ሕገ-መንግሥቱ የሚፈቅድልኝን ሰላማዊ ሰልፍ እንዳላካሂድ ከልክለውኛል፤ አባላቶቼን ያለአግባብ በማንገላታት አስረውብኛል፤ ቅስቀሳ እንዳላካሂድ አግደውኛልና ድምፅ ማጉያዎቼን ቀምተውኛል ሲል አንድነት ለዴሞክራሲ ለፍትህና ፓርቲ (አንድነት) በሶስት የመንግስት ተቋማት ላይ ክስ መሰረተ። ፓርቲው በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 8ኛ ፍትሃ ብሔር ችሎት ላይ ክስ የመሰረተባቸው ተቋማት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ጽህፈት ቤት እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን መሆናቸውን በክስ መዝገቡ ተገልጿል።
ፓርቲው የዘወትር ፖለቲካዊ ስራዎቹን እንዳላያካሂድ መስተጓጉል ተፈጥሮብኛል በማለቱ ክሱ መዘጋጀቱን ለሰንደቅ ያስረዱት የሕግ ባለሙያው አቶ ተማም አባቡልጉ፤ በክስ ዝርዝሩ ውስጥ ፓርቲው በመስቀል አደባባይ የጠራው ሰልፍ እንዳይካሄድ ከመደረጉም በተጨማሪ የቅስቀሳ እገዳ፣ የአባላት መታሰርና የቁሳቁስ መነጠቅ ሁሉ ስለማጋጠሙ በክሱ ውስጥ በዝርዝር ተካቷል ብለዋል።
በከተማዋ ውስጥ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ከፈቃድ ሰጪ አካላት ፈቃድ መገኘት አለበት ቢባል እንኳን ተቋማት የተከተሉት አካሄድ አግባብነት የሌለውና ከሕግም ውጪ በመሆኑ ይህን ለመጠየቅ ክስ መስርተናል ብለዋል። የመንግሥት አካላቱን የሰልፍ እገዳ ተከትሎ አንድነት ፓርቲ ዘጠኝ የሚደርሱ አማራጭ የሰልፍ ቦታዎች ቢያቀርብም አንዱንም ሳይቀበሉ በራሳቸው ምርጫ ጃንሜዳ ላይ ሰልፍ እንዲካሄድ መፍቀዳቸው በሕጉ ላይ ከሰፈረውና ማንኛውም ዓይነት ሰላማዊ ሰልፍ ከጦር ካምፕ በ50 ሜትር ርቀት ላይ መካሄድ አለበት ከሚለው መመሪያ ጋር የማይጣጣም ነው ብለዋል።
ይህም በመሆኑ አንድነት ፓርቲ የመንግስት ተቋማት በጣምራ በመሆን ሕዝብን ለመቀስቀስ የሚደረገውን ጥረት ስልታዊ በሆነ መንገድ አስተጓጉለውብኛል ይላል።
በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 8ኛ ወንጀል ችሎት ክስ የተመሰረተባቸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ጽ/ቤት እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የተመሰረተባቸውን ክስ አስመልክተው በችሎት በመገኘት የሚሰጡትን መልስ ለማድመጥ ለየካቲት 24 ቀን 2006 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል። ምንጭ ዜና ሰንደቅ
No comments:
Post a Comment