ኢትዮጵያዊነት – ”የለህም ይሉኛል፤ እውነት የለሁም ወይ?”
ከመስፍን ነጋሽ (ጋዜጠኛ)
(የቀድሞው አዲስ ነገር ጋዜጣ አዘጋጅ)
(የቀድሞው አዲስ ነገር ጋዜጣ አዘጋጅ)
ከማንነት ጋራ የተያያዙ ጥያቄዎች፣ ሙግቶች፣ በተቃራኒውም አስቀያሚ ሐሳብ አልባ ስድድቦች ሰሞኑን በርከትከት ብለዋል። ጥያቄዎቹና ሙግቶቹ መኖራቸውን አጥብቄ እደግፈዋለሁ። በእኔ እይታ አብዛኞቹ ምልልሶች ወይም ሙግቶች በመሠረቱ አዲስ ጭብጥም ሆነ መከራከሪያ አላቀረቡም። ቢሆንም የነበረውንም ቢሆን በአግባቡ በተደጋጋሚ እያነሱ ሐሳብ መለዋወጡ ጠቃሚ ነው፤ ሙከራው ቢያንስ እርስ በርስ መተዋወቅን ይጨምራል፤ አልፎም አዲስ ሐሳቦችን ለማፍለቅ እድል ይሰጣል።
የማነ ናግሽ ኢትዮጵያዊ የሚባል ማንነት የለም፤ ያለው በብሔረሰብ ላይ የተመሰረተ ማንነት ብቻ ነው የሚለውን ሐሳብ በትግሪኛ ጽፎት ተመልክቼ ነበር። ኃላም ራሱ ወደ አማርኛ እንደመለሰው ይህን ጽሑፍ ወደማጠናቀቁ ስቃረብ ተመልክቻለሁ። በመሠረቱ ሐሳቡ አዲስ አይደለም። በየማነ አስተያየት መነሻነት ሌሎችም አመለካከታቸውን አካፍለዋል፤ ጥቂቶቹን በሚገባ አንብቤያለሁ። በሒደቱ የታየው ጉዳዩን ከመመርመር ይልቅ ተናጋሪውን የማጥቃት ስልት ጠቃሚ ስላልሆነ ወደዚያ አንመለሰም። በሐሳቡ ላይ ግን አስተያየቴን ላካፍል።
1. ስለማንነት እንደ መነሻ
ሁልጊዜም ከጥንቱና ከስሩ መጀመር ጠቃሚ ቢሆንም ጽሑፌን ወደ መጽሐፍ ምእራፍነት እንዳይቀይረው በመስጋት፣ ከዚያ በላይ ደግሞ አንባቢዎቼ ስለማንነት እና ስለፖለቲካው መሠረታዊ ጉዳዮች ያውቃሉ ከሚል እምነት ስለማንነት ወደመዘርዘር አልገባም። በምትኩ ለክርክሬ የሚሆኑኝን መነሻዎች ብቻ እጠቅሳለሁ። አምስት ጭብጦች ላስይዝ፤
1.1. አንድ ሰው ብዙ አይነት ማንነቶች ሊኖሩት ይችላሉ፤ ይኖሩታልም። አንድ ማንነት በጉልህ የሚታየው ከሌላው ጋራ ሲነጻጸር እንደመሆኑ መጠን፣ አንድ ሰው ማንነቱን የሚገልጽበት መንገድ እንደሁኔታው ይለያያል። ጥያቄው ሃይማኖትን ሲከተል፣ ሃይማኖታዊ ማንነቱን ያስቀድማል እንደማለት። እዚህ የምናነሰው ግን ቋንቋን ጨምሮ ከተመሳሳይ ባህል፣ ታሪክ እና ስነልቦና ጋራ ስለተቆራኘው ማንነት ነው። የማንነት ፖለቲካ በአገራችን በዋናነት የሚወከለውም በዚሁ ነው። ለውይይታችን እንዲረዳ በብሔረሰባዊ እና በአገራዊ ማንነት ላይ ብቻ እናተኩር።
1.2.ማንነት (ብሔረሰባዊም ይሁን አገራዊ) ማኅበረሰብ ሠራሽ ነው፤ ተፈጥሯዊ አይደለም። ማንነት ከቤተሰብ፣ ከማኅበረሰብና ከትምህርት ቤት የምንማረው ነው። ስለዚህም ባለበት አይረጋም፤ መጠነኑና ፍጥነቱ ቢለያየም ይለወጣል።
1.3.ማንነት በአጋጣሚ በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ በመወለድ እና/ወይም በማደግ፣ አለዚያም በተጽእኖ ሊገኝ ወይም ሊለወጥ ይችላል። ይህ ብቻ ግን አይደለም። ማንነት በምርጫም ሊገኝ ይችላል፤ አንድ ሰው በፍላጎቱ የአንድ ማንነት አካል ሊሆን ይችላል፤ ምን ያህል ይሳካለታል የሚለውን የሚወስኑ ብዙ ከእርሱ ውጭ የሆኑ ሁኔታዎች ቢኖሩም። አንዳንድ ማኅበረሰቦችና ማንነቶች ከሌላው የበለጠ አዲስ መጤን የመቀበልና የማዋሐድ ጠባይ አላቸውና።
1.4. አንድ ማንነት ከቀላል ጀምሮ ወደ ውስብስብና ብዙ እንደሚያድግ ሁሉ፣ ማንነቶች ሊወራረሱ፣ አልፎም ማንነቶች ተደባልቀው/ተዋሕደው ”አዲስ/የተለየ” ማንነት ሊፈጥሩም ይችላሉ።
1.5. በማንኛውም መንገድ መስተጋብር የመፍጠር እድል ያገኙ ማንነቶች የተለያዩ እሴቶቻቸውን ይለዋወጣሉ፣ ይዋዋሳሉ፣ ያዳቅላሉ። እንዳለ የሚያስጠብቁት የማንነታቸው አካል መኖሩ እንደማይቀርም እሙን ነው። ስለዚህም ንጹህ የሚባል ማንነት አይኖርም። ንጹሕ የሚባል ማንነት ካለ ያ ማንነት በላቦራቶር የተፈጠረና እስካሁንም ወደምንኖርባት የሰው ዓለም ያልመጣ ማንነት ነው።
1.5. በማንኛውም መንገድ መስተጋብር የመፍጠር እድል ያገኙ ማንነቶች የተለያዩ እሴቶቻቸውን ይለዋወጣሉ፣ ይዋዋሳሉ፣ ያዳቅላሉ። እንዳለ የሚያስጠብቁት የማንነታቸው አካል መኖሩ እንደማይቀርም እሙን ነው። ስለዚህም ንጹህ የሚባል ማንነት አይኖርም። ንጹሕ የሚባል ማንነት ካለ ያ ማንነት በላቦራቶር የተፈጠረና እስካሁንም ወደምንኖርባት የሰው ዓለም ያልመጣ ማንነት ነው።
ከዚህ የሚከተለው ክርክሬ ቢያንስ በእነዚህ አምስት መንደርደሪያዎች ላይ የተመሠረተይሆናል።እነዚህን መነሻዎች ይዘን ወደ ጥያቄው እንመለስ።እውነት ኢትዮጵያዊ ማንነት የለም?
በአገራችን የብሔረሰብ ማንነት አለ፤ ራሱን የዚህ ወይም የዚያኛው ብሔረሰብ አባል አድርጎ የሚመለከት ሰውም አለ። ይሄ ለክርክር የሚቀርብ፣ ያልተረጋገጠ ጉዳይ አይደለም። ይህኛው ቡድን ”ብሔርሰብ ነው ወይስ ዘውጌ ወይስ ጎሳ?” የሚለው ጥያቄ ላነሳነው ክርክር አስፈላጊ አይደለም። ለአሁኑ፣ ቁም ነገሩ፣ የራሳችን ባህላዊና ታሪካዊ ማንነት አለን የሚሉና ያላቸው ብድኖች መኖራቸው ነው። ስለዚህ ”እኔ የእገሌ ብሔረሰብ አባል ነኝ፤ የዚያኛው አይደለሁም፤ ማንነቴም አገው፣ ትግራዋይ፣ ጉሙዝ፣ ኦሮሞ፣ አማራ…ነው” የሚሉ ሰዎች አሉ። መኖራቸው እውነት ነው፤ በአግባቡ ከተያዘም ጸጋ ነው። አሁን የቀረበው ጥያቄ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት እነዚህ ብሔረሰባዊ ማንነቶች ብቻ ናቸውን የሚል ነው። ወይም፣ ኢትዮጵያዊ ማንነት የለምን? እርግጥ የአንድ ማንነት ታጋሪዎች ነን የሚሉ ሰዎች እስካሉ ድረስ ስለማንነቱ ለማረጋገጥ ሌላ ምርመራ ማድረግ የግድ አይደለም ብሎ የሚከራከር ይኖር ይሆናል። በዚህ ስሌት፣ ”ኢትዮጵያዊ ማንነት አለን” የሚሉ ሰዎች መኖራቸው ብቻውን በቂ ማስረጃ በሆነ ነበር። ቢሆንም ተጨማሪ ሐሳቦችን መለዋወጡ አይጎዳም።
2. ኢትዮጵያዊ/አገራዊ ማንነት የለም የሚሉ ሰዎች ቢያንስ አራት ስሕቶችን ይፈጽማሉ።
2.1. ከፍ ሲል የጠቀስኩትን የማንነቶችን መወራረስ፣ አልፎም የአዲስ ማንነቶች መፈጠር አይቀበሉም። ይህ ማለት በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙት ብሔረሰቦች (የፖለቲካ ማኅበረሰቡ አባል የሆኑት ወደውም ይሁን ተገደው) በታሪክ ባካሔዱት መስተጋብር የሁሉም ”ቅልቅል” የሆነ (ምናልባትም የሆኑ) አዲስ ማንነቶች ሊፈጠሩ እንደሚችሉ አይቀበሉም ማለት ነው። አዳዲስ ማንነቶች ሊፈጠሩ ይችላሉ ብለው ካመኑ ክርክራችን በአገራችን አዲስ ማንነቶች ስለመፈጠራቸው እና ስለተፈጠረው/ስለተፈጠሩት አዲስ ማንነቶች ስያሜ ይሆናል ማለት ነው። በእኔ እምነት፣ በረጅሙና በውስብስቡ የአገረ ኢትዮጵያ መስተጋብር አዳዲስ ማንነቶች ተፈጥረዋል። (ይህ ማለት የብሔረሰብ ማንነቶች ጠፍተዋል ማለት አይደለም፤ እርግጥ ባሉበት አንዳችም ሳይለወጡ ቀጥለዋል – ንጽሕ የሚለው ቁልምጫ ትርጉሙ እርሱ ይመስላል- ማለትም ቢያንስ ፖለቲካዊ የዋህነት ይሆናል።) ከተፈጠሩት ”አዲስ/የተለዩ” ማንነቶች አንዱና ዋናው ብዙዎቻችን ”ኢትዮጵዊነት” የምንለው ማንነት ነው። ስለዚህ ማንነት አይነቶች ወይም አረዳዶች ወደ ኋላ አነሳለሁ፤ የችግሩ መነሻ ”ኢትዮጵያዊነት” የሚለው ስያሜ ለተለያዩ ሰዎች የተለያየ ትርጉም መስጠቱ ሊሆን ይችላልና።
2.2. ተከታዩ ስህተት አንድ ሰው ከአንድ በላይ ማንነት ሊኖረው አይችልም፣ አንዱን ማንነት ሲቀበል ሌላውን መተው አለበት፣ ወይም የቀደመ ማንነቱን ከአዲስ ማንነት ጋራ ማዳበል ወይም ማዋሐድ አይችልም ከሚል የተሳሳተ አመለካከት የሚመነጭ ነው። ይህ በንድፈ ሐሳብም ሆነ በተግባር የተሳሳተ ነው። አሁን ያለችውን ኢትዮጵያ ተጨባጭ እውነታም መረዳት ይጎድለዋል። ዛሬ፣ ራሳቸውን በብሔረሰባዊም በአገራዊ ማንነታቸውም የሚገልጹ በሚልዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያላቸው ሰዎች አሉ። ልብ በሉ፣ ለእነዚህ ሰዎች ኢትጵያዊነት ዜግነት ብቻ አይደለም፣ ማንነትም ጭምር ነው። ራስን በብሔረሰብ ማንነት ብቻ ሳይሆን በሃይማኖት ማንነትም ደርቦ መግልጽ እንደሚቻለው፣ ኢትዮጵያዊነትን ተጨማሪ ማንነት ማድረግ እውነት የማይሆንበት ምክንያት አይታየኝም። ብሔረሰባዊም አገራዊም ማንነት ያለቸው ሰዎች ስለመኖራቸው ማረጋገጥ ከባድ አልመሰለኝም። አገራዊ ማንነት የለንም የሚሉ ሰዎችን የግድ ይኑራችሁ ብዬ አልከራከርም። ዝርዝሩ ሌላ ውይይት ይፈልጋልና ልተወው።
2.3. ኢትዮጵያዊ ማንነት የለም የሚሉት ሰዎች የሚሰሩት ሌላው ስሕተት ከፍትሕ ጋራ የተያያዘ ነው። እነርሱ ታሪካዊቷ ኢትዮጵያ ”ማንነታችንን ሳታከብር ኖራለች፣ እውቅና ተነፍገን ኖረናል፣ ይህም ሊለወጥ ይገባል” ብለው ይከራከራሉ። ተገቢና እውነት ያለው የፍትሕ ጥያቄ ነውና ከልቤ እደግፈዋለሁ። ይህን እነርሱ የሚጠይቁትን ፍትሕ ግን ለሌሎች፣ ዛሬ ኢትዮጵያዊ የሚባል ማንነት አለን ለሚሉትን ወገኖቻቸው እየከለከሉ ነው። አሁንም ስለዚህ ኢትዮጵያዊ ማንነት ወደ ኋላ አነሳለሁ።
2.4. እነዚህ ሰዎች ከሚሰጡት ማብራሪያ የምንረዳው ሌላው ጭብጥ እውነተኛው/ደንበኛው ማንነት በብሔረሰብ ላይ የተመሰረተው ነው የሚል ነው። እነርሱ ባወጡት የማንነቶች ደረጃ መሠረት፣ ከብሔረሰባዊ ማንነት ውጭ ያሉት ማንነቶች አንድም ውሸት ናቸው አለዚያም ጠንካራ አይደሉም። ብሔረሳባዊ ማንነት ከሌሎቹ ማንነቶች ቀዳሚነት እንዳለው ይሰብካሉ። ይህንን ለፖለቲካ መቀስቀሻነት የሚጠቀሙት ሰዎች ዓላማ የተሰወረ አይደለም። ሐሳቡ ግን በግማሽ እውነት ላይ የተመሰረተ ስንኩል መከራከሪያ ነው። ግለሰቦችና ቡድኖች የሚያስቀድሙት የማንነት መለያ የሚወሰነው በኖሩበትና ባሉበት ታሪካዊ ሁኔታ እንጂ አስቀድሞ በወጣ የማንነቶች ደረጃ አይደለም። ከሌላው ማንነቱ በፊት በሃይማኖታዊ ማንነቱ ራሱን የሚገልጽ ሰው/ቡድን ይኖራል፤ ለሌላው ደግሞ ብሔረሰባዊ አለዚያም አገራዊ ማንነቱን ቀድሞ ይሰማው ይሆናል። ሁሉም የማኀበረሰባቸው ታሪክ ውጤቶች ናቸው። አንዱ ከሌላው የበለጠ ትክክል አይደለም፤ እንደ ግለሰቡ እና ቡድኑ ሊለያይና ሊለዋወጥ የሚችልም ነው። ይህ አመለካከት አንዳንድ ጊዜ ብሔረሰባዊ ማንነታቸውን የማያስቀድሙ ሰዎችን ”የማንነት ችግር” እንዳለባቸው ወይም እየዋሹ እንደሆነ የመክሰስ ድፍረት ተላብሶ የሚታይበት ጊዜም አለ።
3. ኢትዮጵያዊነቶች?
እንደማንኛውም ማንነት ኢትዮጵያዊነትም ብዙ ገጽታዎች አሉት። በታራካዊ ሂደቶችም ብዙ ተለውጧል፤ ገና ይለወጣልም። ኢትዮጵያዊ ማንነት ብዙ ገጽታዎች አሉት ወይም ብዙ አይነት ኢትዮጵያዊ ማንነቶች አሉ ብሎ መነሳት ይቻላል። ለዚህ ጽሑፍ አግባብነት አላቸው ያልኳቸውን ሦስት የኢትዮጵያዊ ማንነት አረዳዶች ብቻ ላስቀምጥ።፡ይህን የማደርገው፣ ኢትዮጵያዊ የምንለው ማንነት ለተለያዩ ሰዎች የተለያየ ትርጉም እየሰጠ አለመግባባት ፈርሮ እንደሆነ በሚል መነሻ ነው። ለመግባባት ሲባል ለማንነቶቹ ሌላ ስያሜም መስጠት እንችል ነበር፣ ለጊዜው ይቆየን።
3.1. አንደኛው ኢትዮጵያዊ ማንነት ራሱን የሁሉም የአገራችን ብሔረሰቦች አካል አድርጎ ይመለከታል፤ ለአንዱ የተለየ ቅርበት አይሰማውም። እነዚህ ሰዎች ምክንያቱ ምንም ይሁን፣ ራሳቸውን የዚህ ወይም የዚያኛው አንድ ብሔረሰብ አባል አድርገው አይቆጥሩም። የዚህ ማንነት ባለቤት የሆነው ኢትዮጵያዊ፣ በአገሪቱ ውስጥ የሚገኝ ማንኛውም ነገር እኩል ተጋሪ ባለቤት እንደሆነ ያምናል። ብሔረሰባዊ ማንነትን ያከብራል። ብሔረሰባዊ ማንነትን ተገዳዳሪው አድርጎ አይፈራውም። ይህ ማንነት ድንገት ከሰማይ ወርዶ የሁሉም አካል ነኝ የሚል፣ ባለቤት አልባ ማንነት አይደለም። በአብዛኛው በተለይ በከተሞች አካባቢ ያደጉ (ለረጅም ጊዜ የኖሩ) ሰዎች የዚህ ማንነት ተጋሪዎች ናቸው። ባህላዊና ስነልቦናዊ ማንነታቸውን የቀረጸው ያለፉበት ታሪክ ነው፤ ፖለቲካው፣ ጦርነቱ፣ የሕዝብ እንቅስቃሴውና መስተጋብሩ፣ ትምህርቱ፣ የከተሜ ኑሮ…። ለእነዚህ ሰዎች ኢትዮጵያዊነት ዜግነት ብቻ ሳይሆን ማንነትም ጭምር ነው። ቁጥር የበለጠ ትርጉም የሚሰጣቸው ሰዎች ካሉ፣ የዚህ ማንነት ባለቤቶች ቢያንስ በሚልዮኖች የሚቆጠሩ ስለመሆናቸው አልጠራጠርም። (እኔም ራሴን ያገኘሁት እና መሆንም የመረጥኩት እዚህ ውስጥ ነው።)
3.2. ሁለተኛው ኢትዮጵዊነት የአንድ ብሔረሰብ ማንነት ያለው፣ ነገር ግን በተጨማሪም ኢትዮጵያዊ ማንነት ያለው ነው። በብሔረሰብ ማንነቱ የብሔረሰቡ የሆነውን ሁሉ ይጋራል፤ እዚያ ግን አያቆምም፤ በኢትዮጵያዊ ማንነቱ ከሎሎች ኢትዮጵያዊ ማንነት ካላቸው ጋራ የሚጋራው ሌላም ብዙ ነገር አለ። ይህ ሰው የሚረዳው ኢትዮጵያዊ ማንነቱ፣ ብሔረሰባዊ ማንነቱን እንዲተው የሚጠይቅ አይደለም። ይህ ማንነት፣ ከከተሞች መስፋፋት፣ ከትምህርትና ከመንግሥት ቢሮክራሲ ዝርጋታ ጋራ እያደገ እንደመጣ እገምታለሁ። አሁንም የዚህ ቡድን አባላት ቁጥር ከአገሪቱ ሕዝብ ከግማሽ በላይ እንደሚሆን አልጠረጥርም። ይህ ባይሆን አገሪቱ ህልውናዋ ባከተመ ነበር ከሚል መነሻ።
3.3. ሦስተኛው ኢትዮጵያዊነት፣ ብሔረሰባዊ ማንነትን የሚክድ ወይም ለማጥፋት የሚፈልግ ተጻራሪ ማንነት አድርጎ የሚመለከት አረዳድ ነው። ከታሪክ አንጻር በከፊል እውነት ነው። ለዚህ አረዳድ፣ ኢትዮጵያዊነት ማለት የክርስቲያን ሰሜን ኢትዮጵያ ባህልና ማንነት ነው። እንደ ጉዳዩ አቅራቢ ይህ ኢትዮጵያዊነት የአማራ ባህልና ማንነት ብቻ ተደርጎ የሚቀርብበት አጋጣሚም አይጠፋም። ለዚህ አመለካከት አስፈላጊው ጭብጥ ግን፣ ”ኢትዮጵያዊ” ማንነት ቀድሞም ይሁን አሁን ሌሎች ባህላዊ ማንነቶችን ለመደፍጠጥ ያሰፈሰፈ ማንነት ተደርጎ መታየቱ ነው። ይህ መሠረተ ቢስ ስጋት ነው ብዬ እንዳልደመድም እነርሱ ”ኢትዮጵያዊነት” ከሚሉት ውጭ ያለ አገራዊም ሆነ ብሔረሰባዊ ማንነት እንዲጠፋ አዋጅ ማወጅ የሚቃጣቸው ሰዎች አሉ። ማለት የምችለው፣ የእኔ ኢትዮጵያዊነት ከዚህ ይለያል። ይህ የኢትዮጵያዊ ማንነት አረዳድ የብሔረሰብ ማንነቶችን የማያከብር፣ ስለመኖራቸውም ሙሉ እውቅና የማይሰጥ ነው። ይህ ኢትዮጵያዊነት ብሔረሳባዊ ማንነቶችን በጥርጣሬ ይመለከታል፣ የአገራዊ መተሳሰር ጠላቶች አድርጎ ይፈርጃል፣ ማንነቶቹን ማዳከምም ይፈልጋል። የዚህ ማንነት አቀንቃኞች በአብዛኛው በአማራ ልሒቃን መካከል የሚገኙ ጥቂቶች ናቸው። እንዳለመታደል ሆኖ ኢትዮጵያዊ ማንነት በዚህ ገጽታው ብቻ ሲወከል ይስተዋላል።
ህወሓት/ኢሕአዴግ በስልጣን ዘመኑ የመጀመሪያ አስር ዓመታት ሆን ብሎ ሁሉንም ኢትዮጵያዊነቶች በጅምላ እንዲጠሉ ብዙ ሰርቷል። ሌሎቹ ብሔረሰብ ተኮር ፓርቲዎችም ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ስትራቴጂ ተከትለዋል። ስጋታቸው ግልጽ ነው፤ የብሔረሰባቸው አባላት ኢትዮጵያዊ ማንነትን ከደረቡ የደጋፊ መጠናቸው ሊቀንስ ይችላል። በውጤቱም፣ ዛሬ፣ ”ኢትዮጵያዊ ማንነት” ሲባል በብዙ የአደባባይ ሰዎች ዘንድ አስቀድሞ የሚጠቀሰው ይህ ሦስተኛው አመለካከት ብቻ ሆኗል። የፖለቲካ ልሒቃኑ ኢትዮጵያዊነትን በቀዳሚዎቹ ሁለት መልኮቹ የሌለ በማስመሰልም፣ ሦስተኛውን ግን በማጉላት፣ የማንነቱን ባለቤቶች በጅምላ ጥፋተኞችና ተጠርጣሪዎች አስመስለው ያቀርቧቸዋል። ይህ ስህተት ብቻ ሳይሆን ሸፍጥም ነው። የሸፍጥነቱ ስላቅ ወደዜኒቱ የደረሰው፣ እነመለስ ደርሶ የሁለተኛው ዓይነት/አረዳድ ኢትዮጵያዊነት (3.2) አራማጆች ሆነው፣ ባንዲራ መስቀልና ስለሺህ ዓመት የኢትዮጵያ ታሪክ መስበክ ሲጀምሩ ነበር። ሌላው በጣም የሚገርመኝ ነገር፣ የመጀመሪያው ዓይነት ኢትዮጵያዊ ማንነት ያላቸው ዜጎች መኖራቸውን ገዢው ፓርቲ ጭምር ዛሬም ድረስ እውቅና ለመስጠት መፍራታቸው ነው።
ብሔረሰባዊ ማንነትን የፖለቲካቸው ማቀጣጠያ አድርገው መጠቀም የሚፈልጉ ልሒቃን፣ እንዲሁም ከማንነት ፖለቲካና የውድድር ስሜት የሚመጣው ስሜተ-ስሱነት የሚያስከትለውን ሚዛን የመሳት አደጋ ቀድመው ያልጠረጠሩ ሰዎች፣ በአገራችን ውስጥ ያሉት ብሔረሰባዊ ማንነቶች ብቻ ናቸው ይላሉ። ይግረማችሁ በማለትም፣ ኢትዮጵያዊ ማንነት የለም ይላሉ።
ማንኛውም ማንነት እና ከእርሱ ጋራ ተያይዘው የሚመጡ ስሜቶች (የኩራት-ሃፍረት፣ የበላይ-የበታችነት፣ የአሸናፊ-ተሸናፊነት፣ የጊዜው የእኛ ነው-አይደለም፣ የተስፋ-ስጋት ወዘተ) መኖራቸውን ማስቀረት ባይቻልም መጠናቸውን ሲያልፉ ከፍተኛ አደጋን ይጋብዛሉ። አደጋው ሐልዮታዊ ብቻ ሳይሆን ማኅበረሰባዊም ነው። በሐልዮት ደረጃ፣ አሁን እንደምናየው፣ ”ያለሁት እኔ ነኝ እንጂ አንተ አይደለም” እስካማስባል ያደርሳል። አገራችንም ሆነች ዓለማችን በዚህ መሰሉ ሚዛኑን የሳተ የማንነት ስሜት ብዙ ዋጋ ስለመክፈላቸው ታሪክ ብዙ ያስነብበናል። አገራዊ ማንነት ሲጦዝ ሌላውን አገር በእብሪት ወደ መውረር ስካር ያመራል፤ በቆዳ ቀለም መኩራት (የሚያኮራ ከሆነ) ከዚያ አልፎ የበላይነት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ሆኖ ሲወሰድ ወደ አፓርታይድ ያደርሳል፤ በብሔረሰባዊ ማንነት ኮርቶ ራስን ማስተዳደርና ባህልን ማዳበር ከዚያ አልፎ የሌላውን (በተለይ ተፎካካሪ ተደርጎ የሚቆጠረውን) ማንነት መኖርና አለመኖር (በሐልዮትም ይሁን በአካል) ለመወሰን ወደሚያስችል ስልጣንነት ሲቀየር የመጠፋፋት በር ማንኳኳቱን ልብ እላለሁ፤ እሰጋለሁም።
ማንኛውም ብሔረተኝነት በጋራ ታሪክና መጻኢ እጣ ሚዛን መገደብ አለበት። ይህ ካልሆነ፣ ገደብ አልባ በራስ የመተማመን እና የእርግጠኝነት ስሜት ይፈጥራል። ትህትናንና መተሳሰብን ከግለሰብ ልብ፣ ከቡድን የጋራ ስነልቦና ያጠፋል። ይህ ስሜት በግለሰብም በቡድንም ደረጃ ሊንጸባረቅ ይችላል።
ኢትዮጵያዊ ማንነት አለ። ኢትዮጵያዊ ማንነት የሚለው አገላለጽ የሚወክለው መጥፎ የታሪክ አሻራም አለ። የመጥፎው አሻራ ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያዊነት አረዳድ በሒደት እየተዳከመ መሔዱ ግልጽ ነው። ምኞቴም ነው። ሌሎቹ ሁለቱ አይነት ኢትዮጵያዊ ማንነቶች ግን የታሪካችን ተጨባጭና በጎ ውጤቶች አድርጌ አያቸዋለሁ። ምንልባትም መጻኢው የኢትዮጵያ መልካም እጣም ያለእነርሱ እውን የሚሆን አይመስለኝም። ራሴንና መሰሎቼን እንዴት ከነገው መልካም ቀን አውጤቼ ልመለከት እችላለሁ? እንዴትስ፣ ”እንኳን የነገው አካል ልትሆን፣ ዛሬም የለህም” ስባልስ ዝም እላለሁ?! ኢትዮጵያዊነት አለ። የለም ስለተባለም አይጠፋም። እኔ አለሁ።
No comments:
Post a Comment