ዳኛቸው ቢያድግልኝ
በቅርቡ የሴቶችን ቀን አስመልክቶ በተደረገ የሩጫ ዝግጅት ወቅት የሚኒሊክና የጣይቱ ልጆችነ ነን ያሉ የሰማያዊ ፓርቲ ወጣት ሴቶች “አትለያዩን! አትከፋፍሉን! ነፃነት እንሻለን! ለድሃው ይታሰብለት! ኑሮ ከበደን! ውሃ ጠማን! መብራት ናፈቀን!” በማለት በጣም ሰብዓዊና እናታዊ ጥሪ ጮክ ብለው አሰምተው ነበር። ይህም መልካም ድርጊታቸው ለፍትህና ለአንድነት የሚደረግ ህዝባዊ ጥሪ በሚያስበርግጋቸው የወያኔ ባለስልጣናት ሁከት ፈጠራ ተብሎ ተወነጀሉ። ፕሮፌሰር አልማርያም በተቆጣው ብዕራቸው
ጩሀቴም ቀደም ሲል በግፍ ለታጎሩ የህሊና እስረኞችና ሰሞኑን ለታፈሱት የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችና ደጋፊዎች አንዲሁም ለጎበዞቹ የዞን ዘጠኝ የሕዝብ አፈቀላጤዎችም (ብሎገሮችም) ነጻነት ያለኝ ጽኑ ፍላጎት መገለጫ ነው።… ያገሬ ወይዛዝርቶች በምህረት አልባ ጨካኞች ሲንገላቱና ሲወገሩ ከዳር ቆሜ ማየትን ህሊናዬ ፈጽሞ አይፈቅድልኝም። ይልቁንም የእንግልታቸው ምክንያት ሰብዓዊ በሆነው መብታቸው ድምፃቸውን ስላሰሙ በመሆኑ የነሱና የመሰሎቻቸውን ጥሪ በዚህም ሳቢያ የሚደርስባቸውን አበሳ ሁሉ ለአለም አሳውቅ ዘንድ ድምጼን ከፍ አድርጌ እጮሃለሁ…
ሁከት ማለት የሌሎችን ሰላም ማደፍረስ፥ አምባጓሮና ጸብ ማንሳትና ማነሳሳት፥ የንብረት ጥፋትና በሰዎች ላይ አካላዊና ስነልቦናዊ ጉዳትን ማስከተል ነው። እኒህ ወጣት ሴቶች ግን ከዚህ በተቃራኒው የተንገላቱት ሰላም አንዳይደፈርስና ህዝብ እንዳይጎዳ በስልጣን ላይ ያሉት መንግስታዊ ግዴታቸውን እንዲወጡ ሰላማዊ ጥሪ ነበር ያቀረቡት። የሀሰት ፕሮፖጋንዳው ሰለባ ያልሆነ በሙሉ ወጣቶቹ በአንድነትና በፍትህ የጸናች ሀገር ለመረከብ ከዚህ የበለጠ ቢያደርጉም ተገቢ ነው የሚል ይመስለኛል። የነርሱ አሳሪዎች በነርሱ እድሜ ጠመንጃ አንስተው መጥፎ ነው ብለው የፈረጁትን መንግስት ለመዋጋት ጫካ መግባታቸውን አለመርሳት ብቻ ሳይሆን እንደትልቅ ገድል በየመድረኩና በየመጽሀፉ ሲናገሩና ሲያስነግሩ እንሰማለን። ታዲያ የዛሬው ትውልድ ያውም እንደነሱ ሰው ለመግደል ጠብመንጃ ሳያነሱ ፍትህ አይጉዋደል ብለው በሰላም መጠየቃቸው እንዴት መጥፎ ሁኖ ነው ለእስርና እንግልት የሚዳርጋቸው? ማሰርንና አፈናን እንደ የስልጣን ዘመን ማራዘሚያ አማራጭ አድርጎ መውሰድ ከሚያስብ አእምሮ ሳይሆን በፍርሃት ከተዋጠና ለውጥ አይቀሬ መሆኑን መቀበል ካቃተው ደካማ ጭንቅላት የሚመጣ ነው። በአንጻሩም ነገ የነርሱ የሆነው ወጣቶች በፍርሀት ተገንዘው አረመኔዎች ሀገራቸውንና ተስፋቸውን ሲያጠፉባቸው በዝምታ ሊያዩ አይቻላቸውም።
ለዚህም ነው በወጣቶቹ የሠማያዊ ፓርቲ መሪዎችና ደጋፊዎች ላይ ያለኝን ጽኑ እምነት መግለጽ የምሻው። የወጣቶች መነሳሳት ለሁሉም ወገን ብርታትን የሚሰጥ ነው። የለገመ፣ የሰነፈና ተስፋ የቆረጠ ወጣት የሞላበት ሃገር ሕዝብ መቃብር አፋፍ እንደቆመ ለቀስተኛ ነው። ለቀስተኛ መቼም ቢሆን ስለሚቀብረው ሰው ከሚሰማው ሀዘን ባሻገር እርሱም ነገ ሙዋች መሆኑን እያሰበ ሙዋቹን አፈር እራሱን ትካዜ አልብሶ ተስፋን ሳይሆን ፍርሀትን ሰንቆ ይመለሳል። ሀገር ተስፋ በቆረጠና ሽንፈትን በጸጋ በተቀበለ ወጣት ከተሞላች ቀብርዋ ተቃረበ ማለት ነው። ስለዚህ የሀገራችን ወጣቶች ተስፋ የሰነቁ፣ የበረቱና በእውቀትና ስነምግባር የታነጹ እንዲሆኑ ሁላችንም የየአቅማችንን ማድረግ ይኖርብናል። የሀገራችን ሰዎች “እናት የሞተች ቀን በሀገር ይለቀሳል… ወንድም የሞተ እንደሁ በሀገር ይለቀሳል…. ሀገር የሞተ እንደሁ ወዴት ይደረሳል?” ይሉ የነበረው ያለምክንያት አልነበረም። እናም የዛሬን ወጣቶች ድርጊት ከቀድሞው የሃበሻ ጀብዱ (የሀበሻ ጀብዱ ከሚለው መጽሀፍ) ጋር ጣምራ ቅኝት ላደርግበትና ወጣቶችን ላደንቅበት መርጫለሁ።
ስለምን የሃበሻ ጀብዱን እንደመረጥኩ ግን እመለስበታለሁ። የጣልያኑም ወረራ ሆነ የባንዳ መራሹ ወያኔ አገዛዝ ለኢትዮጵያ የሚበጅ አይደለምና ሀገሪቱን ወደተሻለ መንገድ ለመውሰድ የሚደርገው ጥረት ኢትዮጵያውያን ነን ለሚሉ ሁሉ የህልውናና የነፃነት ፍልሚያ መሆኑ ግልጽ ሊሆን ይገባል። የሠማያዊ ፓርቲና የትግራይ ተገንጣይ ነን የሚሉትን አቅም በመፈተሽ መንደርደርያውን ማጎልበት ያስፈልግ ይሆናል። ይህም መድፍ ተኳሽና በአውሮፕላን መርዝ የሚርጭን የግራዚያኒን ጦርና ነጠላ ለባሽ ባለጎራዴ እግረኛን እነደማወዳደር ማለት ነው። ምንና ምን ታወዳድራለህ የሚሉ እንዲህ ብለው ሊሞግቱኝ ይችላሉ።
ሰማያዊ ፓርቲ የወጣቶች፣ ተገንጣዮቹ እድሜ ጠገቦች ፤ ሰማያዊ ፓርቲ ባዶ ኪስ፣ መንግስት ነን የሚሉት ደግሞ የሀገሪቱን ሃብት የግላቸው ያደርጉ ዲታዎች አዎ ምንና ምን? ሰማያዊ ፓርቲ ብእርና ወረቀት ፣ ወያኔዎች ባለታንክ፣ አውሮፕላን መድፍና መትረየስ ታጣቂዎች። እናም የማይቻል የሚመስለውን ይቻላል የሚሉ ወጣቶችና ሰው እንደዘበት መፍጨት የማይገዳቸው ‘ተራራ አንቀጥቃጮች’ እንደምን አድርገው መጋጠም ይችላሉ? በዚህ አይነት ንፅፅር ተስፋ የቆረጡት ወገኖች “ይቻላል!” ብለው የተነሳሱትን ወጣቶች “እንዲያው አርፈው ቢቀመጡ ነው የሚሻለው። በአጉል ወኔ ተነሳስተው ማለቅ ብቻ ሳይሆን እኛንም ያስጨርሳሉ። ጊዜው አሁን አይደለም” የሚል ምክር ቢጤ ሲሰጡ ይሰማሉ። የፖለቲካ መሪና ጠቢብ ነን የሚሉም “ለአሁኑ ወያኔ ስልጣን ላይ ቢቆይ ይሻላል” ሲሉ ተደምጠዋል አሉ።
እውነትም ብቸኛ ሃይል መመዘኛ ሁኖ የሚታየው የጠብመንጃው ቁጥርና የመግደል አቅም ከሆነ ያስፈራል። እውነታው ግን የሀይል ምንጭ የጠብመንጃና የጦር ጋጋታ ብቻ አይደለም። ከጠብመንጃ በላይ የዘላቂ ሀይል መሰረቱና የመጨረሻ ድል አጎናጻፊው እውነትና ፍትሀዊ ምክንያት ነውና።
ጊዜው ዛሬ አይደለም የሚሉትም መካሪዎች ጊዜው መቼ እንደሚመጣ ቢያሳውቁንም ደግ ነበር። ኬይንስ የሚባለው የምጣኔ ሀብት ምሁር እንዳለው “ከረጅም ጊዜ በሁዋላ ሁላችንም ሙዋች ነን።” ስለዚህም የዛሬውን ነጻነታችንን ተነፍገን በነገ ተስፋ ብቻ ተሸንግለን ግፍን በፀጋ እንድንቀበል መመከራችን ደግም አይደለም። ነፃነት ተነፍጎ፣ ፍትህን አጥቶ፣ በደልን ተሸክሞ ተስፋ ቢስም ሆኖ መኖር አይቻልም። በደል ሲበዛ በቃኝ ማለት የሰው ልጅ ትክክለኛ ባህርይ ነው። ቢሆንም በርካቶች “እግዜር ያመጣውን እግዜር እስኪመልሰው” ሲሉ ይደመጣል። እግዜር የሌለውን አመል አውጥቶ ጥላቻ ቢለማመድ እንኳን እነዚህ አረመኔ ወንበዴዎች ለዚህን ያክል ጊዜ አናታችን ላይ ሁነው እንዲጨፈጭፉን አያዝብንም።
ፍትህና ነጻነት የሚገኘው በፀሎትና ልመና ብቻ ቢሆንማ ኖሮ አውሮፓውያን ሰሜን አሜሪካ ዘልቀው ሀገሬውን በበሽታና ረሀብ ሲጨፈጭፉት፣ እግዜሩ ዝም አይልም ነበር። አዎን እሱ መሬት ወርዶ ፍርድ የሚሰጥ ቢሆን አውሮፓውያን ጥቁር አፍሪካን ባርያ አድርገው በገዛ ምድሩ ላይ የግፍ ግፍ እየፈጸሙበት የእግዜርን ስም እየጠሩ መስቀልና መጽሀፍ ቅዱስ ይዘው ሲያስገበሩት ዝም ባላለ ነበር። ስለዚህም ነው ለነጻነት ሲባል ታንኩንም መትረየሱንም እንደነ አቡነ ጴጥሮስ መጋፈጥ የግድ የሚሆነው። ጸሎት ለብርታት ጥሩ ነውና ባይሆን እመብርሃን ለልጅሽ በደሌን እንደኔ ሆነሽ ንገሪልኝ ማለት፣ አላህንም ልጆችህ መከራችንን ከትከሻችን አሽቀንጥረን እንጥል ዘንድ ጉልበትና ብልሃት ጀባ በለን እያሉ መለማመን ጥሩ የሚሆነው። ግን ለብቻው በቂ አይደለምና ወጣቶች እንደ የግል ሀይማኖታቸው እያመለኩ እንደ እምነታቸው በጋራ ለነፃነት መታገላቸው የሚያበረታታንም ለዚህ ነው።
አሁን የሃበሻ ጀብዱን ለምን እንደጻፍኩ ላስረዳ አዎን የጣልያን ጀነራሎችን ሹምባሾችና አስካሪዎችን አስታውሼ መሆን አለበት። ታንኩንም፣ አውሮፕላኑንም መድፉንም መትረየሱንም ጭምር። የባንዳ ውርንጭሎችን፣ ልጆችና የልጅ ልጆችንም እንዲሁ አስቤያቸው ነው።
እነዚህ ነጠላ ላባሽ ባዶ እግር ተጓዥ ኢትዮጵያውያን በጣም የሚገርሙ ነበሩ። ኩራታቸውና በራሳቸው የመተማመን አቅማቸው ለውድድር አይመችም። እንደ ሀይል አሰላለፍ ቢሆን ከጣልያን ጋር ደፍሮ መጋጠም ከሞኝነት አይቆጠርም ትላላችሁ? ካላቸው የመሳርያና የወታደር ብዛት፣ ሰልጥኛለሁ የሚለው የነጩ ዓለም ያለው ጉልበትና ስልጣኔን የሚያውቅ ሰው በባዶ እግሩ ታንክ መግጠም ሞኝነት ነው ቢባል ማመን ብዙም ላይከብድ ይችላል። ለነርሱ ማን አልተንበረከከምና? ማንስ ቅኝ ግዛት አልሆነምና! ግን ኢትዮጵያ ምድር ላይ ታንክ በጎራዴ ድል ሆነ። አንዴ ቢሆን እድል እንለዋለን ሁለቴ ሶስቴም ሆነ። ሁለቴም ሶስቴም ነጠላ ለባሽ በባዶ እግር የሚጓዝ እግረኛና ቆመህ ጠብቀኝ ምንሽር ባለአውሮፕላንና ባለታንኩን ድል ነሱት። ግን ይህ አሸናፊነት እውን የሆነው ትክክለኛ ስነልቦና፣ አልገዛም አልንበረከክም የሚል እምቢ ባይነት ስለነበረ ነው። ለነፃነቱ ቀናዒ መሆን ከዚያም በላይ ወንድም የወንድሙ ተበቃይ መሆኑን ነበር። አይዞህ ባይና አጋር አብራ በረሃ ለበረሃ የምትጓዝ ጓድም ነበረችው። እሷን ማሳፈር ለባርነትም አሳልፎ ከመስጠት ሞቱን ይመኝ ስለነበር ነው። ሴቲቱም ብትሆን እርሱ ለነጻነቱ ሞቶ ግን የርሱን የጀግናውን ስም ይዘው ትውልድ የሚቀጥሉት ልጆቻቸው በነፃነት ቢኖሩ ምርጫዋ ስለነበረ ነው። የሴቶቹ ጀግንነትና ድፍረት ለወንዶቹም መነሳሳትና መበረታት ምክንያት ይሆናቸው ስለነበረ ነው የሚል ሃሳብን ነበር የሃበሻ ጀብዱን የጻፈው ፈረንጅ አዶልፍ ፓርለሳክ የዘገበው። “እነዚህ ነጠላ ለባሽ እግረኞች ይላል አዶልፍ ፓርለሳክ በጠላት መትረየስ አስሩ ሲወድቁ ሃያው ወደፊት ይገፋሉ ሃያው ሲወድቁ ሃምሳው ወደፊት ይገፋሉ ለሞት እየተጋፉ ወደፊት ይገሰግሳሉ እናም ያሸንፋሉ” ብሎ ሺህ ጊዜ አድናቆቱን መሰከረላቸው። እርግጥም ፍርሃቱን ያሸነፈ ጀግና ነው! እንዲያውም ነገስታቱ ወይም መሪዎቹ እየገቷቸው እንጂ ጣልያንን ድባቅ እየመጡ ቀይ ባህር ሊከቱ የሚችሉ ጎበዞች እንደሆኑ ሲጽፍ ገድላቸው በዐይነህሊናው የሚታየው ይመስላል። ታድያ ከሰማያዊ ፓርቲ ጋር ምን አገናኘው ሰማያዊ ሰላማዊ ትግል ነው ታንክና ጎራዴን ምን አገናኘው? ለሚሉ በሚከተለው አስተያየት የተነሳሁበትን ለመደምደም እሞክራለሁ።
ልክ ይህንን ታሪክ አስቀምጠው የነገሯቸው አዛውንቶች ያሉ ይመስል ባዶ እጃቸውን ነፃነት ወይም ሞት ያሉ ቆራጦች የሰማያዊ ፓርቲ ወጣቶች ጀግነው ተነስተዋል። ይህንን መነሳሳት ደግሞ በሚገባ አሳይተዋል። አምስት ሲታገትባቸው አስራ አምስት ሆነው ይተማሉ፣ አስራ አምስት ቢታገት አምሳ አምስት ይሆናሉ። ስለዚህ የነጻነት ፍላጎታቸው ካልሞተ ለነፃነት የሚያደርጉት ትግል እንደማይቆም ግልጽ ነው። አዎ በጎበዝ አለቃ ተደራጅቶ በባላባት በባላባት ተጠራርቶ የወጣው ጀግና እንደዚያ ነበር ነፃነትን የተቀዳጀው። ሰማያዊ ፓርቲም መሪው ሲታሰር ሽባ የሚሆን ጥቂት አባላት ቢታገቱ የሚሽመደመድ እንዳይሆን ሆኖ የተደራጀ ይመስላል። እንደዚያ ሆኖ ሊጠናከርም ይገባዋል። ወጣት ወጣት የሚሸት እንቅስቃሴ ተስፋ ይሰጣል። ነቅተው ሌሎችንም የሚያነቁ፣ ጎብዘው ሌሎቸንም የሚያበረታቱ በዘርፈ ብዙው ትግል ውስጥ ብዙሃኑ እንዲሳተፉ ያበረታታሉ። ለዚህም ነው ታስረው ታስረው የማያልቁ… ከጎንደር መልስ አዲሳ አበባ፣ ከአዲስ አዋሳ እያሉ ሺህ ሚሊየን ወጣቶች ለነፃነትና ለክብር ሲቆሙ የምናየው። ያኔ በጠላት ወረራ ጊዜ አቢቹ የሚባል ለጋ ወጣት ነበር በወንድሞቹ ሞት ማግስት ጨርቄን ማቄን የማይሉ 200 ጎበዞች ብቻ ስጡኝ በማለት የራሱን ጦር ሊመራ ወሰነ። የርሱ የነበሩ በሬዎችን አሳርዶ የወንድሞቹን ተዝካር አወጣና ወደ ደፈጣ ውጊያም ገባ። ያ ወጣት ለጣልያን ያደሩ የትግራይ ሽፍቶችን ጨምሮ ጣልያኖችን አርበደበዳቸው። የ16 አመት ወጣት ምንም የጦር ስልጠና ያልነበረው ጀግና ሰልጥነናል ያሉትን መግቢያ መውጫ አሳጣቸው። ምንም እንኳ ከጀግኖቹ ተርታ ስሙን ሊናገሩ ያልፈለጉ ቢኖርም እንኳ ዛሬ ታሪኩ ታውቆ ወደፊትም ሲነገርለት ይኖራል። የዛሬዎቹ ወጣቶች በውል የሚያውቁት ወያኔን ብቻ ነው። ወያኔ ጸረ ኢትዮጵያ ፕሮፓጋንዳውን በሚነዛበት ሀገር ነው ያደጉት። ይሁን እንጂ የማይሞተው ኢትዮጵያዊነትና የነጻነት ጥያቄ አነሳስቷቸዋል። ዛሬም ብዙ አቢቹዎች ይኖሩናልና የወጣቶች መነሳሳት የነፃነት ብስራት ነው ስንል ከጎናችሁ አለን እያልናቸውም ነው። ሞት እስርና እንግልት ሌሎችን ወደፊት ያመጣል። ትግሉ ስልጣን መያዝ አይደለም ስልጣን በሰላማዊ መንገድ የሚያዝበትን የእኩልነት የነፃነት ብስራት የሚሰበክበትንና በተግባርም የሚረጋገጥበትን ጎዳና መቀየስ ነውና ለዚህ ቅዱስ ዓላማ አሁን ተመሳሳይ ዓላማ አለን የሚሉ በተለያየ የትግል ስልት ግን ለነፃነት ለሚታገሉ ሁሉ ብርታትና መነሳሳትን ይፈጥራሉ። ኢትዮጵያ ከጎጠኛ ወራሪዎችና አገር አፍራሾች ነፃ እስክትሆን ድረስ ትግሉ ይቀጥላል።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ።
No comments:
Post a Comment