ኢሳት ዜና :-አንድነት ፓርቲ የሶስት ወራት የህዝባዊ እንቅስቃሴ የትግል ስልቱን ይፋ ማድረጉን ተከትሎ የህዝባዊ ንቅናቄው የመጀመሪያ የአደባባይ ላይ ሰላማዊ ሰልፍም በጎንደር ከተማ ሰኔ 30/10/2005 እንደሚያደርግ አስታውቋል -፡
በሰላማዊ ሰልፉ ላይ ” በጎንደር እየተፈጸመ ያለውን የመልካም አስተዳደር ችግር፣ ሰዎችን በአደራ ማሰር፣ ለሱዳን ከህዝቡ እውቅና እና ፈቃድ ውጪ መሬት መሰጠቱን፣ በነጋዴዎች ላይ የሚፈጸመውን ኢ-ፍትሃዊ አሰራር፣ ለስራ የደረሱ ወጣቶች የፓርቲ አባል ካልሆኑ በስተቀር ስራ የማያገኙበትን ሁኔታ፣ በዘር ላይ የተመሰረተን ማፈናቀልና የኑሮ ውድነትን አስመልክቶ ህዝቡ የተቃውሞ ድምጹን በነቂስ ወጥቶ ” እንደሚያሰማ ለኢሳት በላከው መግለጫ ይፋ አድርጓል፡፡ ብዙ ሺ የከተማው ኗሪዎችም የተቃውሞ ፊርማቸውን ያኖራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ፓርቲው ገልጿል።
ሰላማዊ ሰልፉን በጎንደር ከሚገኙ የፓርቲው አባላትና አመራሮች ጋር የተሳካ ለማድረግ አዲስ አበባ ከሚገኘው ዋና ቢሮ አስተባባሪ አባላት የተላኩ ሲሆን የቅስቀሳ ስረቸውን መጀመራቸውን፣ የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ፣ የብሄራዊ ምክር ቤትና በየመዋቅሩ ያሉ አባሎች በሰላማዊ ሰልፉ ላይ ለመገኘት ወደ ጎንደር እንደሚያመሩ አክሎ ገልጿል።
ሰላማዊ ሰልፉ ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓት ጀምሮ ጎንደር ከሚገኘው የአንድነት ፓርቲ ቅርንጫፍ ቢሮ ተነስቶ ወደ መስቀል አደባባይ በማምራት በመስቀል አደባባይ በሚደረግ ልዩ ልዩ ፕሮግራም የሚጠናቀቅ ይሆናል፡፡ በጎንደር መስቀል አደባባይ ለሚገኘው ህዝብ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮችና ታዋቂ ግለሰቦች የሰላማዊ ሰልፉን ዓላማ የሚገልፅ ንግግር እንደሚያደርጉም ታውቋል።
የሰሜን ጎንደር ዞን የአንድነት ፓርቲ ተወካይ የሆኑት ለኢሳት እንደተናገሩት ሰኔ 30 ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ማቀዳቸውን ለዞኑ ፖሊስ ጽህፈት ቤት፣ ለዞኑ አስተዳዳር እና ለዞኑ ከንቲባ ጽህፈት ቤት ደብዳቤ ቢያስገቡም ሁለቱ ሲቀበሉ፣ የዞኑ ከንቲባ ጽህፈት ቤት ለመቀበል ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል ። ያም ሆነ ግን ህጉ ማሳወቅ እንጅ ፈቃድ የማይጠይቅ በመሆኑ ሰላማዊ ሰልፉ ይካሄዳል ብለዋል
No comments:
Post a Comment