችን፣ ገንዘብ አስቀማጭ ደንበኞችን፣ ተበዳሪ የግል ባለሀብቶችን ማሳመንና መሳብን ጨምሮ ፈጣን፣ ቀልጣፋና ተደራሽ አገልግሎት መስጠት፣ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት ማስተዋወቅ ከጥረቶቹ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ጥረቶቹም የተሳኩ መሆኑን ሕብረተሰቡ በአሁኑ ወቅት ስለ ግል ባንኮች ካለው ቀናና የተስተካከለ አመለካከት መገንዘብ ይቻላል፡፡
ከመንግሥት ባንኮች አንፃር በፋይናንስ ዘርፉ ድርሻቸው አነስተኛ ቢሆንም የግል ባንኮች ለአጠቃላይ ልማት ያበረከቱት አስተዋጽኦም ቀላል አይደለም፡፡ በአስር ሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች የሥራ እድል ፈጥረዋል፡፡ በበርካታ የሀገሪቱ አካባቢዎች ቅርንጫፎችን በመክፈት ዜጎችን የባንክ አገልግሎቶች ተጠቃሚዎች አድርገዋል፡፡ ለግል ባለሀብቶች ብድር በማቅረብና በቢሊዮኖች ብር የሚገመት ግብር ለመንግሥት በማስገባት የልማት ኃይልነታቸውን አረጋግጠዋል፡፡
ይህም ሆኖ ባንኮቹ ከመንግሥት ጋር የነበራቸው ግንኙነት አልጋ በአልጋ አልሆነላቸውም፡፡ መንግሥት በአንድ በኩል የገንዘብና የፋይናንስ ፖሊሲ አውጭ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የባንኮች ባለቤትም በመሆኑና የጥቅም ግጭት (Conflict of interest) እንደመከሰቱ የግል ባንኮችን ያስጨነቁ እርምጃዎችን ሲወስድ ታይቷል፡፡ የብድር ጣራ መወሰን፣ የወለድ ምጣኔ ማስቀመጥ፣ (የግል ባንኮች ለሀገራዊ ልማት ግዴታ እንዳለባቸው ቢረዱም) ከተቀማጭ ገንዘብ የቦንድ ግዢ ባንኮቹ ከፍተኛ የሚሉትን መጠን መወሰን፣ ነፋስ አመጣሽ ግብር (windfall tax) መጣል ሊጠቀሱ ይችላል፡፡ ከዚህም የተነሳ መንግሥት ሊወስድ ከሚችላቸው ሊተነበዩ ከማይችሉ የፖሊሲ እርምጃዎችና መመሪያዎች አንፃር የግል ባንኮች ሁሌም ከስጋት የተለዩ አይመስሉም፡፡ ይህንን ስጋታቸውን የሚያባብሰውና ግልጽ አደጋ የደቀነው ደግሞ መንግሥት ሰሞኑን ባወጣው የቤቶች ልማት ቁጠባ ፕሮግራም የግል ባንኮችን ማግለሉ ነው፡፡
ይህ የመንግሥት እርምጃ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ለግል ባንኮች የሚኖረው አንድምታ የተለያየ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ግንድ ባንክ ይህንን ግዙፍ ገንዘብ ለማንቀሳቀስ እድሉን ያገኘው በውድድር ብልጫ ሳይሆን በመንግሥት ፈቃድ ነው፡፡ ለወትሮውም ከፋይናንስ ሴክተሩ ከ8ዐ% የሚበልጥ ድርሻ ያለው ባንክ በዚህ ያለውድድር በተገኘ ግዙፍ ፋይናንስ የበለጠ እንዲገዝፍ እድሉ ተሰጥቶታል፡፡ ከግል ባንኮች አንፃር ሲታይ ደግሞ ወትሮውንም ዝቅተኛ የነበረውን የፋይናንስ ገበያ ድርሻቸውን በእጅጉ የሚያቀጭጭባቸው ይሆናል፡፡ይህ አደጋ በተጋረጠባቸው ሁኔታ ውስጥ ሆነውም የባንኮቹ ኃላፊዎች በጉዳዩ ዝምታን የመረጡ ይመስላል፡፡
ከፕሮግራሙ አንፃር የግል ባንኮቹ ያደረባቸው ስጋት በብዙ ረገድ የሚገለጽ ነው፡፡ የባንኮች ሕልውና ዋና መሠረት የደንበኞቻቸው ተቀማጭ ገንዘብ ነው፡፡ የደንበኞች ብዛት በጨመረ ቁጥር እድገታቸውም ከፍ ይላል፡፡ የባንኮች ፍላጎትና ይበልጡን የሚተጉትም ነባር ደንበኞቻቸው እንዲቆዩላቸውና አዳዲስ ደንበኞች ደግሞ በየጊዜው እንዲቀላቀሏቸው የሚያስችሏቸውን ዘመናዊ የባንክ አሰራሮች በመዘርጋት ነው፡፡ የአሁኑ ፕሮግራም ግን ባንኮች በጥረታቸው የሚያገኟቸውን አዳዲስ ደንበኞች ቀርቶ ነባሮቹንም ሊያሳጣቸው እንደሚችል ባንኮቹን ከስጋት ላይ ጥሏል፡፡ በፕሮግራሙ ለመሳተፍ በግል ባንኮች የቁጠባ ሂሳብ የነበራቸው ደንበኞች ከባንኮቹ ገንዘብ በማውጣት (ወደ ገበያ ሳያስገቡ) በንግድ ባንክ በዝግ የቁጠባ ሂሳብ ይከፍታሉ፡፡ የቁጠባ ሂሳብ ያልነበራቸው ቤት ፈላጊዎች ደግሞ በቀጥታ የንግድ ባንኩን በደንበኝነት ስለሚቀላቀሉ የግል ባንኮች በውድድር ሳይበለጡ በመንግሥት ውሳኔ ብቻ ነባሮችንም ሆነ አዳዲስ ደንበኞችን በሚያጡበት ሁኔታ ላይ ወድቀዋል፡፡ በዚህ የተነሳ የግል ባንኮቹ ተቀማጭ ገንዘብ ስለሚያጥራቸው ብድር ሰጥተው የሚያገኙት ገቢም በዚያው ልክ ያሸቆለቁልና በነፃ ገበያ መርህ መሠረት በውድድር በመሸነፋቸው ሳይሆን በመንግሥት እርምጃ የተነሳ አደጋው የማይቀርላቸው ይሆናል፡፡ የግል ባንኮችን ለኢንቨስትመንቱ የፋይናንስ ምንጭ ያደረገው ወይም የሚያደርገው አብዛኛው የግሉ ሴክተር ክፍልም ከጉዳቱ ሊያመልጥ አይችልም፡፡
መንግሥት ይህን ለግል ባንኮች አደገኛ የሆነ እርምጃ ለምን ለመውሰድ ፈለገ? ብሎ መጠየቅ አግባብነት አለው፡፡ የግል ባንኮች በዚህ ውሳኔ የተነሳ ምን ሊገጥማቸው እንደሚችል የሀገሪቱን ኢኮኖሚ እመራለሁ የሚል መንግሥት አልተገነዘበውም ከማለት ጠንቅቆ ያውቀዋል ማለቱ ይቀላል፡፡ ባንኮቹ ሊከተላቸው የሚችለውን ጉዳት መንግሥት ከተረዳስ ባንኮቹን በዚህ ፕሮግራም በማሳተፍ ከጉዳቱ ለመታደግ የሚያስችል የአሰራር ሥርዓት ለመዘርጋት የዐቅም ውስንነት ገጥሞታል ወይ? ቢባልም አያስኬድም፡፡ የግል ባንኮች ከተለያዩ የውጭ ሀገራት ባንኮች ለሚሰበስቡት የውጭ ምንዛሪ የእለት በእለት የመቆጣጠሪያ አሰራር ተግባራዊ ያደረገ መንግሥት በራሱ ዋና ከተማ ባሉ የግል ባንኮች በቤት ፈላጊ ዜጎች ተቀማጭ የሚደረገውን ገንዘብ ሥራ ላይ ለማዋልም ሆነ ለመቆጣጠር የሚያስችል አሠራር መዘርጋት ከብዶታል ለማለት አይቻልም፡፡ ግንዛቤውም ሆነ ዐቅም ባልጠፋበት ሁኔታ ግን መንግሥት ፍላጎት አለማሳየቱ መንግሥት በግል ሴክተሩ አስፈላጊነት ያለው እምነት ከፕሮፓጋንዳ ብዙም አለመዝለሉን ያመለክታል፡፡ ይህም የግል ሴክተሩ በመንግሥት ፖሊሲዎች ላይ እምነት እንዲያጣ ስለሚገፋፋ ለግሉ ኢንቨስትመንት በር ሊዘጋ ይችላል፡፡ የሀገሪቱ ኢኮኖሚም በመንግሥት ሞኖፖሊ ሥር መውደቅ ግድ ይሆንበትና ሕገ-መንግሥታዊው የነፃ ገበያ ሥርዓት በመንግሥታዊ ካፒታሊዝም ሊተካ ይችላል፡፡
ይህ አካሄድ የግል ባንኮቹን ከመጉዳት አልፎ በሐገሪቱ ኢኮኖሚና ፖለቲካ ላይ የራሱ አሉታዊ ተጽእኖ ያለው ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ እውቅና ያገኘው በውድድር ላይ የተመሠረተ የነፃ ገበያ መርህ በፋይናንስ ዘርፍ በመንግስታዊ አሠራር የተነሳ ተገፍቷል፡፡ የኢኮኖሚ እድገት አቅጣጫውም የግል ክፍለ ኢኮኖሚው መጫወት ለሚገባው ገንቢ ሚና በር የሚከፍት ሳይሆን መንግሥት በኢኮኖሚ የሚኖረውን የተዛባና የገዘፈ የበላይነት ሊያስከትል የሚችል ነው፡፡ የግዙፍ የፋይናንስ ዐቅም የበላይነት የጨበጠ መንግሥት ደግሞ በፖለቲካውም የበላይነቱን ለሁሌም ለማረጋገጥ ስለሚሻ የአንድ ፓርቲ ሥርዓት ተመልሶ ይመጣል ማለት ነው፡፡ በሂደቱም ሆነ በውጤቱ ደግሞ በሕገ-መንግስቱ የተደነገገው የመድብለ ፓርቲ የፖለቲካ ሥርዓት ግንባታ ካሁኑ በባሰ አደጋ ላይ ይወድቃል፡፡
ከላይ ከተጠቀሰው አደጋ አንፃር የግል ባንኮቹም ሆነ መንግሥት ኃላፊነት ያለባቸው በመሆኑ፡-
1) የባንኮቹ ኃላፊዎች ከገቡበት ዝምታ ተላቅቀው የአደጋውን ጥልቀትና ስፋት ለሕዝብና ለባለ አክሲዮኖቹ በይፋ ማሳወቅና ከመንግሥትና ባለድርሻዎች ጋር ውይይት እንዲደረግ እንዲጠይቁ፤
2) የግሉ ክፍለ-ኢኮኖሚ ተዋናዮችን የሚወክሉ የንግድና ዘርፍ እንዲሁም የኢንቨስተሮች ማኅበራት እግሩ በአባላት እንቅስቃሴ ላይ የሚያሳድረውን አሉታዊ ተጽዕኖ ለመንግሥት በማሳወቅ የመፍትሔ ውይይት እንዲያደርጉ፤
3) ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው እንደ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ማኅበር የመሳሰሉ የሙያ ማኅበራትም በጉዳዩ ላይ ለባለድርሻ አካላት መረጃና የመፍትሄ ኃሳብ እንዲያቀርቡ፤
4) መንግሥትም በበኩሉ የግል ባንኮቹን የሚገጥመው ጉዳት በኢኮኖሚውና በቀጣይ የግል ኢንቨስትመንት የሚኖረውን የከፋ ተጽእኖ በማጤን በጉዳዩ ላይ ከግል ባንኮችና ባለድርሻአካላት ጋር የውይይት መድረክ በማመቻቸት እንዲመክርበትና የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስድ፤
ጥሪያችንን እንቀርባለን፡፡
ጤናማና ቀጣይነት ያለው ልማትና ዕድገት በፍትሃዊና አሳታፊ የነጻ ገበያ ውድድር ይረጋገጣል!
ሰኔ 20 ቀን 2ዐዐ5 ዓም
አዲስ አበባ
No comments:
Post a Comment