Saturday, December 7, 2013

ከሳውዲ ተመላሽ ዜጎች ንብረታቸው በጉምሩክ እንደተወሰደባቸው ተናገሩ


ህገወጥ ናችሁ ተብለው ከሳውዲ አረቢያ ወደ አገራቸው የተመለሱ ኢትዮጵያዊያን፤ ለበርካታ አመታት ለፍተን ያፈራነውን ንብረት ይዛችሁ መግባት አትችሉም ተብሎ ተነጥቀናል፡፡ የፍተሻ ሰራተኞች ሻንጣዎቻቸውን በመፈተሽ፣ ሞባይል ከአንድ በላይ ከያዙ ትርፉን በማስቀረት፣ አዳዲስ አልባሳት እና ኤሌክትሮኒክስ ቁሰቁሶች የተወሰኑትን ብቻ በመፍቀድ እና ያመጡትን ወርቆች ግራም በመቀነስ ንብረታቸውን እየወሰዱባቸው እንደሆነ ተመላሾቹ ገልፀዋል፡፡ መሃመድ አባመጫ የተባለ የሳኡዲ ተመላሽ፤ ከሳውዲ ስድስት ሻንጣ ይዞ መምጣቱን ገልፆ፤ ቦሌ አውሮፕላን ማረፍያ ሲደርስ ግን ከሁለት ሻንጣ በላይ ይዞ መግባት እንደማይችል፣ ከአምስት ሞባይሎችም ሁለቱ ብቻ እነደተፈቀደለት ለአዲስ አድማስ ተናግሯል፡፡ የሳውዲ መንግስት ከአንድ ኪሎ በላይ ወርቅ ይዛችሁ መውጣት አትችሉም የሚል መመሪያ ማሳለፉን የጠቆመው ተመላሹ፤ ንብረቱን እዚያው ጥሎ ለመመለስ መገደዱን ገልጿል፡፡ የሳኡዲ መንግስት እንኳን ከወርቅ በስተቀር ሌላ ንብረታቸውን ሁሉ ይዘው እንዲወጡ መፍቀዱን የገለፀው መሃመድ፤ በአገራቸው ንብረታቸውን እንዳያስገቡ መከልከላቸው እንዳሳዘነው ይናገራል፡፡

ኤሌክትሮኒክስና ለቤተሰቦቹ ያመጣውን ልብሶች ቀረጥ ከፍለህ ነው የምትወስደው በመባሉ፣ ለሁለት ቀን በስደት ተመላሾች በተዘጋጀው ድንኳን ውስጥ ያለምንም ፍራሽና ልብስ ተኝቶ ንብረቱን ቢጠብቅም ማግኘት እንዳልቻለ ገልጿል፡፡ “ሳዑዲም እዚህም ሀገራችን ስንደርስ እየበደሉን ያሉት ሃበሾች ናቸው” ያለው መሃመድ፤ መንግስት በሚዲያ በተሟላና በተደላደለ መንገድ እንደሚቀበለን ቢገልፅም እዚህ የጠበቀን ግን ሌላ ነው ሲል ቅሬታውን ገልፆ “ሌላው ቢቀር እስካሁን ተመላሾቹን የሚያመላልሰው እንኳን የሳዑዲ እንጂ የኢትዮጵያ መንግስት አይደለም” ብሏል፡፡ ከሳኡዲ ካመጣችው ወርቅ ላይ ሃምሳ ግራሙን ብቻ እንደምትወስድ የተነገራት ተኪያ ሙሃመድን ያገኘናት በቁጭት መሬት ላይ እየተንከባለለች ነበር፡፡
ተኪያ እያለቀሰች እንደነገረችን፤ ለ14 ዓመት ሰርታ ከሶስት መቶ ሃምሳ ግራም በላይ ወርቅ እንዳጠራቀመች ገልፃ፤ በተፈጠረው ችግር ምክንያት ከሳውዲ እንድትወጣ ከመገደዷ በፊት ሙሉ ንብረቷን አስቀድማ ብትልክም እስካሁን እንዳልደረሰላት ትናገራለች፡፡ አሁንም፤ ከተመለሰች በኋላ የያዘቻቸውን ሻንጣዎች ለመውሰድ እንዳልቻለች የምትገልፀው ተኪያ፤ በፍተሻ ስም ሰራተኞቹ ሻንጣዋን በርብረው በማየት፣ ያመጣቻቸውን የኤሌክትሮኒክስ እቃዎችና ሶስት ሞባይሎች መውሰዳቸው ሳይንስ፣ ሶስት መቶ ግራም የሚመዝን የወርቅ ንብረቷን እንዳታስገባ መከልከሏን በጩኸት ትናገራለች፡፡ ለምን ንብረቷን እንደከለከሏት ስትጠይቅም “እናንተ ነጋዴዎች ናችሁ፤ በስደተኞች ስም ያለቀረጥ ንብረት ለማስገባት ትፈልጋላችሁ” በማለት ሰራተኞቹ እንደመለሱላት ገልፃ፤ ጉዳዩን ለአለቆቻቸው ለማመልከት ብትፈልግም የሚያናግራት ሰው አለማግኘቷን ጠቁማለች፡፡ በዚሁ ስፍራ ያገኘናቸው በርካታ ተመላሾች፤ የንብረታቸው ጉዳይ እንዳሳሰባቸው ይናገራሉ። ንብረታቸውን ሳይዙ ወደቤተሰቦቻቸው ላለመቀላቀል በሚል የተሰበሰቡበት ካምፕ፣ ምንም ለማረፊያ የተመቻቸ አገልግሎት ባለመኖሩ መቸገራቸውንም ገልፀዋል፡፡ መንግስት የሚሰጣቸውን 900 ብር፣ በትራንስፖርትና በስልክ አገልግሎት እንደሚጨርሱ አክለው ተናግረዋል፡፡
በርካቶች በእቃዎቻቸው መታገድ በመበሳጨታቸው ጭቅጭቅና አላስፈላጊ ውዝግብ ውስጥ ለመግባት መገደዳቸውን ተመላሾቹ ይናገራሉ፡፡ “ስንመጣ የሚሰጠንን ሊሴ ፓሴን አይተው ማስተናገድ ሲገባቸው እነሱ ግን ንብረታችንን እየወሰዱብን ነው” በማለት የሚናገሩት ተመላሽ ዜጎቹ፤ “ምናልባትም ንብረት የላቸውም ብለው አስበውን ይሆናል፤ ነገር ግን በርካታ አመታት ስንቆይ መቼም ባዶ እጃችንን አንመጣም” በማለት በምሬት ይናገራሉ፡፡ “ዛሬ እቃችንን የከለከሉን ነገ ምን ተስፋ ይዘን ነው ተደራጅታችሁ ስራ ስሩ ለሚሉን?” የሚሉት እነዚህ ተመላሾች፤ “በመንግስት ላይ አመኔታ የጣልነው ሳውዲ ድረስ በተወካዮቹ አማካኝነት መጥቶ ባናገረን መሰረት ነበር፤ ነገር ግን የተገባልን ቃል ታጥፏል” ይላሉ፡፡ መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት ባለመስጠቱ እና ለቤተሰብ መርዶ ባለመነገሩ፣ ለሚያውቋቸው ቤተሰቦች መርዶ ለመንገር ጭንቀት ላይ መሆናቸው ሌላ ችግራቸው እንደሆነ የተናገሩት ተመላሾች፤ አሁንም ቢሆን ሳውዲ ላይ ሃበሻዎችን በመኪና እየገጩ መግደል የሳውዲ ፖሊሶች የቀን ተቀን ስራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ታዲያ በዚህ አጣብቂኝ ውስጥ አምልጠው የሚመለሱ ዜጐችን ንብረት መቀማት ምን የሚሉት ተግባር እንደሆነ አልገባንም፤ በማለት አማርረዋል-ተመላሾቹ፡፡ ምናልባትም የፖለቲካ ማራመጃ ሊያደርጉን ነው በማለትም ስጋታቸውን አንፀባርቀዋል፡፡
ተመላሾቹ የተሟላ መጠለያ ተዘጋጅቶላችኋል በተባለበት ቦታ ሳይቀር፣ መተኛ ሥፍራ እንኳን እንዳልተዘጋጀ ሲረዱ ተስፋ መቁረጣቸውን እና ንብረታቸውን እንዳያስገቡ ሲከለከሉ፣ ተመልሰው በህገወጥ መንገድ ለመሰደድ ሙከራ መጀመራቸውን ይገልፃሉ፡፡ በጉዳዩ ላይ መልስ እንዲሰጡን የጠየቅናቸው የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በበኩላቸው፤ “ተመላሾቹ ስለንብረት የሚያነሱትን ጥያቄን በተመለከተ፤ እኛ ተመላሾች በሙሉ ንብረት እንደሌላቸው ነው የምናውቀው“ በማለት ተናግረዋል፡፡ አምባሳደሩ አልፎ አልፎ ባዶ እግራቸውን ከሳዑዲ የተመለሱ እንዳሉ ጠቁመው፤ በሳኡዲ መንግስት ጓዛችሁን ይዛችሁ እንዳትወጡ ተከልክላችኋል በመባላቸው፣ መጀመሪያውኑም ንብረት ይዘው ባለመምጣታቸው ነው፤ ብለዋል፡፡ እነዚህ ዜጎች ከመደበኛ የአየር መንገዱ ተጓዦች እኩል እንደማይስተናገዱና ለብቻቸው ተጠብቀው እንደሚስተናገዱ ገልፀው፤ ምናልባት ከነዚህ ዜጎች ጋር ተቀላቅለው የሚመጡ ሌሎች ሰዎች ስለሚኖሩ እሱን ለማጣራት ንብረታቸው ይፈተሻል እንጂ ማንም የእነሱን ንብረት የሚወስድ እንደሌለ የተናገሩት አምባሳደሩ፤ እንኳን በሀገር ውስጥ የገባ ንብረት፣ ሳዑዲ ያለውንም የላባቸውን ውጤት ለማስመጣት እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡
የሟቾችን ቁጥር እና ለቤተሰቦቻቸው መርዶ አለመንገርን በተመለከተ አምባሳደሩ በሰጡት ምላሽ፣ አሁን ሙሉ በሙሉ ትኩረታችን በህይወት ያሉ፣ ንብረታቸውን ያጡ እና ጉዳት የደረሰባቸው ላይ ነው፤ ብለዋል፡፡ የሟቾቹን ቁጥር በተመለከተ ግን መንግስት ከገለፀው በኋላ፣ የተፈጠሩ ነገሮች መኖራቸውን አምነው፤ ነገር ግን ቁጥሩ ላይ ተመላሾች የሚሉትና አንዳንድ ሚዲያዎች የሚያወሩት ትክክል ሊሆን ቢችልም የተጣራ ነገር እስካላገኘን ድረስ የሞቱበትን ሁኔታ ለማወቅ ያስቸግራል፤ ብለዋል፡፡ የሳውዲ አየር መንገድ እንጂ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በመመለሱ ሂደት ምንም አስተዋፅአ ለስደተኞቹ አላደረገም ለተባለው አምባሳደሩ መልስ ሲሰጡ፡- የሳውዲ አውሮፕላን የሚያመላልሰው እራሱ በማባረሩ ምክንያት ነው፤ ወጪውን የሚችለውም እራሱ ነው ብለዋል፡፡
addis admas

No comments:

Post a Comment